ፈልግ

በደቡብ ሱዳን የእመቤታችን ማርያም የተልዕኮ ልጆች ማኅበር ሐዋርያዊ አገልግሎት በደቡብ ሱዳን የእመቤታችን ማርያም የተልዕኮ ልጆች ማኅበር ሐዋርያዊ አገልግሎት  

እህት ማርጋሬት፥ “ትምህርት ለአንድ አገር ዕድገት ወሳኝ ነው!”

የእመቤታችን ማርያም የተልዕኮ ልጆች ማኅበር አባል የሆኑት እህት ማርጋሬት ከተቀሩት የማኅበራቸው አባላት እና የሌሎች ማኅበራት ደናግል ጋር ሆነው በደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ አገልግሎት በማበርከት ላይ ይገኛሉ። የአገልግሎታቸው ዋና ዓላማ አስተማሪዎችን በማሰልጠን ወጣቶች መልካም የወደፊት ዕድል እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2008 ዓ. ም. የሱዳን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የዕርዳታ ጥያቄውን ይፋ አድርጎ ነበር። በዚህ ጊዜ የገዳማት የበላይ አለቆች አንድነት እና ዓለም አቀፍ የገዳማት የበላይ አለቆች ኅብረት በመተባበር ለደቡብ ሱዳን የበኩላቸውን እገዛ ለማድረግ ወሰኑ። የእመቤታችን ማርያም የተልዕኮ ልጆች ማኅበር አባል እህት ማርጋሬት ስኮት፣ ጉባኤውን በግል በመሳተፍ ያገኙትን ልምድ መሠረት በማድረግ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለአገሩ ሕዝብ ምን ማለት እንደሆነ እንደሚከተለው ይገልጻሉ፥

“እንደ ጎርጎሮስውያኑ 2006/2007 ዓ. ም. በሮም የተካሄዱ አንዳንድ ስብሰባዎችን በተካፈልኳቸው ወቅት፣ የገዳማት የበላይ አለቆች አንድነት እና የዓለም አቀፍ ገዳማት የበላይ አለቆች ልኡካን በጉባኤው ላይ ስለ ደቡብ ሱዳን ያላቸውን ልምድ አካፍለው ነበር። የእኔ ማኅበርም በደቡብ ሱዳን በሚደረገው አገልግሎት ለመቀላቀል ወስኖ ስለ ነበር አገልግሎቱን እኔ ራሴ ማቅረብ እንደምፈልግ ተጠየቅሁ። ስለዚህ በጎርጎሮሳውያኑ ነሐሴ ወር 2008 ዓ. ም. ከአራት እህቶች ጋር ወደ ደቡብ ሱዳን በመሄድ፣ በቶምቡራ-ያምቢዮ ሀገረ ስብከት ውስጥ በሚገኝ ሪመንዜ መንደር አምስት የእመቤታችን ማርያም የተልዕኮ ደናግል የሚኖሩበትን የማኅበር ቤት አቋቋምን። ዓላማችን በማላካል እና በሪመንዜ የመምህራን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤትን እና በዋዉ የጤና ማሰልጠኛ ተቋም መመሥረት ጨምሮ የሐዋርያዊ አገልግሎት ወኪሎችን ማሰልጠን ነበር።

የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅን ማቋቋም

ከመካከላችን ሁለቱ እህቶች በያምቢዮ ሀገረ ስብከት ውስጥ በሚገኝ የመምህራን ማሰልጠኛ እንዲሠሩ ተጠየቅን። የሥራ ድርሻችንም በቅድሚያ በተቋማቱ ውስጥ ሙያዊ ስልጠና መስጠት ነበር። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2011 ዓ. ም. አካባቢ ከሌሎች ገዳማት የመጡትን ጨምሮ የአባላቱ ቁጥር ማደግ ጀመረ። ቀጥሎም ወደ ያምቢዮ ከተማ በመዛወር የቤተ ክርስቲያን ይዞታ በሆነው መሬት ኮሌጅ ተገነባ። በዚህ ልዩ ማዕከል ውስጥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2012 ዓ. ም. ስለ ስልጠና ማስተማር ጀመርን። ምክንያቱም በወቅቱ ያስፈልግ ስለ ነበር ዋና ግባችን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንን ማዘጋጀት ነበር።

 

ደቡብ ሱዳን ራሷን የቻለች ሀገር ሆነች

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2011 ዓ. ም. ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ስትቀዳጅ በሕዝቡ ዘንድ ታላቅ ደስታ ሆነ። ይህም ችግሮችን በሙሉ ያቃልላል የሚል ተስፋን አሳደረ። የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ራሱን ችሎ ሀገሪቱን በራሱ ማስተዳደር እንደሚችል በማሰብ ነዋሪው በተስፋ እና በጋለ ስሜት የተሞላ ነበር። ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት በርካታ ችግሮች በማጋጠማቸው እና ነገሮች የተጠበቁትን ያህል ስላልሄዱ በተወሰነ መልኩ ብስጭቶች ነበሩ። እንደ አንድ ሉአላዊ አገር አብረን መሥራት ስንጀምር ሁሉ ዓይነት ችግር መጡ።

