ፈልግ

በቅዱስ ቃሉ ላይ የሚደረግ አስተንትኖ፤ በቅዱስ ቃሉ ላይ የሚደረግ አስተንትኖ፤ 

የኅዳር 4/2015 ዓ. ም. ዘጽጌ 6ኛ ዕለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ፤

  የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ (ማቴ 6፡ 25-34)

          “እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” (1ኛ ጴጥሮስ 5፡7)

በክቡር አባ ዳንኤል ኃይሌ የተዘጋጀ፤

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ እንደምን ሰንብታችኋል!  ቃሉን ሰምተን እውነተኛ የእርሱ ደቀ መዝሙር እንድንሆን መንፈስ ቅዱስ ይርዳን። ዛሬም ለእያንዳንዳችን እግዚአብሔር ድምፁን በቃሉ አማካኝነት ያሰማናል። በቃሉ መንፈሳዊ ሕይወታችን ይታደሳል። የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስማት እንድንችል እንደ ሳሙኤል “ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” እንል ዘንድ ልቦናችንን ይክፈትልን።

በዛሬው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ለኑሮ መጨነቅ እንደሌለባቸው ያስተምራቸዋል። እንዲህም ይላቸዋል፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? (ማቴ. 6: 25) አንድ ክርስቲያን ወይም አንድ የክርስቶስ ተከታይ ለምን  ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት  ያስረዳል። በዚህ ምድር ላይ ሰው ፍላጎቱ እና ምኞት ብዙ ነው፤ ማለቂያ የለውም። ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል እስከ የት መሄድና ምን ማድረግ እዳለብን መስመር ያስቀምጥልናል፤ ገደብ ያበጅልናል። የእግዚአብሔር ቃል ምን ማድረግ እንዳለብን እና እንደሌለብን ይናገራል። ለዚህ ነው ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፥ “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው” ያለው። (መዝ. 119:105) አንድ ክርስቲያን ማስቀደም ያለበት ነገር ቢኖር፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት እና ጽድቅ መሆን አለበት። ለነፍሳችን ቅድሚያ መስጠት አለብን። የ “አባታችን ሆይ!” ጸሎት ስናደርስ፥ “በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ! ስም ይመስገን መንግሥትህ ትምጣ!” እንላለን። ይህ ማለት ለእግዚአብሔር መንግሥት ቅድሚያ መስጠታችንን ይገልጻል። ቀጥሎ ያለው የጸሎት ክፍል ደግሞ፥ “የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን” የሚል ነው። ይህ ጸሎት እንዴት መጸለይ እና ምን ማስቀደም እንዳለብን ያስተምረናል።

በዛሬው ወንገልም፥ “ከሁሉ አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት እና ጽድቅ ፈልጉ!” ይለናል። አብዛኛውን ጊዜ ስንጸልይ ራሳችንን እናስቀድማለን፤  ለችግሮቻችን ቅድሚያ እንሰጣን። በዛሬው ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለማን ቅድሚያ መስጠት እዳለብን ይናገረናል። በዚህ የወንገል ክፍል ስድስት ጊዜ ስለ ጭንቀት ይናገራል። “ሰለምትበሉበት እና ሰለምትጠጡት ነገር አትጨነቁ” ይለናል። ጭንቀት እና ክርስትና አንድ ላይ የሚሄዱ አይደሉም። ጭንቀት የእምነት ማነስ ምልክት ነው። የክርስትና ግብ ስለ ምግብ መጨነቅ አይደለም። ምግብ እና ሰውነት ጊዜያዊ ናቸው። ነፍስ ግን ዘላለማዊ ናት። የምድሩ ጊዜያዊ ነው፤ የሰማዩ ግን ዘላለማዊ ነው። ስለዚህ ጭንቀት የአረማውያን መለያ ነው እንጂ የክርስቲያኖች መለያ አይደለም። አረማዊያን ሰማያዊ አባት የላቸውም፤ የእግዚአብሔር ፍቅር ምን እደሆን አያውቁም፤ ልግስናን አያውቁም፤ እነርሱ እግዚአብሔርን ስለማያምኑ “ነገ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን?” እያሉ ይጨነቃሉ። እግዚአብሔርን አያውቁም፤ ለምድራዊ ኑሮ ብቻ ይጨነቃሉ። ጭንቀት ኃጢአት ነው። ጭንቀት ከእግዚአብሔር መራቅን ያመለክታል። ጭንቀት ደስታን ይሰርቃል፤ ጭንቀት ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ይጎዳል። ጭንቀት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ያበላሻል። በአጠቃላይ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን መስመር ከተቋረጠ ሕይወታችን ችግር ውስጥ ይወድቃል። ጭንቀት በእግዚአብሔር አለመተማመንን ያመለክታል።

