ፈልግ

በጃፓን ሂሮሺማ ከተማ የተሰበሰቡት የቡድን 7 አገራት መሪዎች በጃፓን ሂሮሺማ ከተማ የተሰበሰቡት የቡድን 7 አገራት መሪዎች  

የአፍሪካ ጳጳሳት የቡድን 7 አገራት መሪዎች ከባድ የዕዳ ጫናን እንዲሰርዙ ጠየቁ

በ23 የአፍሪካ አገራት የሚገኙ የካሪታስ ድርጅቶች ተወካይ ጳጳሳት፣ በጃፓን ሂሮሺማ ከተማ ለተሰበሰቡት በኢንዱስትሪ ለበለጸጉት የቡድን 7 አገራት መሪዎች ባቀረቡት አቤቱታቸው፣ መሪዎቹ አፍሪካ የምግብ እና የአየር ንብረት ለውጥ ቀውሶቿን እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን ድህነት ለመቅረፍ የሚያስችላትን ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወስዱ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅቶች ወይም ‘ካሪታስ’ የበላይ ሃላፊ ጳጳሳት፣ በጃፓን ሂሮሺማ ከተማ ዓመታዊ ስብሰባቸውን ላካሄዱት የቡድን 7 አገራት መሪዎች ባቀረቡት አቤቱታ፣ ‘ለመክፈል ከባድ’ የሆነውን የዕዳ ጫና መሰረዝን ጨምሮ ከድህነት ጋር የሚታገሉትን የአፍሪካ ሀገራት ለመደገፍ ደፋር እርምጃዎችን እንዲወስዱ፣ የዕርዳታ መጠንን እንዲጨምሩ እና ፍትሃዊ የንግድ ፖሊሲዎችን እንዲዘረጉ ጠይቀዋል።

ዓርብ ግንቦት 11/2015 ዓ. ም. ተጀምሮ ለሦስት ቀናት በተካሄደው ስብሰባ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የካናዳ፣ የጃፓን፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን እና የእንግሊዝ መሪዎች ተገኝተዋል። መሪዎቹ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ባካሄደችው ጥቃት፣ በኒውክሌር የጦር መሣሪያ መፍታት እና እቀባ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በልማት፣ በምግብ ዋስትና እና በዓለም ጤና ላይ ተወያይተዋል።

በአፍሪካ የምግብ ዋስትና እጦት ማደግ

ከመሪዎቹ ስብሰባ ቀደም ብሎ፣ የ23 የአፍሪካ አገራት የ ‘ካሪታስ’ ድርጅቶች ተወካይ ጳጳሳት፣ አፍሪካን በአሁኑ ወቅት እያጋጠሟት ያሉ ዘርፈ ብዙ ቀውሶችን ለመቅረፍ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ፣ በኢንዱስትሪ ለበለጸጉት የቡድን 7 አገራት መሪዎችን ተማጽኗቸውን አቅርበዋል። ጳጳሳቱ በመግለጫቸው ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስ በኋላ ተባብሶ ለቀጠለው የአፍሪካ ድህነት ያላቸውን ጥልቅ ስጋት ገልጸው፣ እየጨመረ ያለው የምግብ ዋስትና እጦት በብዙ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ግጭቶችን እና ማኅበራዊ አለመግባባቶችን እያስከተለ እና እያባባሰው እንደሚገኝ፣ አስተዳደርን የበለጠ ደካማ እንዲሆን ማድረጉንም ገልጸዋል። “ባለፈው ዓመት ከ300 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የምግብ ዋስትና እጦት አጋጥሟቸው ነበር” ያለው መግለጫው፣ “ይህም በብዙ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ግጭቶችን እና ማኅበራዊ ውጥረትን በማባባስ አስተዳደርን ይበልጥ ደካማ እንዲሆን አድርጎታል” ብሏል።

