ፈልግ

2021.12.26 Famiglia

በጋብቻ ውስጥ የፍቅር አስፈላጊነት ክፍል ሁለት

መውደድ ጨዋና ለሌሎች አሳቢ መሆንም ነው፡፡ ፍቅር ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፣ወይም ብልግና የለበትም፣ ጨካኝ አይደለም፡፡ ድርጊቶቹ፣ ቃላቱና እንቅስቃሴዎቹ ደስ የሚያሰኙ ናቸው፤ ሻካራ ወይም ግትር አይደሉም፡፡ ፍቅር ሌሎችን ማሰቃየትን አጥብቆ ይጠላል፡፡ ይሉኝታ አንድን ሰው ‹‹አእምሮውንና ስሜቶቹን ማዳበርን፣ እንዲሁም እንዴት መስማት፣ መናገርና አንዳንዴም ዝም ማለት እንዳለበት መማርን የሚጠይቅ የስሜትና አድልዎ የሌለበት ትምህርት ቤት ነው›› (ኦክታቪዮ ፓዝ፣ ላ ላማ ዶብሌ፣ ባርሴሎና፣ 1993፣ 35)።

ክርስቲያን ሰው በፈቃደኝነት የሚቀበለው ወይም የሚተወው ነገር አይደለም፡፡ ፍቅር መሠረታዊ ነገር እንደ መሆኑ መጠን ‹‹ማንኛውም ሰው በዙሪያው ካሉት ጋር ተስማምቶ የመኖር ግዴታ አለበት››(ቶማስ አኳይናስ፣ ሱማ ቴዎሎጊየ 2-2፣ ጥ. 114፣ አንቀጽ 2፣ 1):: በየቀኑ ‹‹ አንድ ሰው በሕይወታችን ውስጥ ቀድሞውኑ ሚና ቢኖረውም እንኳ፣ ወደ ሌላው ሰው ሕይወት ውስጥ መግባት፣ መተማመንንና መከባበርን የሚያድስ ስሜትንና መቆጠብን ይጠይቃል፡፡ በእርግጥ፣ የፍቅር ጥልቀቱ ሲጨምር፣ የሌላውን ሰው ነጻነት የማክበርና ሌላው ሰው የልቡን በር እስኪከፍት ድረስ የመጠበቅ ችሎታ በይበልጥ ማዳበርን ይጠይቃል›› (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ፣ (እ.አ.አ. ግንቦት 13፣2005)፡ ለኦሰርቫቶሬ ሮማኖ፣ ግንቦት 14፣2015፣ ገጽ. 8)።

ከሌሎች ጋር በሐቅ ለመገናኘት ዝግጁ ለመሆን ‹‹ በጎ አስተሳሰብ›› አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም የራስን ችላ ብሎ የሌሎች ሰዎችን ድክመት ከመጠቆም አሉታዊ አስተሳሰብ ጋር አይጣጣምም፡፡ በጎ አስተሳሰብ ከራሳችን ውስንነቶች ባሻገር እንድንመለከትና ትዕግሥተኞችና ልዩነቶች ቢኖሩን እንኳ ከሌሎች ጋር እንድንተባበር ይረዳናል፡፡ በጎ አስተሳሰብ መስተጋብርን ይመሠርታል፣ ግንኙነቶችን ያዳብራል፣ አዳዲስ የውህደት መረቦችን ይዘረጋል፣ ጥብቅ ማኅበራዊ ትስስርን ይፈጥራል፡፡ በዚህ ዐይነት ይበልጥ እየጠነከረ ይሄዳል፤ ምክንያቱም፣ የባለቤትነት ስሜት ሳይኖር ለሌሎች  ያለንን ቁርጠኝነት መቀጠል አንችልም፤ የራሳችንን ምቾት ብቻ በመሻት ላይ የምናተኩር ከሆነ የጋራ ሕይወት የማይቻል ይሆናል፡፡ ጸረ ኅብረተሰብ አkም ያላቸው ሰዎች ሌሎች ሰዎች ያሉት የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ለማርካት ነው ብለው ያስባሉ፡፡ በመሆኑም፣ ለፍቅራዊ ጨዋነትና ለመገለጫዎቹ ክፍት ቦታ አይኖርም፡፡ የሚወዱ ሰዎች የሚያስደስት፣ የሚያጸና፣ የሚያጽናናና የሚያበረታታ ቃል መናገር ይችላሉ፡፡    ‹‹ አይዞህ፣ ልጄ›› (ማቴ. 9፡2)፣ ‹‹ እምነትሽ ታላቅ ነው›› (ማቴ. 15፡ 28)፤‹‹ ተነሺ ቁሚ›› (ማር. 5፡ 41)፤ ‹‹ በሰላም ሂጂ›› (ሉቃ. 7፡ 50)፤ ‹‹ አይዞአችሁ፣ አትፍሩ›› (ማቴ. 14፡ 27) የሚሉ እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ራሱ የተናገራቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሰውን የሚያዋርዱ፣ የሚያሳዝኑ፣ የሚያስቆጡ ወይም የሚንቁ ቃላት አይደሉም፡፡ በቤተሰቦቻችን ውስጥ፣ እርስ በርስ ስንነጋገር፣ ጨዋ ኢየሱስን መምሰልን መማር አለብን፡፡

