ፈልግ

ዓለም አቀፉ ካሪታስ እንተርንሽናሊስ 70 አመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር የሚያሳይ ዓርማ ዓለም አቀፉ ካሪታስ እንተርንሽናሊስ 70 አመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር የሚያሳይ ዓርማ  

ካሪታስ ኢትዮጵያ በሃገሪቱ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ተባለ

ካሪታስ ኢትዮጵያ አባል የሆነበት ‘ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ’ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ200 በላይ አገሮች እና ግዛቶች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የ163 የካቶሊክ የዕርዳታ ፣ የልማት እና የማህበራዊ አገልግሎት ድርጅቶች ኮንፌዴሬሽን ነው።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ  

በጀርመን ሃገር እ.አ.አ. በ1897 (1889 ዓ.ም.) ሎሬንዝ ዋርትማን በሚባል አንድ ትሁት ሰው የተጀመረው ዓለም አቀፉ ካሪታስ (ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ) ፥ ፍቅር እና ርህራሄ ወይም ‘በህዝቦች መሃከል ያለ ፍቅር’ የሚል ትርጉም ያለውና በላቲን ቃል የተሰየመው ድርጅት አሁን ላይ በዓለም ላይ ካሉት ትልቅ የዕርዳታ እና የልማት ተቋማት አንዱ ለመሆን በቅቷል። በ 20 ኛው ክፍለ ዘመንም ጆቫኒ ባቲስታ ሞንቲኒ የተባሉ ሰው ፥ በኋላ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ ሆነው በቅድስት መንበር የተሰየሙት ፥ ለዚህ ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ መታወቅ ትልቅ መሠረት ጥለዋል። በዚህም መሰረት እ.አ.አ. በ1954 በዓለም አቀፍ ደረጃ ‘ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ’ በይፋ እውቅና አግኝቷል።

 ወደ እኛ ሃገር ስንመጣ ፥ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ማሕበራዊ ልማት ኮሚሽን ወይም ‘ካሪታስ ኢትዮጵያ’ ተብሎ የሚታወቀው ተቋም መቼ ተመሰረተ ፣ በሃገራችንስ ምን ምን ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል የሚለውን ጥያቄ የሚመልሱልን አቶ ሺፈራው ማሞ የካሪታስ ኢትዮጵያ የማህበራዊ ልማት ኮሚሽን የፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ ፥ ካሪታስ ኢትዮጵያ በ 1957 ዓ.ም. እንደተመሰረተ እና ፥ በ 1992 ዓ.ም. ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት እውቅና አግኝቶ መመዝገቡን አብራርተዋል። የመጀመሪያ ተልእኮውንም ያደረገው በኢትዮጵያ የዓለም አቀፏን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የማህበራዊ እና ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ሥራ ማስተዋወቅ እና ማስተባበር እንደሆነ እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ከ150 ዓመታት በፊት ጀምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ተበታትነው ሲሠሩ የነበሩትን የልማት ሥራዎች አንድ ላይ በማቀናጀት ፥ የ13 ቱም ሃገረ ስብከቶች እንዲሁም 67 የሚሆኑ ማህበረ ምእመናን ከብሄራዊ ጽ/ቤቱ ጋር አንድ ላይ ሆኖ በተዋቀረ ሁኔታ በሁሉም ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች እንዲሠራ ተደርጓል ይላሉ አቶ በቀለ። አያይዘውም ቤተክርስቲያኒቷ ለሁለንተናዊ የሰው ልጅ እድገት እንደመስራቷ መጠን በየሃገረ ስብከቶቹ የምታከናውናቸውን ሃዋሪያዊ ሥራዎች ጎን ለጎን ፥ ስታከናውናቸው የነበሩትን  የማህበራዊ ልማት ኮሚሽን መርሃ ግብሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በሂደት በገጠርና በከተማ በህዝቡ ህይወት ላይ ዘላቂ ለውጥ በማምጣት ረገድ የሚታይ ስኬት እያስመዘገቡ እንደሚገኙና ፥ ካሪታስ ኢትዮጵያ ጥራት ያለው ትምህርት ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ እና የምግብ ዋስትና ፣ የማህበራዊ መልሶ ማቋቋም ፣ የውሃ ሥራዎች ፣ የአካባቢ ጽዳትና ንፅህና ፣ የጤና እና የኤች አይ ቪ/ኤድስ ትምህርት ፣ ከስደት እና ከስደተኞች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ፣ በሴቶች እና ቤተሰብ ጉዳዮች እንዲሁም አቅምን በማጎልበት በማህበረሰብ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየሰራች ትገኛለች ። ይህ ብቻም አይደለም ፥ የልማት ፕሮግራሞችን በማበልፀግ ፣ እና የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት ዘመቻዎችን በሴቶች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ በኩል የማጎልበት ሥራዎችን ትሠራለች።

