ፈልግ

ለዩክሬን ሰላም የቀረበ የመቁጠሪያ ጸሎት፤ ለዩክሬን ሰላም የቀረበ የመቁጠሪያ ጸሎት፤ 

በሮም የተካሄደው የመቁጠሪያ ጸሎት ለዩክሬን የጦርነት ሰለባዎች ድጋፍ እንደሆነ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ግንቦት 23/2014 ዓ. ም. ሮም ከተማ በሚገኝ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ ለዩክሬን ሰላም የቀረበውን የመቁጠሪያ ጸሎት መርተዋል። ቅዱስነታቸው በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን የመቁጠሪያ ጸሎት ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ማይካሂሎ፣ የቅዱስነታቸው ጸሎት ለዩክሬን ሰላም ድጋፍ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ መልዕክታቸው ሁልጊዜ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ፣ በፖለቲከኞች እና በሌሎች መሪዎች ዘንድም ተደማጭነት ያለው መሆኑን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዩክሬን የግሪክ-ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማይካሂሎ ቡብኒ፣ በዩክሬን ውስጥ የሚሰቃዩ ሰዎች በማስታወስ የሚደረግ የመቁጠሪያ ጸሎት ትልቅ ድጋፍ መሆኑን ገለጹ። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከበርካታ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካኅናት፣ ደናግል እና ምዕመናን ጋር ሆነው ሮም በሚገኝ በታላቋ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ ግንቦት 23/2014 ዓ. ም. ያቀረቡትን የመቁጠሪያ ጸሎት አስታውሰው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት “በጨካኔ የተመላ” በማለት መግለጻቸውንም አስታውሰዋል።

"የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንደ መሆኔ፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚገኙ ሀገረ ስብከቶች እና የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ሐዋርያዊ ክልሎች በኩል ድጋፍ እንደሚደረግልኝ ይሰማኛል" በማለት በዩክሬን የግሪክ-ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እና የኦዴሳ ሐዋርያዊ ክልል መሪ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማይካሂሎ ቡቢኒ ገልጸዋል።

የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ሁኔታ

በኦዴሳ ሐዋርያዊ ክልል ውስጥ ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ሁኔታ በአጠቃላይ ሲታይ እጅግ ውስብስብ ነው” ያሉት ብጹዕ አቡነ ማይካሂሎ፣ የሐዋርያዊ ክልላቸው አንደኛው በኩል በሩሲያ ወረራ ሥር የሚገኝ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎች አካባቢዎች፣ ከዶኔትስክ እና ከካርኪቭ የተፈናቀሉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ያም ሆኖ ግን ከጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ ቀናት ጋር ሲነጻጸር አሁን በምዕራብ ዩክሬን ውስጥ የሚገኙ የግሪክ-ካቶሊካዊ ቁምስናዎች ከተለያዩ የውጭ አገር ሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ከምስጋና ጋር ገልጸዋል። በሰብዓዊ ዕርዳታ ማከፋፈል እንቅስቃሴ ውስጥ ካኅናት መሳተፋቸውን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ማይካሂሎ፣ የከተማው ሕይወት ቀስ በቀስ ወደ ነበረበት እየተመለሰ በመሆኑ ገልጸዋል።

ሐዋርያዊ አገልግሎት በሩሲያ በተያዙ አካባቢዎች

ጦርነት ቢኖርም ለምዕመናን የሚቀርብ ሐዋርያዊ አገልግሎት ፈጽሞ አልተቋረጠም የኦዴሳ ሐዋርያዊ ክልል ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማይካሂሎ፣ በመጀመሪያዎቹ የወረራ ቀናት ካኅናት ከሚኖሩበት ቁምስና እንዲወጡ ቢገደዱም፣ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ወደ ቁምስናቸው ተመልሰው ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን መስጠት መጀመራቸውን እና ከምዕመናን ጋር ለጸሎት መሰብሰባቸውን አስረድተዋል።

በዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በዚያች አገር የሚገኙ አብያተ ክርስትያን በአዳዲስ ፈተናዎች ውስጥ እንዳስገባቸው የገለጹ ብጹዕ አቡነ ማይካሂሎ፣ እንደ ሌሎች በርካታ ቁምስናዎች በኦዴሳ ሐዋርያዊ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ ቁምስናዎች ምዕመናን ጦርነቱ እንዲያበቃ በማለት የሰላም ጸሎት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ካኅናትም በየአካባቢያቸው በተዘጋጁ የሰብዓዊ ዕርዳታ መስጫ ማዕከላት በመገኘት በችግር ለወደቁ ተፈናቃዮች ዕርዳታ ለማቅረብ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በሐዋርያዊ ክልላቸው ውስጥ ከሚገኙ አምስት ካኅናት መካከል ሁለቱ በሩሲያውያን ቁጥጥር ስር በሚገኙ አካባቢዎች እንዳሉ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ማይካሂሎ፣ ቤተ ሰቦቻቸውን ይዘው የሄዱት አንዳንድ ባለትዳር ቄሶች በጦርነቱ ምክንያት መመለስ ባይችሉም ከሩቅ ሆነው ወገኖቻቸውን ለመርዳት እየሞከሩ እንደሆነ፣ ካሉበት ሆነው ሰብዓዊ ዕርዳታን ለችግረኞች በማጓጓዝ እና ገንዘብ ሰብሰበው በመላክ የሚተባበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጦርነቱ የመጀመሪያ ተሞክሮ አይደለም

በጦርነቱ ወቅት የተንሰራፋውን ችግር እንዴት መወጣት እንደሚገባ የግል ልምዳቸውን ያካፈሉት ብጹዕ አቡነ ማይካሂሎ፣ ችግሮችን በሙሉ በእግዚአብሔር እጅ በአደራ እንደሚሰጡ ገልጸው፣ ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር በመታመን፣ ለእርሱ በግልጽ መንገር፣ በእርሱ ተስፋን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ላጋጠማቸው አሰቃቂ ሁኔታዎች አዲስ እንዳልሆኑ የገለጹት የ52 ዓመት ዕድሜ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማይካሂሎ፣ እ. አ. አ በየካቲት ወር 2014 ዓ. ም. የኦዴሳ እና የክሪሚያ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ሆነው መሾማቸውን ገልጸው፣ በተመሳሳይ ዓ. ም. በክሪሚያ ግዛት ወረራ መካሄዱን አስታውሰዋል። በብፁዕ አቡነ ስቪያቶስላቭ ዕርዳታ፣ ከቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ በኩል በሚደረግላቸው እገዛ በመደገፍ ካህናቱ የቁምስና አገልግሎታቸውን በክሪሚያ በሚገኙ የቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች ውስጥ ማቅረብ መቻላቸውን አስረድተዋል። ግንቦት 23/2014 ዓ. ም. ሮም ከተማ በሚገኝ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ የተካሄደውን የመቁጠሪያ ጸሎት ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ማይካሂሎ፣ “ይህ ጸሎት ቅዱስ አባታችን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በችግር ውስጥ የሚገኘውን የዩክሬን ሕዝብ ለመደገፍ የተደረገ የሚያበረታታ ምልክት ነው” ብለው፣ በሁለቱ አገራት መካከል እስካሁን የቃላት አለመግባባቶች ቢኖሩም፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባላቸው ተደማጭነት፣ በጸሎት የሚያደርጉት ድጋፍ፣ በቃል እና በተግባር የሚያደርጉት ሰብዓዊ ዕርዳታ፣ በ 21ኛው ክፍለ ዘመን ጭካኔ በተሞላበት ጦርነት ለሚሰቃይ የዩክሬን ሕዝብ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን፣ በዩክሬን የግሪክ-ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እና የኦዴሳ ሐዋርያዊ አስተዳደር መሪ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማይካሂሎ ቡቢኒ ገልጸዋል።

31 May 2022, 17:28