ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ (በስተ ግራ) እና ክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ (በስተ ቀኝ) ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ (በስተ ግራ) እና ክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ (በስተ ቀኝ) 

በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ እና ልማት ኮሚሽን ዓመታዊ ጉባኤ ተካሄደ

በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ እና ልማት ኮሚሽን ዓመታዊ ጉባኤ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ. ም. ተካሄደ። በቤተ ክርስቲያኒቱ ጠቅላይ ጽ/ቤት የተካሄደውን ጉባኤ በጸሎት እና በቡራኬ የከፈቱት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስትያን የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ናቸው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ - አዲስ አበባ

በጉባኤው ላይ ክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ ፥ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ጸሃፊ የሚመራ 16 የቦርድ አባላት እና ከ 13 ቱም የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሃገረ ስብከቶች የመጡ የፕሮጀክት ሃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተዋል። አጠቃላይ የጉባኤው አጀንዳ ለጉባኤተኞቹ ቀርቦ አጀንዳዉን በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ጉባኤው ተጀምሯል። የአንድ ቀን ጉባኤው እ. አ. አ. የ 2022 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሥራ አፈጻፀም ቀርቦ ውይይቶች የሚደረጉበት ሲሆን፣ በተጨማሪም የ 2023 የሥራ ዓመት ዕቅድ እና ትግበራ ላይ ተመካክሮ ዉሳኔ አስተላልፏል።

በአቶ በቀለ ሞገስ ፥ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ እና ልማት ኮሚሽን ሊቀ መንበር የቀረበው የ2022 ዓመት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን 2.6 ቢሊዮን ብር በመመደብ ፥ ሁሉንም የሃገሪቱ ክፍሎች ሊባል በሚችል ሁኔታ ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ አጠቃላይ 530 ወረዳዎች ውስጥ 434 ወረዳዎችን ተደራሽ በማድረግ ፥ 8.9 ሚሊዮን ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፥ 164 የተለያዩ ፕሮጄክቶችን ለማከናወን ታቅዶ ፥ በዓመቱ መጨረሻ ከታቀደው በላይ በመከወን 192 ፕሮጄክቶችን ተግባራዊ አድርጓል። አቶ በቀለ በመቀጠል በዚህ ዓመት አጠቃላይ ወደ ህዝቡ የደረሰው የብር መጠን 4 ቢሊዮን ብር እንደሆነም ተናግረዋል። በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያ በኢትዮጵያ ላይ የምታከናውነው የዕርዳታ ሥራ ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር የአንበሳዉን ድርሻ እንደሚይዝ አመላክተዋል።

“እነዚህን ሁሉ ፕሮጄክቶች ስንሠራ በብዙ ተግዳሮቶች ታጅበን እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል” ያሉት አቶ በቀለ፣ ከእነዚህም ተግዳሮቶች ዉስጥ በጥቂቱ ሲገልፁ ፥ በሃገሪቷ ዉስጥ ተከስተው የነበሩት የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተደረገው ጦርነት ፣ የዋጋ ንረት ፥ ከፍተኛ የኑሮ ዉድነት ፣ ዝቅተኛ የገበያ አቅርቦት ፣ በተለያዩ የሃገሪቱ አከባቢዎች የተከሰቱ ድርቆቸና የሰብል መምከን ፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች  በከፍተኛ ሁኔታ የተከሰቱ የሰዎች መፈናቀል ሥራችንን በአግባቡ እንዳናከናውን እንቅፋት ሆነውብን ነበር ብለዋል። ቢሆንም ግን ይላሉ አቶ በቀለ ፥ የባለፉት አምስት ዓመታትን የሥራ አፈጻፀሞችን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናይ፥ በ 2018 ፥ 6,603,101፣ በ 2019 ፥ 5,149,310፣ በ 2020 ፥6,133,067፣ በ 2021 ፥ 6,992,310 ሰዎችን ተደራሽ ያደረግን ሲሆን ፥ በአንፃሩ በ 2022 የተረጅዎች ቁጥር በአንጻራዊነት ከፍ በማድረግ ፥ 8,915,302 ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ገልጸዋል።

ከዚህም በመቀጠል የጎርግሮሳውያኑ 2023 የበጀት ዓመትን የዕቅድና የሥራ አፈፃጸምን በተመለከተ ገለፃ እና ማብራሪያ ያደረጉ ሲሆን ፥ በዚህም ዓመት ተደራሽነቱን ወደ 8.7 ሚሊዮን ህዝብ ከፍ በማድረግ ፥ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት በፅኑ ባሳተፈ መልኩ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ታቅዷል ብለዋል። በዚህም መልኩ የተጠቃሚ የጾታ ተዋፅኦን ያብራሩ ሲሆን ፥ የእንስቶችን ቁጥር ከአለፉት ዓመታት ከፍ በማድረግ 3,952,873 ሴቶችን ያቀፈ እንዲሁም 4,478,372 ወንዶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ እና ልማት ኮሚሽን በአጠቃላይ የሃገሪቱ ክልሎች የሚያደርጋቸው የልማት እና የዕርዳታ ሥራዎች ዉስጥ ፥ በጤናው ዘርፍ ፣ በትምህርት ዘርፍ ፣ በሴቶች እና በቤተሰብ ልማት ፣ በውሃ እና በአከባቢ ልማት ፣ በስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች መልሶ ማቋቋም ላይ ፣ የተሳለጠ ልማት ፣ እንዲሁም በበጎ አድራጎት እና በአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ላይ እንደሚሰራ ይታወቃል።

31 March 2023, 16:06