ፈልግ

በኬንያ የሚካሄደው ፕሬዝደንታዊ እና የፓርላማ ምርጫ በኬንያ የሚካሄደው ፕሬዝደንታዊ እና የፓርላማ ምርጫ   (AFP or licensors)

የኬንያ ካቶሊካዊ ጳጳሳት በአገሪቱ የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ጥሪ አቀረቡ

የኬንያ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ነሐሴ 3/2014 ዓ. ም. የሚካሄደውን ፕሬዝደንታዊ እና የፓርላማ ምርጫ በማስመልከት ለወጣቶች ባስተላለፈው መልዕክት፣ ወጣቶች በፖለቲካ ሽንገላ ሳይገቡ፣ በጎሰኝነት ስሜት ሳይወድቁ እና ጥላቻን ሳይቀሰቅሱ በምርጫው በንቃት በመሳተፍ የወደ ፊት ዕጣ ፈንታቸውን እንዲወስኑ አሳስቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኬንያ የኒዬሪ ሀገረ ሰብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶኒ ሙሄሪያ ለወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ምርጫ የወደ ፊት ዕድልን ለመወሰን የሚያስችል በመሆኑ በንቃት መሳተፍ ያስፈልጋል በማለት የጳጳሳት ጉባኤ ካስተላለፈው የቪዲዮ መልዕክቶች መካከል በአንዱ አሳስበዋል። ፊደስ የተሰኘ የዜና ወኪል እንደዘገበው፣ የአሁኑ ምርጫ ከዚህ ቀደም የተደረጉ የምርጫ ቅስቀሳዎች በተግባር ያልታዩበት፣ በዚህም ምክንያት ወጣቶች ተስፋ የቆረጡበት የምርጫ ዋዜማ መሆኑን አስታውቋል።

"ሰላም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው"

ከዚህ ቀደም እንደተከሰተው የድህረ ምርጫ ብጥብጥ ስጋት አሁንም ያለ ሲሆን፣ እ. አ. አ በ 2007 እና 2008 መካከል በኪኩዩ እና በካሌንጂን ጎሳዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ከ1100 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታውሳል። በኬንያ የኒዬሪ ሀገረ ሰብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶኒ ሙሄሪያ ይህን በማስታወስ ለወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት ሰላምን እንዲጠብቁ አሳስበው ሰላም የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ ምክንያት ጳጳሱ ወጣቶች በፖለቲካዊ ተንኮል እንዳይተባበሩ፣ የጎሳ እና የጥላቻ ንግግር ሰለባ እና የጥቃት መሣሪያ እንዳይሆኑ አስጠንቅቀዋል። ብዙውን ጊዜ ወጣቶች የአመፅ መቀስቀሻነት እንደሚውሉ የገለጹት አቡነ አንቶኒ፣ በመሆኑም ማንኛውንም ዓይነት ሙስና ወይም የኃይል ማጭበርበርን ውድቅ አድርገው፣ ወጣቶች ድምጽ ከሰጡ በኋላ ወደ ቤታቸው ተመልሰው መልካም የምርጫ ውጤትን በጸለዩ እንዲጠባበቁ አሳስበዋል።

የምርጫው አስፈላጊነት

ወጣቶች በምርጫ ወቅት የሚመርጡት ሰው የማን ጎሳ አባል እንደሆነ መመልከት የለባቸውም ብለው፣ ምርጫ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ሳይሆን የሀገራችን የዕለት ከዕለት ግንባታ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል። ጳጳሱ አክለውም፣ በድምጾቻችን አሸናፊዎቹ ሀገሪቱን ለተወሰነ ጊዜ እንዲመሩ ዕድል እንደሚሰጡ፣ በምርጫ የተሸነፉትም ሀገሪቱን ወደ ቀጣዩ ድምጽ ለመምራት ሌላ ዕድል ይኖራቸዋል ሲል ተናግረዋል። በናይሮቢ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ የሆኑት ሞንሲኞር ሁበርተስ ቫን መገን በበኩላቸው፣ ሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን አክብሮ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን መሪ ከየትኛውም ጎሳ ወይም ክልል ቢሆን እንዲቀበል ጠይቀዋል።

08 August 2022, 16:39