ፈልግ

ኒቆዲሞስ እና ኢየሱስ ኒቆዲሞስ እና ኢየሱስ  

የመጋቢት 24/2015 ዓ.ም ዘኒቆዲሞስ እለተ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.     ሮሜ 7፡1-18

2.     1 ዮሐ 4፡ 18-21

3.     ሐዋ ሥራ 5፡ 34-42

4.     ዮሐ 3፡1-11

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ኒቆዲሞስን አስተማረ

ከፈሪሳውያን ወገን፣ ከአይሁድ አለቆች አንዱ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ ሰው ነበረ፤ በሌሊትም ወደ ኢየሱስ መጥቶ፣ “ረቢ፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ ሰው በቀር አንተ የምታደርጋቸውን ታምራዊ ምልክቶች ማንም ሊያደርግ ስለማይችል፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣህ መምህር እንደሆንህ እናውቃለን” አለው።

ኢየሱስም መልሶ፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” አለው። ኒቆዲሞስም፣ “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ እንዲወለድ ተመልሶ ወደ እናቱ ማሕፀንስ ሊገባ ይችላልን?” አለው።

ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደም መንፈስ ነው። ‘ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ’ ስላልሁህ አትገረም፤ ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደ መጣ፣ ወዴት እንደሚሄድም አታውቅም፤ ከመንፈስም የተወለደ ሁሉ እንደዚሁ ነው።” ኒቆዲሞስም፣ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀው።ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ሳለ እነዚህን ነገሮች አታውቅምን? እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉም።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

 

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘኒቆዲሞስ የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን ። በዚህም ሰንበት የእግዚአብሔር ሕግ ትክክለኛ መሆኑንና በእርሱም ሕግ የምንመራ ከሆነ መልካሙንና ክፉውን በቀላሉ ለመለየት ብሎም በትክክለኛ መሥመር ለመመላለስ እንደምንችል ይነግረናል።

“አቤቱ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው፣ ለዘለዓለም ለእኔ  ነውና ትዕዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ፣ ከትዕዛዝህ የተነሳ አስተዋልሁ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ፣ ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው” (መዝ. 119፡97) ይላል። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚነግረን አይሁዳውያን በእግዚአብሔር ዘንድ ጻድቅ ተብሎ ለመጠራት እነዚህን በቁጥራቸው እጅግ በጣም የበዙትን ምን አልባትም ከ 1500 በላይ የሆኑትን ሕግጋት ቃል በቃል ለመፈፀም ይተጉ ነበር። አብዛኞቹ አይሁዳውያን ሕግን ቃል በቃል ለመፈፀም ይትጉ እንጂ በሕጉ ውስጥ ባሉት መንፈሳዊ እሴቶች ራሳቸውን ለማሳደግ ያን ያህል አይጨነቁም ነበር።

ሕግ በማንኛውም ሰው ላይ ስልጣን የሚኖረው በሕይወት ሲኖር ብቻ ነው፤ የሞተ ሰው ሕግን የመፈፀም ግዴታ የለበትም ስለዚህ እኛም ከክርስቶስ ጋር አብረን ሞተናልና ልክ እንደ አይሁዳውያኑ ለሕግ ሳይሆን ለኃጢአት በመሞት  ከክርስቶስ ትንሳኤ ጋር አብረን እንነሳለን። በአይሁዳውያኑ ሕግ መሰረት ሚስት ከባሏ በሞት ምክንያት ከተለየች ሌላ ለማግባት በሕግ አንደማትያዝ ሁሉ እኛም በፊት ለነበረን ኃጢአት ከሞትን በአዲስ መልክ ከጌታችን እየሱስ ጋር አዲስ ውህደት ለመፍጠር የሚይዘን ነገር አይኖርም።

“እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሳ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀቱ ከእርሱ ጋር ተቀበርን፣ ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” (ሮሜ 6፡4-5) ይላል ። ሰው ከኃጢአት ጋር ሲቆራኝ ከክርስቶስ ጋር ይፋታል ውጤቱም ለሞት ፍሬ ማፍራት ብቻ ነው በትቃራኒው ደግሞ ከኃጢአት ጋር ተፋቶ ከክርስቶስ ጋር ሲቆራኝ ውጤቱ ለሕይወት ፍሬ ማፍራት ነው፣ ይህንንም በመድረጉ በምድራዊም ሆነ በሰማያዊ ቤቱ ሰላምን ደስታን ፍቅርን ይጎናጸፋል።

