ፈልግ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ አርማ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ አርማ 

የኢትዮጵያ ከቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ወቅታዊውን የአገራችን ሁኔታ አስመልኮቶ ያስተላለፈው መልእክት

የኢትዮጵያ ካቶሊከዊት ቤተክርስቲያን በጋምቤላና በምዕራብ ወለጋ የደረሰውን አሰቃቂ የወገኖቻችን ግድያ አስመልክቶ ያስተላለፈችው መልዕክት

በስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ፣ አሀዱ አምላክ አሜን!

“አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። እኔ ግን እላችኋለሁ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል” ማቴ. 5:21።

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በአገር ውስጥ እና በተለያዩ የውጭ ሀገራት ለምትኖሩ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ላላችሁ ወገኖች በሙሉ

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ከየትኛውም ሃይማኖት አስተምህሮ ፈጽሞ ተጻራሪ የሆኑ ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ ሕይወት ለሞት፣ ለመፈናቀል እና ለስደት የሚዳርጉ ተግባራት እየተደጋገሙ ነው። የሰውን ልጅ ክብር ለመገሰስ፣ ለሞት እና ለእንግልት ለመዳረግ የሚያበቃ እና ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። የሰው ልጅ በቅድስትሥላሴ አምሳል የተፈጠረ፣ ሙሉ ክብር ያለው እና በምንም ምክንያት እና በማንም ሊገሰስ የማይችል በሕይወት የመኖር መብትን የተጎናጸፈ ነው። በሕይወት መኖር ብቻ ሳይሆን ለመኖር ምቹ በሆነ አካባቢ፣ የአካል እና የአዕምሮ ደህንነቱ ተጠብቆ ሊኖር ይገባል።

ዜጎች በሀገራቸው፣ በቄአአቸው በሰላም የመኖር ዋስትናቸው ስጋት ላይ እየወደቀ ያለበት ይህ ሁኔታ ቤተክርስቲያነችንን በእጅጉ የሳስባታል። እስካሁን በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች የበርካታ ንጹሀን ዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል። በርከቶች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ይገኛሉ። የእነዚህ ሁኔተዎች ቀጥተኛ ተጎጂዎችም አረጋውያን፣፣ ሴቶች እና ህፃነት ናቸው። የኢትዮጵያ ከቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በየአካባቢው የሚፈጸሙ  ዜጎችን ለሞት፣ ለመፈናቀል እና ለንብረት መውደም የሚዳርጉ ሁኔተዎችን አስመልክቶ በተለያዩ  ጊዜያት ግልጽ ተቃውሞዋን በመግለጽ ስታወግዝ ቆይታለች።

አሁንም በጋምቤላና በምዕራብ ወለጋ የተፈጸሙትን በአብዛኛው ሴቶች እና ህፃናት ሰለባ የሆኑበትን የንጹሀን ወገኖች ግድያ በጽኑ ታወግዘለች። እንዲሁም ሰው በማንነቱ እና በሃይማኖቱ ሊገደል የለበትም ትላለች።

መንግሥት እና አከበቢያዊ አስተዳደሮች፣ የሀገር ሽመግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ዜጎች በሙሉ እንዲህ መሰል እኩይ ተግባራት በአጭሩ እንዲቀጩ እና የቆየው እና በመላው ዓለም የምንታወቅበት የሕዝባችን ተከባብሮ እና ተደጋግፎ የመኖር ልማድ እንዲመለስ ለማድረግ ተግተው እንዲሠሩ ለማሳሰብ እንወዳለን።

በጥቃቱ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎችን እግዚአብሔር በመንግሥቱ እንዲቀበላቸው እና ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንዲልክላቸው እንጸልያለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርካት፣ ይጠብቃት።

የኢትዮጵያ ከቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት

ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

24 June 2022, 13:49