ፈልግ

7ኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ በጣሊያን ሚላኖ ከተማ 7ኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ በጣሊያን ሚላኖ ከተማ 

ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ፣ የፍቅር ጥሪ እንደገና የሚገኝበት ዕድል መሆኑ ተነገረ

በሮም ከሰኔ 15 – 19/2014 ዓ. ም. የሚከበር 10ኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ፣ የፍቅር ጥሪ እንደገና የሚገኝበት ዕድል እንደሆነ ታውቋል። በስብሰባው ላይ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና በአውሮፓ የካቶሊክ ቤተሰብ ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ኒኮላ ስፔራንሳ የሚገኙ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባው ከሁለት ዓመት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ቤተሰብ መድኃኒቱ መሆኑን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንት አቶ ኒኮላ ስፔራንሳ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለ10ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን ለኅብረተሰቡ አስፈላጊ እንደሆነ እውቅና የሚሰጥበት እና አስፈላጊነቱንም በድጋሚ ለመግለጽ ዕድል የሚገኝበት አጋጣሚ መሆኑን አቶ ኒኮላ ስፔራንሳ ገልጸዋል። ከመጪው ሰኔ 15 – 19/2014 ዓ. ም. የሚካሄደው 10ኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫሉ በሁሉም አገራት ዘርፈ ብዙ በሆኑ ሰፊ ዝግጅቶች እንደሚከበር እና በዋናነት በሮም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሚገኙበት ደማቅ ዝግጅት እንደሚቀርብ በአውሮፓ የካቶሊክ ቤተሰብ ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ኒኮላ ስፔራንሳ አስረድተዋል። ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባው ከሁለት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓመታት በኋላ ቤተሰቦች ለማኅበረሰብ መድኃኒት መሆናቸውን፣ ሰላም የሚሰፍንባቸው ትምህርት ቤቶች፣ ፍቅር እና በጎ አድራጎት የሚፈነጥቁበት ማዕከል መሆናቸውን ፕሬዚደንቱ አብራርተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ፈጣን ለውጥ በሚታይበት ዘመን ላይ እንገኛለን” ያሉትን ያስታወሱት አቶ ኒኮላ፣ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባም የለውጥ ጊዜ አካል መሆኑን አስረድተዋል። በመላው ዓለም የሚገኙ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች በአካባቢያቸው የቤተሰብ ቀንን የተለያዩ ዝግጅቶችን በማቅረብ እንዲያከብሩት የተጋበዙት የቤተሰብ ሕይወት አስፈላጊነትን እና በሕይወቱ ዙሪያ   መወያየት አስፈላጊ እንደሆነ ለመግለጽ መሆኑ ታውቋል። ከዋናው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ አስቀድሞ በአውሮፓ ውስጥ ዓርብ ሰኔ 3/2014 ዓ. ም. መለስተኛ የቤተሰብ ስብሰባ ለማካሄድ መታቀዱን የገለጹት አቶ ኒኮላ፣ ዕለቱ የፌዴሬሽናቸው ምሥረታ 25ኛ ዓመት የሚከበርበት ዕለት መሆኑን አስታውሰው፣ በዕለቱ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በቫቲካን ተገናኝተው የማበረታቻ ቃል እንደሚቀበሉ አስረድተዋ። 

የቤተሰብን ውበት መመስከር እና ሁለ ገብነቱም ከቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ጋር ፍጹም ተስማሚ መሆኑን የገለጹት አቶ ኒኮላ፣ “ቤተሰብ ቅዱስ ወንጌልን በታማኝነት በመኖር የክርስቲያናዊ ጋብቻ ውበትን በተግባር እንዲመሰክሩ ወደ እያንዳንዱ ቤተሰብ ቤት በመግባት ማሳመን መቻል አለብን” ብለዋል። እያንዳንዱ ቤተሰብ የተልዕኮ ጥሪ አለበት ብለው፣ ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋን የምትወጣው በዚህ መንገድ መሆኑን በማስርዳት ለቤተሰብ የፍቅር ጥሪ አፅንዖትን ሰጥተዋል።

ቤተሰብን እያጋጠመ ያለውን ተግዳሮት ለማሸነፍ መሠረታዊ ሚናን መጫወት እንደሚገባ የገለጹት አቶ ኒኮላ፣ ከቤተሰብ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ የብቸኝነት ሕይወት እንደሆነ ገልጸው፣ በአውታረ መረብ አማካይነት አስቸኳይ የእርስ በእርስ ግንኙነቶችን በማመቻቸት ቤተ ክርስትያን መሆናችንን እንደገና ማረጋገጥ ይገባል ካሉ በኋላ፣ አንድ ሰው እራሱ ወደ ሌሎች ካላቀረበ በስተቀር ቤተሰብ መፍጠር የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል።

01 June 2022, 18:08