“ሰዎች የሚፈሩት ኃጢአት መሥራትን ሳይሆን ቅጣትን ነው። እግዚአብሔር ግን ለእኛ ለልጆቹ ካለው ፍቅር የተነሳ በጌታችን እየሱስ ከርስቶስ በኩል ከኃጢአታችን ሁሉ ነፃ አደረገን በጌታችን እየሱስ ከርስቶስ በኩል ራሱን ለእኛ ለልጆቹ በሙላት ገለፀልን ስለዚህ እኛ በውስጣችን ያለውን ፍርሃት ሁሉ በማስወገድ በፍጹም ፍቅር ልንቀርበው ይገባል” (1 ዮሐ. 4፡18-21)። የእግዚአብሔርን ፍርድ በመፍራት ወደ እርሱ የምንቀርብ ከሆነ ፍቅራችን ፍጹም ፍቅር ሊሆን አይችልም። “የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው” (ምሳሌ 1፡7) ይላል። ይህ ማለት ግን የአክብሮት ፍርሃት የፍቅር ፍርሃት እንጂ የቅጣት ፍርሃት አይደለም።

እግዚአብሔር ፍጹም ፍቅር ስለሆነ በፍቅር ብቻ ልንቀርበው ይገባል እርሱንም ማፍቀራችንን በዙሪያችን የሚገኙትን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ሁሉ በማፍቀር ልናስመሰክር ይገባል። ምክንያቱም እግዚአብሔርን ማፍቀርና ወንድም እህቶቻችንን ማፍቀር የማይነጣጠሉ ሁልጊዜም አብረው የሚሄዱ እውነታዎች ናቸው። በአንድ መልኩ ስንመለከተው እግዚአብሔር መንፈስ ሰለሆነ አርሱን መውደድና ማፍቀር ሰውን ከመውደድና ከማፍቀር ትንሽ ቀለል እንደሚል ልንገምት እንችል ይሆናል ምክንያቱም በምናደርገው ክፋትና ኃጢአት እግዚአብሔር ከቁጣ ይልቅ ምክርን ከቅጣት ይልቅ ምህረትን ከመራቅ ይልቅ ቅርብነቱን ስለሚያሳየን ።

በአጠገባችን ያሉ ሰዎች ግን በተለያየ መንገድ ስለሚያበሳጩን ስለሚያሳዝኑን ስለሚያናድዱን ለስራነው ክፋት ወዲያውኑ አፀፋውን ስለሚመልሱልን በሙሉ ልብ ለማፍቀር ይከብዳል  ነገር ግን ልብ ልንል የሚገባው ነገር  1ኛ ዮሐንስ 2፡4 ላይ አንደተፃፈው በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች ሳንወድ እግዚአብሔርን እንወዳለን ብንል ሐሰተኞች መሆናችንን ነው ለዚህ ነው እግዚአብሔርንና ሰውን መወደድ የማይነጣጠሉ ሁልጊዜም እጅና ጓንት በመሆን የሚጓዙ እውነታዎች ናቸው የምንለው።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን ሰዎች ሲሰድቡት ሲገርፉት ሲያሰቃዩት በመጨረሻም በመስቀል ላይ ሲሰቅሉት እርሱ ግን ስለእነሱ ይጸልይ ነበር አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁም እና ይቅር በላቸው በማለት ከእግዚአብሔር ምሕረትን እንዲያገኙ ይለምንላቸው ነበር እንግዲህ እኛም መከተል ያለብን መንገድ ይህን ነው የቱንም ያህል ወንድሞቻችንንና እህቶቻችን ቢበድሉን ቢያሰቃዩን ስለ እነሱ ከእግዚአብሔር ምሕረትን መለመን ያስፈልጋል የበለጠ ወደእነሱ በመቅረብ ልናግዛቸው ይገባል እግዚአብሔር ወደ ልቦናቸው እንዲመልሳቸው ማስተዋልን እንዲጨምርላቸው ወደ እርሱ መጸለይ ያስፈልጋል ይህ ነው እግዚአብሔርን በፍጹም ነፍስ  በፍጹም ኃይል በፍጹም ልብ ባልጀራንም ድግሞ እንድ እራስ አድርጎ መውደድ ማለት።

ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሯልና በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ የእግዚአብሔር የሆነ ነገር አለ እንግዲህ በዓይናችን የሚታየውን የእግዚአብሔርን ሽራፊ በውስጡ የያዘውን ሰው ሳንወድ እንዴት አድርገን በዓይናችን ያላየነውን እግዚአብሔርን እንወዳለን ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን? ስለዚህ እግዚአብሔርንም ሆነ ሰውን መውደድ እንዲሁ ቀላል ነገር እንዳልሆነና ሁል ጊዜም ውስጣዊ ዝግጅትና ጥልቅ ማስተዋል እንደሚያስፈልግ ልንረዳ ይገባል።

