ፈልግ

በብራዚል የሚገኝ ግዙፉ የአዳኙ ክርስቶስ ሐውልት በቀይ መብራት ደምቆ በብራዚል የሚገኝ ግዙፉ የአዳኙ ክርስቶስ ሐውልት በቀይ መብራት ደምቆ  

በዓለማችን ውስጥ የክርስቲያኖች ስደት እየጨመረ መሄዱ ተገለጸ

በስደት የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን የሚረዳ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን እንግሊዝ ከሚገኝ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ በኩል ይፋ ባደረገው አዲስ ዓመታዊ ሪፖርቱ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ጭቆና ወይም ስደት 75 በመቶው መጨመሩን ጥናቱ ከተካሄደባቸው አገራት ያገኘውን መረጃ ዋቢ በማድረግ አስታውቋል። ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ በዓለም ዙሪያ የሃይማኖት ነፃነት የሌላቸው እና በስደት ላይ የሚገኙ ክርስቲያኖች ሁኔታ ትኩረት ለመሳብ በሚል ዓላማ በየዓመቱ ዓለም አቀፍ “ቀይ ሳምንት” የተሰኘ ዘመቻ እንደሚያካሄድ ይታወቃል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓመታዊ ዘመቻው በተለምዶ በኅዳር ወር ውስጥ በተለያዩ አገራት ሕንፃዎች እና ምልክቶች በቀይ መብራት እና በልዩ ተነሳሽነቶች፣ በጸሎት እና ምስክርነቶችን በመስጠት የሚሄድ መሆኑ ይታወቃል። ምንም እንኳን ዝግጅቶቹ በሙሉ የኅዳር ወር ውስጥ የሚቀርቡ ቢሆንም በዓለም ዙሪያ የሚዘጋጁ በርካታ የጸሎት እና የምስክርነት ዝግጅቶች ኅዳር 14 ቀን እንደሚካሄዱ ታውቋል።

“የተሰደዱት እና የተረሱት?”

የዘንድሮ ዘመቻው ለንደን በሚገኝ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ጽ/ቤት አስተባባሪነት ኅዳር 7/2015 ዓ. ም. በይፋ መጀመሩ ታውቋል። ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ ከዚህም ጋር በተያያዘ “የተሰደዱት እና የተረሱ?” በሚል ርዕሥ ከ2012 እስከ 2014 ዓ. ም. ድረስ በእምነታቸው የተጨቆኑ ክርስቲያኖች ሪፖርት ይፋ አድርጓል። ጥናቱ የዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅት ዓመታዊ የሃይማኖት ነፃነት ሪፖርትንም የሚያካትት ሲሆን የተዘጋጀውም በእንግሊዝ በሚገኝ፣ በስደት የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን የሚረዳ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ብሔራዊ ቢሮ መሆኑ ታውቋል። ጥናቱ በተካሄደባቸው 24 አገራት ውስጥ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርስ ስደት ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ 75 በመቶ መጨመሩ ታውቋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ የሚታይ የክርስቲያኖች ስደት

በተለይ አሳሳቢው በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ክርስቲያኖች ሁኔታ ሲሆን፣ በአንድ ወቅት በማደግ ላይ የሚገኙ ማኅበረሰቦች በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም ከኢስላማዊ አክራሪነት ጀምሮ በመድልዎ፣ በጦርነት እና በምጣኔ ሃብት ችግሮች ምክንያት የመካከለኛው ምሥራቅ ህዝቦች ችግር ውስጥ መውደቃቸው ተመልክቷል።ሪፖርቱ አንዳስታወቀው የእስራኤል መንግሥት ከተመሠረተበት ከጎርጎሮሳውያኑ 1948 ዓ. ም. ጀምሮ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል በተፈጠረው ውጥረት እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት በፍልስጤም ግዛቶች ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ቁጥር 18 ከመቶ ወደ 1 ከመቶ ዝቅ ማለቱን ታውቋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢየሩሳሌምን ጨምሮ ከ5,000 የሚበልጡ ክርስቲያኖች ግዛቶቹን ለቀው መሰደዳቸው የሚታወስ ሲሆን ይህም ቀደም ሲል ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ እና ካናዳ ከሄዱት በአሥር ሺዎች ከሚቆጠሩት ጋር እንደሚደመር ታውቋል።

ኢራቅ

በተለይ ከጎርጎሮሳውያኑ 2014 እስከ 2017 ዓ. ም. ድረስ በእስላማዊ መንግሥት (ዳኢሽ) ሽምቅ ውጊያ ወቅት በሶርያ እና በኢራቅ የታየው የክርስቲያኖች ስደት ከፍተኛ እንደነበር ታውቋል። በኢራቅ ክርስቲያኖች ዘንድ ስደት የተጀመረው በአሜሪካ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ሳዳም ሁሴንን ከሥልጣን ለማውረድ አመጽ በተካሄደበት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ 2003 ዓ. ም. እንደነበር ይታወሳል።   እስላማዊ መንግሥቱ የሜሶጶጣሚያ ክርስትና መገኛ የሆነውን የነነዌ ሜዳን በያዘበት ወቅት ከ 100,000 በላይ ሰዎች ለስደት በተገደዱበት ወቅት በክርስቲያኖች ላይ መከራ መባባሱ ታውቋል። በወቅቱ በርካታ ክርስቲያኖች የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለቀው መሸሸጊያ ፍለጋ ወደ ኩርዲስታን ወይም ሌሎች አጎራባች አገሮች ካልሆነም ክልሉን ሙሉ በሙሉ ለቀው ወደ ሰሜን አሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና አውሮፓ መሰደዳቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ሶርያ