እግዚአብሔር ከኛ የሚፈልገው እምነት ብቻ ነው። ጭንቀት የሚያመጣው ለውጥ የለምና። ተጨንቆ በእድሜው ላይ አንድ ቀን የሚጨምር ሰው የለም። ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ሴንቲ ሜትር የሚጨምር ሰው የለም። ተጨንቆ በባንክ ሂሳብ ውስጥ አንድ ብር የሚጨምር ሰው የለም።  ስለዚህ ጭንቀት በተቃራኒው ጤናን ይጎዳል። እዚህ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አትጨነቁ ሲለን መርሳት የሌለብን ነገር ቢኖር፥ ምንም ሳንሠራ እጆጃችንን እና እግሮቻችንን አጣጥፈን እንድንቀመጥ አይደለም። የዕለት ተዕለት ኑሮአችንን ለመኖር መሥራት አለብን። ጭንቀት እና ሥራ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። “አትጨነቁ!”  ማለት ለነገ አታቅዱ ማለት አይደለም። “አትጨነቁ!” ማለት አትሥሩ ማለት አይደለም። ሥራ ለሰው ልጆች የተሰጠ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴ. ወንጌል በምሳሌ ሲያስረዳ፥ “እስቲ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ” ይለናል። እነርሱ አይዘሩም፣ አያጭዱም፣ በጎተራም አይከቱም፤ ነገር ግን የሰማዩ አባታቸው ይመግባቸዋል።

እግዚአብሔር በብዙ መንገድ ቃሉን ያስተምረናል። ራሱን ከገለጠባቸው መንገዶች አንዱ ሥነ-ፍጥረት ነው። ተፈጥሮን በመመልከት ሰለ እግዚአብሔር ብዙ ነገር መማር እንችላለን። ወፎች “ምን እንበላለን፣ ምንስ እንጠጣለን” ብለው አይጨነቁም። ወፎችን “የሰማዩ አባታቸው ይመግባቸዋል” ሲል ሳይሠሩ እግዚአብሔር ምግብ ይሰጣቸል ማለት አደለም። እነርሱም ምግብ ፍለጋ እና መኖሪያ ጎጆአቸውን ለመቀለስ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። ከወፎች መማር ያለብን ሌላው ነገር፥ ባማረ ድምፃቸው ጥዋት ተነስተው እግዚአብሔርን ሲያመሰገኑ መስማት ነው። እኛስ ቀኑን የምንጀምረው እግዚአብሔር ስላደረግልን መልካም ነገር በማመስገን ወይስ በማማረር። ስለዚህ እግዚአብሔር ለዚህ ለትንሹ ፍጡር የሚያስብ ከሆነ እኛ በእርሱ አምሳል ለተፈጠርን እንዴት አብልጦ አያሰብልንም? “በእርሱ ታመኑ፤ የሚያስጨንቃችሁን ነገር ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።” (1ኛ ጴጥ. 5:7)

