ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል 

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2014 ዓ.ም. የፍልሰታ ፆም መግቢያን በማስመልከት መልዕክት አስተላለፉ

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ኢትዮጵያውያን ካቶሊካውያን ምእመናንና የቅድስት ማርያምን ፍልሰታን ለሚያከብሩ ሁሉ እንኳን ለ2014 ዓ/ም የፍልሰታ ማርያም ጾም በሰላም አደረሳችሁ እያልኩ የተቀደሰ የተባረከ ጾም እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡

እመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር መገኘት ምልክት የሆነች የቃል ኪዳኑ ታቦት ናት። ለአብዛኛዎቹ የብሉይ ኪዳን ሰዎች የቃል ኪዳኑ ታቦት ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ቦታ ብቻ አልነበረም፣ ነገር ግን የሕልውናቸው ዋናው ቦታ፣ ልዩ ቦታ ነበር። ያ ሁሉ መተማመኛቸው ግን በ587 ዓ.ዓ አካባቢ ተለወጠ። ባቢሎናውያን በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሊዘርፉና ሊያፈርሱ እንደሚመጡ ባወቀ ጊዜ ነቢዩ ኤርምያስ የቃል ኪዳን ታቦቱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ ወስዶ በኔቦ ተራራ ላይ በዋሻ ውስጥ ሸሸጎ ቀበረው። አንዳንዶች የቃል ኪዳን ታቦቱ ወደ ተደበቀበት ቦታ የሚያስኬድን መንገድ ምልክት ለማድረግ እንደሞከሩ ባወቀ ጊዜም “እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደገና ሰብስቦ ምሕረቱን እስኪያሳይ ድረስ ቦታው አይታወቅም” ብሏቸው ነበር። (2መቃ. 2:7)

ከ 600 ዓመታት በላይ የሆነው ጥበቃ ፍጻሜውን ያገኘው በአዲስ ኪዳን የቃል ኪዳኑ ታቦት በሆነችው በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፅን ባደረው በልዑል እግዚአብሔር የምሕረት ጉብኝት ነው። ይህም የሆነው በተሰቀለው እና ከጎኑ ባፈሰሰልን በአንድያ ልጁ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ውኃ እና ቅዱስ ደም አማካይነት በመጣልን የምሕረት ቃል ኪዳን ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እናቱን ማርያምን እጅግ ለሚወደው ለደቀ መዝሙሩ ለዮሐንስ እንክብካቤ አደራ ሰጠው፤ የዮሐንስንም አደራ ለእርሷ ሰጣት። ከተወሰነ ዓመታት በኋላም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አንቀላፋች፤ በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛ ኃይል ወደ መንግሥተ ሰማይ ተወሰደች። ዮሐንስም በዚያው ሕይወት ቀጠለ እና በመጨረሻም ክርስቲያንነቱ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ በሮማው ንጉሠ ነገሥት ግዞት ሥር ወደቀ። በዚያም ዮሐንስ በራእይ ኢየሱስን እንደገና አየው። ኢየሱስም እናቱን ማርያምን ለዮሐንስ በራእይ አሳየው። ኢየሱስ የቃል ኪዳኑን ታቦት ራእይ ለዮሐንስ አሳየው። እነዚያህ ሁለቱ አንድ ናቸው። ምክንያቱም ማርያም በአካል እና በነፍስ ወደ መንግሥተ ሰማያት የፈለሰች አዲስ የቃል ኪዳን ታቦት ናትና።

ይህንን ታላቅ የእምነታችንን ምስጢር በሚገባ ለማክበር ይቻለን ዘንድ ቤተክርስቲያናችን ከጥንት ጀምሮ ምእመኖቿ በጾም፣ በሱባኤ እና በፍቅር ሥራ በታላቅ መንፈሳዊነት እንድንዘጋጅ ልዩ ዕድል ሰጥታናለች። ይህ በየዓመቱ የሚመጣልን የፍልሠታ ለማርያም ጾም እና ሱባኤ ምንም እንኳ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ቢሆንም በክርስቲያኖች ሁሉ ልብ እጅግ የተወደደ እና ትልቅ መንፈሳዊ በረከትን የሚሰጠን ልዩ አጋጣሚ ነው። ፍልሠታ ለማርያምን ማክበር ማለት የእኛን የእያንዳንዳችንንም የትንሣኤ ተስፋን ማክበር ማለት ነውና። ምክንያቱም እርሷ ከልጇ ጋር ሁና የዲያብሎስን ውጊያ ያሸነፈች (ራእይ 12)፤ ቅዱስ ጳውሎስም   በድፍረት “ሞት ሆይ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? (1ኛ ቆሮ 15፡55) ባለው መሠረት ሞትን ድል በማድረግ ትንሣኤን የተለማመደች ከፍጥረታት ሁሉ የመጀመሪያ ፍሬ የሆነችው እናታችን የእኛም ዕጣ ፋንታችን ትንሣኤ መሆኑን እርግጠኛ ተስፋ እና መጽናኛችን ስለሆነች ነውና። እስከዚያ ጊዜ ግን በተስፋ እንጓዛለን።

የተወደዳችሁ ….

ይህንን የፍልሠታ ጾም ስንጾም እና ሱባኤ ስንገባ ምንም እንኳን ዛሬም ቢሆን በብዙ ጨለማ ተከብበን የዲያብሎስን ውጊያ እየተጋፈጥንም ቢሆን እንደ ከርስቲያንነታችን በጽኑ እምነት እና ተስፋ ተሞልተን ነው። ምክንያቱም ምንም ያኽል ቢጨላልም ንጋት አይቀርምና። ሞት የመጨረሻ ቃል የለውምና። ትንሣኤ መሆኑ አይቀርምና።

ስለሆነም እያንዳንዳችን በልባችን በዚህ በጾም ወቅት ከእኔ በላይ የተቸገረ፣ የሚሰቃይ፤ የተፈናቀለ፣ የተሰደደ፣ በጦርነት አውድ ዘወትር በስጋት እና ጭንቀት የሚኖር አለ በማለት ወንድማዊ የርኅራኄ፣ የአለኝታነት እና የቅርበት መንፈስ እየተሰማን ሊሆን ይገባል።

እንዚህንም የጾምና የሱባኤ ቀናት በተጋድሎም በማሳለፍ ለበዓለ ፍልሰታዋ በሰላም ለመድረስ ያብቃን። አምላክ የተቀደስ የተባረከ ጾመ ፍልሰታ ለመላው ካቶሊካውያን እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሁሉ ያድርግልን እያልኩ የደስታ ምንጭ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእኛ ለልጆቿ እና ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ትለምንልን፡፡ አሜን!

ቸሩ አምላካችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ኢትዮጵያን ይባርካት፡፡

†ካርዲናል ብርሃነየሱስ

  ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን

  የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዝደንት

04 August 2022, 17:11