የካሪታስ ዋና ተግዳሮቶች 'በዓለም ላይ በጣም ድሃ የሆኑ ሰዎችን መድረስ ነው
ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
22ኛው የካሪታስ ዓለም አቀፍ ጠቅላላ ጉባኤ በሮም እየተካሄደ ሲሆን አዲስ የተመረጡት ፕሬዝዳንት እና ዋና ፀሀፊ ለዓለም አቀፉ ኮንፌዴሬሽን ቀጣይ ጉዞ የሚመሩበትን ስልታዊ ዕቅድ ጋዜጣዊ መግለጫ በማዘጋጀት ጉባኤውን ማክሰኞ ዕለት ሊያጠናቅቁ ዕቅድ ተይዟል።
ሰኞ ዕለት ልዑካኑ ኪርስቲ ሮበርትሰንን የዓለም አቀፉ ካሪታስ ምክትል ፕሬዝዳንት አድርገው መርጠዋል። ክርስቲ እ.አ.አ. ከ2019 ጀምሮ የካሪታስ አውስትራሊያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው አገልግለዋል ፥ ከዚህ ቀደምም በካሪታስ አውስትራሊያ የፓሲፊክ ፕሮግራሞች አስተባባሪ እና የግንኙነት ቡድን መሪነትን ጨምሮ የተለያዩ የሥራ ቦታዎች ላይ ሠርተዋል።
ሮበርትሰን ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት በዓለማችን ከ160 በላይ ሀገራት የተውጣጡ የካሪታስ ቤተሰብ አባላት “የወንድማማችነት አዲስ ጎዳና መገንባት” በሚል መሪ ቃል አንድ ላይ ተሰባስበዋል።
“ወደዚህ ስብሰባ የመጣነው የእርስ በእርስ ግንኙነቶችን ለመገንባት እና ለማጠናከር ሲሆን ፥ ነገር ግን ራሳችንን በአዲስ አካሄድ ገንብተን ለኮንፌዴሬሽኑ አዲስ መንገድ ለማዘጋጀት መሆኑንም ጭምር በመረዳት ነው” ብለዋል። ‘በ6 ቀናት ስብሰባ ላይ ሁሉም ተሳታፊዎች እንደ ኮንፌዴሬሽን አዲስ የቀጣይ መንገድ አቅጣጫ ለመንደፍ ፈቃደኞች እንደሆኑም ግልጽ ነው’ በማለት አክለውበታል።
“የዓለም አቀፍ ካሪታስ አባል የሆኑ162 ሃገር አቀፍ የካሪታስ አባል ድርጅቶችን ያቀፈው እና በሰብአዊ ሥራ ላይ ፣ በአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ላይ እና በዘላቂ ዕርዳታ ላይ የተሰማራው ‘የቤተ ክርስቲያን የእርዳታ እጆች’ በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ካሪታስ ትሥሥር ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ባለፈው ህዳር ጊዜያዊ አስተዳደር ከሾሙለት በኋላ አሁን ላይ ጥልቅ ተሃድሶ ላይ እንዳለም አዲስ ተመራጯ ወይዘሮ ክርስቲ ገልፀዋል።
ወይዘሮዋ እሁድ ዕለት ካሪታስ ኢንተርናሽናልስ የሚሰራውን ‘የተልእኮውን የጋራ እሴት’ ለማጉላት የድርጅቱ አዲስ ስትራቴጂያዊ ማዕቀፍ መጀመሩን ጠቁመዋል።
“ሁሉም አባሎቻችን ወንድማማችነትን ለመገንባት እና በዓለም ላይ ያሉ እጅግ በጣም ድሃ ህዝቦችን ለማገልገል አዳዲስ መንገዶችን በመፈለግ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ናቸው” ሲሉም ተናግረዋል።
አዳዲስ ተግዳሮቶች
አዲሷን የካሪታስ ምክትል ፕሬዝዳንት ወደፊት በሚመጣው የሥራ መንገድ ላይ ዋና ዋና ፈተናዎች ሆነው ምን እንደሚጠብቃቸው ተጠይቀው ፥ “እንደተለመደው ዓለም አቀፉን ካሪታስ የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች የዓለም ድሃ ህዝቦችን የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች ናቸው” ብለዋል።
“በአሁኑ ወቅት በዩክሬን ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ክፍሎች እና በአፍጋኒስታን እየተደረጉ ያሉ ግጭቶችና እና እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተከሰቱ ተግዳሮቶች በኦሽንያ እና በአፍሪካ ውስጥ የምናገለግላቸውን ማህበረሰቦች ምን ያህል እየተጎዱ እንዳሉ እያየን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
“የዓለም አቀፉ ካሪታስ ፈተናዎች የግድ የእኛ ፈተናዎች ሊሆኑ አይችሉም”
ወይዘሮ ሮበርትሰን በመቀጠል “እንደ ድርጅት ፥ ትኩረታችንን ዛሬ በምናገለግላቸው ሰዎች ላይ ማድረግ እንፈልጋለን ብለዋል።
አዲስ ስለተመረጡት ፕሬዝዳንት መደሰታቸው
ኪርስቲ ሮበርትሰን ፥ ሊቀ ጳጳስ ታርሲየስ ኪኩቺ እንደ አዲሱ የካሪታስ ኢንተርናሽናል ፕሬዝደንት ሆነው በመመረጣቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ፥ የምርጫው ሂደቱ እጅግ ንፁህ ፣ ግልጽ እና ፍትሃዊ እንደነበር ተናግረዋል። በማከልም “የኮንፌዴሬሽኑ አባላት ተስፋ አድርገውት የነበረው ይህንኑ ነበር” ብለዋል።
‘የቶኪዮው ሊቀ ጳጳስ የዓለም አቀፍ ካሪታስ ፕሬዝደንት ሆነው በተመረጡበት ወቅት ልዑካኑ ድጋፋቸውን ገልጸዋል ፥ ይህም ከሁሉም የካሪታስ አባላት ያላቸውን ድጋፍ አጉልቶ አሳይቷል’ በማለት ሃሳባቸውን ደምድመዋል።