ፍቅር ለጋስ ነው

ደጋግመን እንደተናገርነው፣ ሌላ ሰውን ለመውደድ በቅድሚያ ራሳችንን መውደድ ይኖርብናል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በጳውሎስ የፍቅር መዝሙር ላይ ፍቅር ‹‹የራስን ጥቅም ብቻ አይሻም››፣ ‹‹የራሱንም አይፈልግም›› ይላል፡፡ ይኸው ሐሳብ በሌላ ጽሑፍ ላይ ‹‹ እያንዳንዳችሁ ሌሎችንም የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ›› (ፊልጵ. 2፡ 4) ተብሎ ተገልጾአል፡፡ ሌሎችን በልግስና ማገልገል ራሳችንን ከመውደድ እንደሚበልጥ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ያደርግልናል፡፡ ራሳችንን መውደድ አስፈላጊ የሚሆነው ሌሎችን ለመውደድ ሥነ ልቦናዊ መነሻ ሲሆን ነው፡፡ ‹‹ሰውነቱን የሚነፍግ ሰው ለማን ይለግስ ዘንድ አለው? ሰውነቱን ከሚነፍግ ሰው የሚከፋ የለም›› (ሲራክ 14፡5-6)፡፡  ቅዱስ ቶማስ አኳይናስ ‹‹ ከመወደድ መውደድ ተገቢ ነው›› (ቶማስ አኳይናስ፣ ሱማ ቴዎሎጊየ ፣ 2-2፣ ጥ. 27፣ አንቀጽ 1፣ 2)፣ በእርግጥ   ‹‹ከሁሉ አስበልጠው የሚወዱ እናቶች፣ ከመወደድ በላይ ለመውደድ ይሻሉ›› ይላል(ከላይ የተጠቀሰው፣ ጥ. 27፣ አንቀጽ 1)። ስለ ሆነም፣ ፍቅር ከፍትሕ ጥያቄ የላቀና ከዚያም የዘለለ ‹‹መልሶ ለመቀበል ተስፋ የማያደርግ›› (ሉቃ. 6፡ 35) ነው፤ ከሁሉ የሚበልጠው ፍቅር ደግሞ ‹‹የራስን ሕይወት ለሌላ አሳልፎ እስከ መስጠት የሚያደርስ ነው (ንጽ. ዮሐ. 15፡ 13)፡፡ ለመሆኑ፣ በነጻነትና በሙላት ራሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ የሚያደርግ ይህን የመሰለ ቸርነት የሚቻል ነገር ነው? አዎን፣ ምክንያቱም ወንጌል ‹‹በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ›› (ማቴ. 10፡8) ይላልና፡፡  