ለመክፈል የሚዳግት የዕዳ ጫና

ጳጳሳቱ “መክፈል የማይቻል” ያሉትን የዕዳ ጫና ማቃለልን ከሰው ልጅ የልማት ፍላጎቶች ጋር እንደገና በማገናኘት መመልከት እንደሚገባ እና የዕዳ መቆምን ማረጋገጥ፣ ሁሉም አበዳሪ አገራት ዕዳን በመሰረዝ ችግር ውስጥ ለሚገኙ  ታዳጊ አገራት በሙሉ ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በመግለጫቸው አሳስበዋል። ለልማት የሚውሉ አዳዲስ እና ተመጣጣኝ የፋይናንስ ምንጮች ካልተመቻቹ በከፍተኛ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ተግዳሮቶች ውስጥ የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ወደ አስከፊ የዕዳ አዙሪት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ጳጳሳቱ አስጠንቅቀዋል።

በሥነ-ምግባር የታገዘ የፋይናንስ ማሻሻያ ያስፈልጋል

እንደ አፍሪካ ጳጳሳት እምነት፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት ልዩ መብቶችን እንደገና በማጤን እንደ ፋይናንስ መሣሪያ የበለጸጉ አገራት ለአፍሪካ አህጉር ለመስጠት ካስቀመጡት የሃብት ክምችት ጋር በማደግ ላይ የሚገኙ ደሃ አገራትን እንደገና ማገናኘት መሆኑ ተመልክቷል። “የገንዘብ ድጋፍን የማግኘት ልዩ መብት” የሚለው ደንብ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ፈንድ፣ 180 አባል አገራት ከኦፊሴላዊ መጠባበቂያ ክምችት ድጋፍን እንዲያገኙ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1969 ዓ. ም. የደነገገው መብት ነው።

በኢንዱስትሪ ከበለጸጉት የቡድን 7 አገራት ከተገኘው ዕርዳታ በተጨማሪ “የገንዘብ ድጋፍ የማግኘት መብት” በሚሰጠው የ650 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ፣ የዕዳ ጫና ሳይጨምር ወረርሽኙን ለመቅረፍ ትልቅ ዕርምጃ መሆኑን ጳጳሳቱ ገልጸው፣ በኢንዱስትሪ ከበለጸጉ አገራት በኩል የሚቀርብ ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበው፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክትን በመጥቀስ “ሥነ-ምግባርን የተከተለ የፋይናንስ ማሻሻያ እና ሁሉንም ሰው የሚጠቅሙ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

"ዘርፈ ብዙ የልማት ባንኮች ሰብዓዊ ዕድገትን ለማምጣት እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚያጋጥሙ ቀውሶችን ለማሸነፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦን እንደሚያደርጉ፣ በተለይም በችግር ጊዜ አበዳሪዎች በራቸውን ሲዘጉ ጊዜያዊ ተግዳሮቶችን በብቃት ለመወጣት እና በሚያስፈልገው መጠን ለመሥራት ከአባላት ከፍተኛ የገንዘብ መዋጮን በመቀበል የካፒታል አጠቃቀምን የሚገዙ ፖሊሲዎችን እና ሕጎችን ማውጣት እንደሚያስፈልግ ጳጳሳቱ በመግለጫቸው አሳስበዋል።

የአፍሪካን ተስፋ ማደስ

"የአፍሪካን እና የወደፊት ትውልዶቿ ተስፋን ማደስ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይጠይቃል" ያሉት ብጹዓን ጳጳሳቱ፣ “በጋራ በመሥራት አፍሪካ በርካታ ችግሮቿን ለማሸነፍ እና ለሁሉም ሰው ብሩህ የወደፊት ተስፋን ለመገንባት የሚያስፈልጋትን ዕርዳታ እንደምታገኝ ያላቸውን እምነት በማረጋገት ጳጳሳቱ መግለጫቸውን ደምድመዋል።

22 May 2023, 14:14