በዚህ በዛሬው የዮሐንስ ወንጌል 3፡1-11 ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ከሚባል የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሸንጎ አባልና የአይሁድ አለቃ ጋር ስላደረገው ውይይት እንመለከታለን። ኒቆዲሞስ የአይሁድን ሥርዓት ጠንቅቆ የሚያውቅና የተማረ ሰው ነበረ። ነገር ግን በአይሁድ ሸንጎ ዘንድ እንደ ነብይ ከማይቆጠረውና  እንደ ነውጠኛ ከሚታየው ከእየሱስ ዘንድ በማታ በመሄድ እየሱስን ያነጋግረው ነበረ። ይህ ኒቆዲሞስ ውስጠ ቀናና በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ነቢይነት ያምን የነበረ በዚህም ምክንያት ማታ ማታ ወደ እርሱ በመሄድ ከእየሱስ ጋር ይወያይ የነበረ መልካም ሰው ነው።

አይሁዳውያኑ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ላይ ሲነሱ ሲቃወሙ ኒቆዲሞስ ግን እየሱስን በተቻለው አቅም ይከላከልለት ነበር ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን  “ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምን እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን አላቸው? እንርሱም መለሱና አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንደማይነሳ መርምረህ እይ አሉት” (ዮሐ. 7፡50-52) ይነበባል።።

ይህ መልካም ሰው ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የነበረው አመለካከት በዚህ አልተቋጨም የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የቅርብ ሰዎች የነበሩት ሐዋርያት ከእርሱ ጋር አብረው የበሉት ከእርሱ ጋር አብረው የጠጡት ከእርሱ ጋር አብረው ከቦታ ቦታ የተዘዋወሩት ብዙ ተዓምር ሲያደርግ በዓይናቸው የተመልከቱት በዛ በጭንቅ ሰዓት ሲሸሹት ይህ ኒቆዲሞስ ግን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከሞተ በኃላ  ከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ በመምጣት እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከገነዙት ከሽቶ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከከፈኑት በቅርቡ በነበረም የአትክልት ሥፍራ  አዲስ መቃብር ውስጥ ካኖሩት መልካም ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው (ዮሐንስ  19፡39)።

ይህ ሰው በዚህ ድርጊቱ ከሐዋርያቱ የበለጠ ለጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ያለውን ታማኝነት አስመስክሯል። ይህ እንግዲህ ለእያንዳዳችን የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንም እንኳን ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር ሕብረት ቢኖረንም ለእርሱ ያለንን ታማኝነት በይፋና ጉልህ በሆነ መልኩ ማንንም ሳንፈራ ማስቀመጥ ይገባናል።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከኒቆዲሞስ ጋር በነበረው ውይይት ያስተማረው አንድ ጠልቅና መሠረታዊ  ነገር አለ ይኸውም “እውነት እውነት እልሃለው ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ሊገባ አይችልም ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው” (ዮሐ 7፡5-6)።

እውነት ነው ሰው ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ሊገባ የሚችለው ሕግን በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሲታደስ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አምኖ በዕምነቱም አዲስ ሕይወት መላበስ ሲችል ብቻ ነው። “ነገር ግን ሰው በእየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አወቅን ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ እየሱስ አምነናል” (ገላ. 2፡16) ይላል። እንግዲህ ዛሬም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እያንዳዳችን በአዲስ መልክ ከውኃና ከመንፈስ እንድንወለድ ይፈልጋል ይኸውም ኃጢአታችንን በምስጢረ ንስሃ አማካኝነት አንድናጥብና ለኃጢአት እንድንሞት ብሎም በእግዚአብሄር መንፈስ እንድንሞላ ይህንንም አድርገን የዘለዓለማዊ  ሕይወት ተቋዳሾች አንድንሆን ይፈልጋል።

ሰው በጥምቀትና በምስጢረ ንስሃ አማካኝነት ኃጢአቱን ካጠበ መላ እሱነቱ በመንፈስ እንደሚሞላ ግልጽ ነው ይህ መንፈስ ነው ታዲያ እንደ እግዚአብሄር ቃል እንዲመላለስ የሚያደርገን የስይጣንን ዕቅድ በሙላት እንድንዋጋ ብርታት የሚሆነን ዘወትር ከሚስጢራት ጋር የሚያቆራኘን። ስለዚህ ሰው ሁል ጊዜ በመንፈስና በሥጋ መታደስ ይገባዋል ይህንን ካደረገ ብቻ ምድራዊ ሕይወቱ የተስተካከለና የታረመ እንዲሁም የተቀደሰ ይሆናል የመንግሥተ ሰማይም እጩ ይሆናል።

እንግዲህ እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ ውስጥ እየተመላለስን መኖር እንድንችልና የእርሱ እውነተኛ ደቀማዛሙርት ለመሆን እንድንችል የዘውትር ጠባቂያችንና አማላጃችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሄር ፊት ትቁምልን በሥጋና በመንፈስ ለመታደስ እንድንችል በረከቱን ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ታሰጠን።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን 

 

01 April 2023, 09:05