ቀጥሎም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሜዳ አበቦችን በምሳሌነት ወስዶ ያስተምረናል። አበቦች ለውበታቸው አይጨነቁም፣ አይፈትሉም፣ አይደክሙም። “ነገር ግን እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም!” (ማቴ. 6:30) እዚህ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እሳት ሲናገር የመጨረሻ የፍርድ ቀን መሆኑን ያመለክታል። እንዲህም ይላል፥ “ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? (ማር. 8:36) እሳት ወይም ገሃነም የሚባለው  እግዚአብሔር የማይገኝበት፣ ፍቅር እና ሰላም የሌለበት ቦታ ምሳሌ ነው። ስለዚህ ወንድሞችና እህቶች ሆይ! ክርስቶስ የሌለበት ሕይወት፣ ክርስቶስ የሌለበት ኑሮ እና ሃብት ይህን ይመስላል። “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት እና ጽድቅ ፈልጉ!” የተባልነው ለዚህ ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት እና ጽድቅ ያለ መልካም ተግባር የምናገኘው አይደለም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር፥ “መንግሥተ ሰማይ በመካከላችሁ ናት!” ይላል። ይህ ማለት በምድር ላይ ናት ማለቱ ነው። የክርስቶስን ሕይወት በተግባር መኖር የምንጀምረው ከምድራዊ ሕይወት ነው። የክርስትና ሕይወት በኢየሱስ ክርስቶስ መኖር፣ የእርሱን ሕይወት ለመኖር መጣር ማለት ነው። የክርስትና ሕይወት የቅዱስ ቁርባን ሕይወት ነው። የክርስትና ሕይወት የወድማማችነት እና የእህትማማችነት ሕይወት ነው።  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃል ብቻ ሳይሆን በሕይወቱም ጭምር አስተምሮናል። እኛም የምንሰማውን የቅዱስ ወንጌል ቃል በተግባር ማሳየት አለብን። ስለዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው ጥያቄ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ፥ “ስንት ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ሄደሃል? ወይም ሄደሻል?” የሚል ሳይሆን “ምን አድርገሃል? አድርገሻል?” የሚል ነው። በራእ. 22:12 እንዲህ ይላል፥ “እነሆ እኔ በቶሎ እመጣለሁ፤ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው የምሰጠውን ዋጋ ይዣለሁ” ይላል። እንዲሁም በማቴ. ምዕ. 25 ላይ ስለ መጨረሻው የፍርድ ቀን የተጠቀሰውን መመልከት እንችላለን።

የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ሁሉም ይጋሩታል፤ ይሰሙታልም። ነገር ግን በዓለማችን ውስጥ ጦርነት፣ የሰላም መደፍረስ፣ ረሃብ፣ በሽታ፣ ራስ ወዳድነት፣ ስግብግብነት እየበዛ መምጣቱ እንመለከታለን። ፍቅር እና መተሳሰብ የለም፤ አንዱ የዓለማችን ክፍል ጠግቦ ሲተርፈው ሌላው በረሃብ ተሰቃይቶ ሲሞት እንመለከታለን። እግዚአብሔር በቃሉ የሚነግረንን በተግባር የመተርጎም ችግር እንዳለ እንገነዘባለን። እግዚአብሔር ሃብት ሲሰጥ ያለ ምክንያት አይደለም። ለሌላቸው እድናካፍላቸው ጭምር ነው። ጌታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ፥ “ድሆች ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው” አላቸው። (ማቴ. 26:11) የተሰጠን ጸጋ ለግል ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ለማካፈል መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ይላል፥ “ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ እምነትን ያገኝ ይሆን?” (ሉቃ. 18:8) ይህ ለሁላችን የቀረበ ትልቅ ጥያቄ ነው።

የኢየሱስ ክርስቶስ ስብከት ዋና ማዕከል ስለ እግዚአብሔር መንግሥት መናገር ነበር። “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት እና ጽድቅ ፈልጉ!” ይለናል። የእግዚአብሔርን መንግሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍቶልናል። ሐዋርያትም ወደ ምድር ዳርቻ ሁሉ የተላኩት ስለ እግዚአብሔር  መንግሥት እንዲሰብኩ ነው። ይህች በሰናፍጭ የተመሰለች ትንሽዋ  ዘር የክርስቲያኖች ሁሉ ቤት እና ጥላ ናት። ጸሎታችን እና  ልመናችን የዘለዓለም ማረፊያችን የሆነች የእግዚአብሔርን ቤት ለመውረስ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካችን በምድራዊ ነገሮች ተታልለን ዘላለማዊ የሆነውን የሰማይ ቤት እንዳናጣ፣ በኑሮአችን እና በሥራዎቻችን ሁሉ ለቃሉ ታማኞች  እንድንሆን  መንፈስ ቅዱስ ይርዳን። የቃሉ ማደሪያ የሆነች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።

12 November 2022, 09:22