በተመሳሳይ መልኩ በሶርያ ውስጥ በበሽር አል አሳድ መንግሥት እና በታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት ባስከተለው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት አሁንም በርካታ ክርስቲያኖች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ እያስገደዳቸው ሲሆን ብዙዎቹንም ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱ ተስፋ እያስቆረጠ መሆኑ ታውቋል። በዚህም ምክንያት ከጎርጎሮሳውያኑ 2011 ዓ. ም. በፊት ከሶርያ ሕዝብ መካከል 10 በመቶ የነበረው የክርስቲያን ማኅበረሰብ ቁጥር ዛሬ ወደ 2 በመቶ ዝቅ ማለቱን እና ህልውናው አሁን አደጋ ላይ መውደቁን በስደት የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን የሚረዳ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ዘገባ አመልክቷል።

ሊባኖስ

በሊባኖስ ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ እየተባባሰ ሲሄድ፣ በፖለቲካ እና በተቋማት ውስጥ በሚታይ አለመረጋጋት በርካታ ክርስቲያኖች አገራቸውን ለቀው መውጣታቸውን ቀጥለዋል። ባለፉት 30 ወራት በቤሩት የሚገኘው የካናዳ ኤምባሲ ከ10,000 በላይ የኢሚግሬሽን ማመልከቻዎችን ከወጣቶች እና ከቤተሰቦች ተቀብሏል። እንደ ዘገባው ከሆነ አንጻራዊ የፖለቲካ መረጋጋት እና የተሻለ ደህንነት ቢኖርም ብዙ ክርስቲያኖች ዮርዳኖስን እየለቀቁ መውጣታቸው ተመልክቷል።

አፍሪካ

ሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የተመለከተው ጥናቱ ትኩረቱን ያደረገው መንግሥታዊ ካልሆኑ ታጣቂዎች የሚሰነዘር የሽብር ጥቃት እና በተለይም እስላማዊው አሸባሪ ቡድን ቦኮ ሃራም በሚፈጽመው የሽብር ተግባር ከጎርጎሮሳውያኑ ጥር ወር 2021 እስከ ሰኔ ወር 2022 ዓ. ም. መካከል ከ7,600 በላይ የናይጄሪያ ክርስቲያኖች መገደላቸው ታውቋል።

እስያ

በእስያ አኅጉር ስደት በከፍተኛ ቁጥር በተመዘገበባት ሰሜን ኮርያ ውስጥ ሃይማኖት እና ልምምዱ በኪም አገዛዝ ለአሥርት ዓመታት በተደራጀ መልኩ ሲጨቆን መቆየቱ ታውቋል። እንደዚሁም በሃይማኖታዊ ብሔርተኝነት ምክንያት እንደ ሕንድ እና ስሪላንካ ባሉ ሌሎች የእስያ አገራት በክርስቲያኖች ላይ የሚደርስ ጥቃት እየጨመረ መሄዱ ታውቋል። ሕንድ ከጎርጎሮሳውያኑ ጥር ወር 2021 ዓ. ም. እና ሰኔ ወር 2022 ዓ. ም. መጀመሪያ መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ 710 ፀረ-ክርስቲያን ሁከቶችን ያሳለፈች ሲሆን ብዙዎቹ በሂንዱ ብሔርተኞች የተመሩ እንደነበር ታውቋል። ሪፖርቱ በተጨማሪም እንደ ግብፅ እና ፓኪስታን ባሉ የተለያዩ ሀገራት፣ ክርስቲያን ልጃገረዶች የእስልምናን እምነት እንዲቀበሉ ለማድረግ የግዳጅ ጋብቻ እንዲፈጽሙ፣ ስልታዊ አፈና እና መደፈር እንደሚደርስባቸው ታውቋል። በዚህ አስደማሚ ሁኔታ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ ምዕመናን በሙሉ ረቡዕ ኅዳር 14/2015 ዓ. ም. በጸሎት እንዲተባበሩ እና የስደትን መቅሠፍት በመቃወም በቤተ ክርስቲያናቸው መብራት እንዲያበሩ ጠይቋል።

የ “ቀይ ረቡዕ” ተነሳሽነቶች

ሪፖርቱ አክሎም ዕለቱን ምክንያት በማድረግ በአውስትራሊያ የሚገኙ አሥር ካቴድራሎች በመብራት እንደሚደምቁ፣ በእንግሊዝም እንደዚሁ ዕለቱን ምክንያት በማድረግ የሚከናወኑ በርካታ ተግባራት መኖራቸው ታውቋል። በፈረንሳይ ውስጥ በሚገኙ አንድ መቶ ቁምስናዎች ደወል እንደሚደወል እና ስብሰባዎች እንደሚካሄዱ ታውቋል። በጀርመንም እንደዚሁ ከኢራቅ፣ ከናይጄሪያ እና ከፓኪስታን የመጡ ስደተኞች ምስክርነታቸውን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል። “ቀይ ሳምንት” በብራዚል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2015 ዓ. ም. የተጀመረ ሲሆን እዚያው የሚገኝ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ቢሮ በኢራቅ ውስጥ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን ስደት በማስመልከት በአገሪቱ በሚገኝ ግዙፍ የክርስቶስ አዳኝ ሃውልትን በቀይ መብራት ባደመቀብት ወቅት እንደ ነበር ይታወሳል።  

22 November 2022, 16:28