ፍቅር አይበሳጭም ወይም ቅር አይሰኝም

የጳውሎስ የመጀመሪያው የፍቅር መዝሙር ስለ ሌሎች ሰዎች ድክመትና ጥፋት ፈጥኖ በማመናጨቅ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ትዕግሥት እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡ ቀጥሎ የተናገረው ቃል ደግሞ በውጫዊ ምክንያት የሚመጣውን ውስጣዊ ንዴት የሚመለከት ነው፡፡ ሌሎች ሰዎችን በተመለከተ ፣ ችግር  ወይም ሥጋት ፈጣሪ ስለሆኑ ከእነርሱ መራቅ ይገባል የምንለውንና በውስጣችን ያለውን ኃይለኛ ስሜትና ሥውር ቁጣ  የሚመለከት ነው፡፡ ይህን የመሰለ ውስጣዊ ጥላቻ ማሳደር ለማንም አይበጅም፡፡ መቀያየምንና መገለልን ብቻ ነው የሚፈጥረው፡፡ ንዴት ጤናማ የሚሆነው፣ ለትልቅ በደል ምላሽ መስጠት ሲያስፈልግ ብቻ ነው፡፡ ለሌሎች ሰዎች ወዳለን አመለካከት ሰርጾ ሲገባ ግን ጎጂ ነው፡፡

ወንጌል በዐይናችን ውስጥ ያለውን ግንድ እንድንመለከት ይነግረናል (ንጽ. ማቴ. 7፡5)፡፡ ክርስቲያኖች ለቁጣ ትኩረት እንዳይሰጡ የሚናገረውንና ‹‹በክፉ አትሸነፍ›› (ሮሜ. 12፡ 21) የሚለውን  የእግዚአብሔርን ብርቱ ተግሳጽ ችላ ማለት የለባቸውም፡፡ ‹‹ በጎ ነገር ከማድረግ አንታክት›› (ገላ. 6፡ 9)፡፡ ድንገት ቱግ የሚል የጥላቻ ስሜት ማሳደር አንድ ነገር ሲሆን፣ በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰድ ማድረግ ግን ሌላ ነው፤ ‹‹ተቆጡ፣ ነገር ግን ኃጢአት አትሥሩ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ›› (ኤፌ. 4፡ 26)፡፡ እንዲያውም የኔ ምክር በቤተሰብ ውስጥ ዕርቅ ሳታወርዱ አንድ ቀን እንኳ ከቶ አታሳልፉ የሚል ነው፡፡ ‹‹ዕርቅ እንዴት ማውረድ እችላለሁ? በጉልበቴ ተንበርክኬ ነውን? አይደለም! ትንሽ እንቅስቃሴ በማሳየት፣ አንድ የተለየ ትንሽ ነገር በማድረግ፣ በቤተሰብ ውስጥ ስምምነትን ማደስ ይቻላል፡፡ ከትንሽ ማሻሸት  ውጭ ሌላ ቃላት ላያስፈልጉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን፣ በቤተሰባችሁ ውስጥ ሰላም ሳይወርድ አንድም ቀን አታሳልፉ›› (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ( እ.አ.አ. ግንቦት 13፣ 2015)፡ ለኦሰርቫቶሬ ሮማኖ) ስንናደድ የመጀመሪያው ምላሻችን ልባዊ ቡራኬ፣ ያንን ሰው እንዲባርከው፣ ነጻ እንዲያወጣውና እንዲፈውሰው እግዚአብሔርን መለመን  መሆን አለበት፡፡ ‹‹በዚህ ፈንታ ባርኩ፣ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው›› (1 ጴጥ. 3፡ 9)፡፡ ክፋትን መዋጋት ካለብን እንዋጋ፤ ነገር ግን ለቤት ውስጥ ብጥብጥ ‹‹እምቢ›› እንበል፡፡

ፍቅር ይቅር ይላል

በልባችን ውስጥ ክፉ ፈቃድ ሥር እንዲሰድ ካደረግን፣ ወደ ጥልቅ ቅሬታ ሊወስደን ይችላል፡፡ ፍቅር ‹‹በደልን አይቆጥርም››፤ ‹‹ አይናደድም››፡፡ የንዴት ተቃራኒ የሌሎች ሰዎችን ድክመቶች ለመረዳትና እነርሱንም ይቅር ለማለት በሚሻ አዎንታዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ይቅርታ ነው፡፡ ኢየሱስ ‹‹ አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› (ሉቃ. 23፡ 34) አለ፡፡ እኛ ግን ትልልቅ ክፋትን እያሰብን፣ ማናቸውንም ክፋት እያሰላሰልንና ስሕተቶችን ይበልጥ እየፈለግን ስንሄድ፣ ንዴት እየጨመረና ሥር እየሰደደ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ፣ በባል ወይም በሚስት በኩል የሚፈጸም ማንኛውም ስሕተት ወይም ጥፋት የፍቅር ግንኙነትንና የቤተሰብ መረጋጋትን ሊጎዳው ይችላል፡፡ ሁሉም ችግር እኩል መስሎ ሲታየን አንድ ከበድ ያለ ችግር አለ ማለት ነው፡፡   በዚህ ዐይነት፣ በሌሎች ድክመት ላይ አላስፈላጊ ጭካኔ ወደማሳየት ሥጋት ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ መብቶቻችን እንዲከበሩ ያለን ተገቢ ምኞት ክብራችንን በአግባቡ በማስጠበቅ ፈንታ ወደ ቂም በቀል ጥማት ይለወጣል፡፡