ለአንድ አዲስ አገር ትምህርት ወሳኝ ነው

ልማትን ለማምጣት መልካም የትምህርት ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ብዙ ሰዎች ተረድተዋል። የማሰልጠኛ ተቋማት እጥረት ስለ ነበር፣ በወቅቱ የሰለጠኑ መምህራን ቁጥር ጥቂት ነበር። ነባር ተቋማት በገንዘብ እጦት ምክንያት አገልግሎት መስጠት አቁመዋል። የሰለጠኑ መምህራንን ለማቅረብ እኛም በበኩላችን ጥቂቶች ነበርን። በመላ አገሪቱ የወደፊት ትውልዶችን ማዘጋጀት የሚችሉ የሰለጠኑ እና ብቁ መምህራን ፍላጎት ነበር።

ገና ከጅምሩ በብዙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መማር የሚፈልጉ ያልሰለጠኑ መምህራን መኖራቸውን ተገነዘብን። በዚህ የተነሳ በሁለት ደረጃዎች መሥራት ጀመርን፥ የመጀመሪያው በሚሠሩባቸው ተቋማት ውስጥ ሥልጠናን መስጠት ሲሆን፣ ሁለተኛው ከውጪ የሚሰጡ ኮርሶችን እንዲከታተሉ ማድረግ ነበር። ምንም ዓይነት ቅድመ ዝግጅት ያልነበራቸው፣ ዕድሜያቸው 20 የሚሆናቸው የኮሌጅ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች ዕድሜያቸው 50 የሚሆናቸውም ነበሩ። ተማሪዎቹ በከፍተኛ ስሜት የተሞሉ እና ለመማር የሚጓጉ፣ ተምረው ከተመረቁ በኋላም ወደ ትምህርት ቤታቸው ተመልሰው ወይም ወደ ትምህርት ሥርዓቱ ገብተው በማስተማር ለወጣቶች የተሻለ ነገር ለመስጠት የሚፈልጉ ነበሩ። ለሕይወት አደገኛ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ቢሠሩም አዎንታዊነት ነበራቸው። ከፍተኛ የማስተማር ፍላጎት ስላላቸው ዛሬም ሰዎችን ከዛፍ ሥር ሲያስተምሩ ማየት ይቻላል።

የመምህራን የሥልጠና መርሃ ግብር ውጤት አለው

በተቋማችን ያስተማርናቸው ሰዎች በጉጉት በየቦታው እየሄዱ በማስተማሪ ሥራ ላይ ለመሰማራት ቆርጠዋል። ሥራቸውን በተለያዩ የትምህርት መገልገያ መሣሪያዎች አዘጋጅተው ሁሉንም ዓይነት ጥረቶች በማድረግ ጠቃሚ ነገር ለተማሪዎቻቸው ያቀርባሉ። ብዙውን ጊዜ እኛ ያሰለጠንናቸው ሰዎች በትምህርት ቢሮ ውስጥ ተቀጠረው እንዲሠሩ በመንግሥት ይፈለጋሉ። ተማሪዎቻችንን በትምህርት ቤቶች ስንከታተላቸው፣ የሚተማመኑባቸው አስተማሪዎች ስላላቸው የተማሪዎች ተሳትፎ፣ ደስታ እና ጉልበት መኖሩን ተመልክቻለሁ። አንድ ሰው ለወደፊት ዕድገቱ ማለቂያ የሌላቸው ዕድሎች መኖራቸውን ማየት ይችላል። ስለዚህ ይህ ሁሉ ለሀገር ዕድገት እጅግ ጠቃሚ ነው።

ደቡብ ሱዳንን የሚጎበኙ ሦስት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የካንተርበሪው አንግሊካዊ ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ እና የስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጉባኤ ተወካይ ቄስ ያን ግሪንሺልድስ(ዶ/ር) ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ ባላቸው ርኅራኄ አጋርነታቸውን መግለጽ እና ከጎኑ መቆም ይፈልጋሉ። ጉብኝታቸውም ወሰን የሌለው የድጋፍ ምልክት ነው። እነዚያ ሰዎች እና ለሰላም የጸለዩባቸው ቤተ ክርስቲያናት ለዚህች ወጣት እና በችግር ውስጥ ለምትገኝ አገር የሰላም ተስፋን የሚሰጡ ናቸው። ሦስቱ የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በሕዝቦች መካከል አንድነትን ማምጣት የሚቻል መሆኑን ያሳያሉ። አብያተ ክርስቲያናት አንድ መሆን ከቻሉ አገር እንዲያድግ እና ሕዝቦችም አንድ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል። ከፍተኛ ተምሳሌታዊ እሴት ያለበት ምልክት በመሆኑ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ለጉብኝታቸው አድናቆትን ይኖራቸዋል ብዬ አስባለሁ።

አስደናቂ እምነት ያላቸው ሕዝቦች

የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ጠንካራ እምነት ያለው እና በእግዚአብሔር የሚያምን ሕዝብ ነው። እግዚአብሔር እንደሚወደው የሚያውቅ ሕዝብ ነው። የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ያንን የምንለማመድበት ሌላው መንገድ ነው። በደቡብ ሱዳን ውስጥ ሕይወት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እና በአሁኑ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ የተጋለጡ መሆናቸውን ብዙ ጊዜ አንሰማም። በቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እና በደቡብ ሱዳን ላይ ትኩረት ይደረጋል። ይህም በደቡብ ሱዳን በስቃይ ውስጥ ለሚገኙ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕርዳታውን ሰላማዊ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ ማድረስ የሚያስችል ግንዛቤን እንደሚያስጨብጠው ተስፋ አደርጋለሁ።”

 

01 February 2023, 15:17