በተጨማሪም የረዥም ጊዜ መርሃ ግብሮችን በመዘርጋት ፥ ለምሳሌ ለሴቶች እና ለወጣቶች አማራጭ የገቢ መንገዶች በመፍጠር የስደተኞችን ቁጥር በመቀነስ ረገድ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልፀው ፥ ይህንንም የምታከናውነው በየሃገረ ስብከቶቹ ላይ እና በየፕሮጀክቶቹ ላይ በምትከፍታቸው ጽ/ቤቶች አማካይነት እንደሆነ ገልፀዋል።  

ከ2008 እስከ 2009 ዓ.ም. በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም ካሪታስ ኢትዮጵያ ለአደጋ እና አደጋዎችን የመቋቋም አቅምን ለማሻሻል የመልሶ ማቋቋም እና የማገገሚያ ፕሮጀክትን ተግባራዊ አድርጋለች ፥ በዚህም መሰረት በውሃ ተደራሽነት ፣ በግል ጤና አጠባበቅና በአከባቢ ፅዳት አጠባበቅ ፣ በሰብል እና በከብት እርባታ ፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ላይ ሥራዎችን በመስራት ማሻሻያዎችን አድርጓል።

ካሪታስ ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የሴት ልጅ ግርዛት እና ሌሎች ወጣት ልጃገረዶችን እና ሴቶችን እድገት የሚያደናቅፉ ጎጂ ልማዶችን ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ዘመቻዎችን ታደርጋለች። እንደ አንድ ማሳያ ተግባራዊ ምሳሌ ውስጥ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ በኩል የሴት ልጅ ግርዛትን በመቃወም አንድ ሰነድ አዘጋጅቶ አቅርቧል።

የካሪታስ ኢትዮጵያ አጋር ድርጅቶች እነማን እንደሆኑ ለተጠየቁት ጥያቄ አቶ ሺፈራው ማሞ ሲመልሱ ፥ ካሪታስ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሃገራት የካሪታስ አባላት ፥ ከሰሜን አሜሪካ ፣ አውሮፓ ፣ ኢሲያ እና አውስትራሊያ ካሉ ፥ እዚህ ኢትዮጵያ ዉስጥ ጽ/ቤት ያላቸዉም ሆነ የሌላቸው አጋር አካላት ለምሳሌም ሲ አር ኤስ የተባለው የአሜሪካ የጳጳሳት ጉባኤ አካል የሆነው የሰብአዊ ዕርዳታ ድርጅት ከዋነኞቹ አጋር ድርጅቶቻችን አንዱ ነው በማለትም ይገልፃሉ። ከእነዚህም የእርዳታ ድርጅቶች የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፎችን ያገኘች ሲሆን ፥ በዚህ ዓመት ብቻ ከ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዓይነት እና የገንዘብ ድጋፍ አግኝታ በተለያዩ የሃገሪቷ ክፍሎች ላይ በርካታ ሥራዎችን እየሠራች እንደሆነ ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አበክረው እንደሚናገሩት “የበጎ አድራጎት ሥራ የሌላት ቤተ ክርስቲያን ህልዉና ዬላትም” ይላሉ ፤ ካሪታስ የቤተክርስቲያንን ተልእኮ ትካፈላለች ፥ ይህም ለማህበረሰቡ የታዘዘ አገልግሎት ነው።