ስንበደል ወይም ችላ ስንባል፣ ይቅር ማለት ይቻላል፣ አስፈላጊም ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ማድረግ ቀላል ነው የሚል ማንም ሰው የለም፡፡ በእውነቱ ‹‹ የቤተሰብ አንድነት የሚጠበቀውና የሚጠራው በታላቅ የመሥዋዕትነት መንፈስ ነው፡፡ በመሠረቱ፣ ለመረዳት፣ ለመታገስ፣ ይቅር ለማለትና ዕርቅ ለማውረድ የእያንዳንዱንና የሁሉንም ሰው ዝግጁነትና ለጋስ ግልጽነት ይጠይቃል፡፡ ራስን ብቻ መውደድ፣ አለመስማማት፣ ውጥረትና ግጭት የራሱን ኅብረት በኃይል እንደሚያጠቃና አልፎ አልፎም ክፉኛ እንደሚያቆስል፣ በዚህም ሳቢያ በቤተሰብ ውስጥ በርካታና የተለያዩ የክፍፍል ዐይነቶች እንደሚፈጠሩ የማያውቅ ቤተሰብ የለም›› (ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ፋሚሊያሪስ ኮንሶርሲዮ የተሰኘ ሐዋርያዊ ማበረታቻ)።

ዛሬ ሌሎች ሰዎችን ይቅር ማለት መቻል ራሳችንን የመረዳትና ይቅር የማለት አስደሳች ልምድ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ብዙውን ጊዜ  ስሕተታችን ወይም ከምንወዳቸው ሰዎች የሚደርስብን ነቀፌታ በራስ መተማመናችንን ሊያሳጣን ይችላል፡፡ በመሆኑም ከሌሎች ሰዎች እንርቃለን፣ መወደድን ልንጠላና የእርስ በርሳችንን ግንኙነቶች ልንፈራ እንችላለን፡፡ ሌሎችን መውቀስ ያላግባብ ያስደስተናል፡፡ ስለዚህ፣ ባለፈው ታሪካችን ላይ መጸለይን፣ ራሳችንን መቀበልን፣ ከነድክመታችን መኖርን፣ እንዲሁም ለሌሎች ተመሳሳይ አስተሳሰብ ይኖረን ዘንድ ራሳችንንም ይቅር ማለትን መማር ያስፈልገናል፡፡   

ይህ ሁሉ የሚያሳየው፣ እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር ይቅር መባላችንን፣ በራሳችን በጎ ምግባር ሳይሆን በጸጋው መጽደቃችንን ነው፡፡ ከራሳችን ጥረት በላይ ቅድሚያ የሚሰጠውን፣ ሁልጊዜ በሮችን የሚከፍተውን፣ የሚያሳድገውንና የሚያበረታታውን ፍቅር አውቀናል፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር በነጻ የተሰጠ መሆኑን፣ የአብ ፍቅር በገንዘብ ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንደማይችል  አምነን ከተቀበልን፣ እኛም፣ ቢበድሉን እንኳ፣ ለሌሎች ሰዎች ገደብ የሌለው ፍቅር ልናሳይና ይቅር ልንላቸው እንችላለን፡፡ ያለበለዚያ፣ የቤተሰብ ሕይወታችን ከእንግዲህ የመግባባት፣ የመደጋገፍና የመጽናናት ሥፍራ መሆኑ ቀርቶ የማያkርጥ ውጥረትና እርስ በርስ የመነቃቀፍ ቦታ ይሆናል፡፡

ምንጭ፡ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 99-114 ላይ የተወሰደመሆኑን እንገልጻለን።

አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

 

 

 

17 March 2023, 12:47