በወንጌል እሴቶች እና በካቶሊክ ማህበራዊ ትምህርት ተመስርቶ ካሪታስ ለአደጋዎች ምላሽ ይሰጣል ፣ የሰው ልጅን ወሳኝ ሁለንተናዊ እድገት ያበረታታል ፥ ብሎም የድህነት እና የግጭት መንስኤዎችን ለማጥፋት ይታገላል።

ዘንድሮው በጣሊያን ዋና ከተማ በሆነችው ሮም ውስጥ ከግንቦት 3-8 2015 ዓ.ም. ‘አዲስ የወንድማማችነት መንገዶችን መገንባት’ በሚል መሪ ቃል የተካሄደው 22 ኛው አጠቃላይ የጋራ ጉባኤ ዋና ዓላማ አቶ በቀለ ሲገልፁ ፥ ‘አሳታፊ በሆነ መልኩ በጋራ ለመስራት እና በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለንን ተልእኮ በተሻለ ለመወጣት በተጠራንባቸው ሦስት አቅጣጫዎች ማለትም የወንድማማችነት ትብብር ፣ ሲኖዶሳዊነት እና ክልላዊነት ላይ ትኩረት አድርጎ ነው የተሰበሰበው’ ብለው ፥በተጨማሪም ኮንፌዴሬሽኑን ለማጠናከር እንዲሁም ድሆችን እና እጅግ በጣም የተጎዱትን በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል እንዲቻል ያለመ እንደሆነም ተነግሯል።

ከኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተወክለው ጉባኤውን ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ያቀኑት ክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሃፊ እና ክቡር አቶ በቀለ ሞገስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማህበራዊ ልማት ኮሚሽን ዳይሬክተር እና ምክትል ጠቅላይ ጸሃፊ መሆናቸዉንም አክለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያው ካሪታስ ከዚህ ጉባኤ ምን ይጠብቃል ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ ፥ ካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ ካሉት ዘርፈ ብዙ ንኡስ ኮሚቴዎች ውስጥ በአንዱ ካሪታስ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀመጫ አግኝታለች ፥ በመሆኑም ለሚቀጥሉት የሥራ ጊዜያት ኢትዮጵያን ወክላ እንድታገለግል ዕድል ይሰጣታል ፥ ይህም ቤተክርስቲያኒቷ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ አስተዋጽኦዋ እየጎላ እንዲመጣ ያግዛታል ብለው ፥ ሌላው ኢትዮጵያ ከዚህ ጉባኤ የምታገኘውን ነገር ሲያብራሩ ኢትዮጵያ በዚህን ሁለት እና ሶስት ዓመታት ከተፈጥሮዋዊው ችግሮች ባልተናነሰ እና ሊበልጥ በሚችል መልኩ ሰው ሰራሽ ችግሮች ተበራክተዋል ፤ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ደግሞ በርካታ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ እሙን ነው ፥ ይሄን ክፍተት ለመሙላት በዘንድሮው ዓመት የካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ አባል ድርጅቶች ለኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ ፥ ይህም ለሃገራችን ትልቅ ነገር ነው በማለት አብራርተዋል አቶ ሺፈራው።

የካሪታስ ኢትዮጵያ ዋና ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ ሲሆን ፥ 13 የሀገረ ስብከቱ አስተባባሪ ጽ/ቤቶች እና ንኡስ ጽ/ቤቶች በመላ አገሪቱ ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜም ከ3000 በላይ ሰዎች በካሪታስ ኢትዮጵያ ተቀጥረው እየሰሩ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

ካሪታስ ኢትዮጵያ የካሪታስ ኢንተርናሽናልስ እና የካሪታስ አፍሪካ አባል እንደመሆኗ መጠን ከዓለም አቀፉ የካሪታስ ኔትወርክ አባላት ፣ የካሪታስ ካልሆኑ የካቶሊክ ድርጅቶች ፣ ጳጳሳዊ ድርጅቶች ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች ፣ የአውሮፓ ህብረት እና በተመሳሳይ ከብዙ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየሰራች ትገኛለች።

ይህንን ዝግጅት በድምጽ ለማዳመጥ ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ

 

19 May 2023, 14:12