ፈልግ

ሐዋርያዊ ተግባራትን የሚያከናውኑ ሰዎች የሚገጥሟቸው ፈተናዎች ሐዋርያዊ ተግባራትን የሚያከናውኑ ሰዎች የሚገጥሟቸው ፈተናዎች 

ሐዋርያዊ ተግባራትን የሚያከናውኑ ሰዎች የሚገጥሟቸው ፈተናዎች

በቤተክርስቲያን ውስጥና ለቤተክርስቲያን ለመሥራት ዝግጁ የሆኑትን ሁሉ እጅግ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ እዚህ ላይ ከጳጳሳት አንሥቶ እጅግ ዝቅተኛና የተደበቀ አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ ሐዋርያዊ ሠራተኞችን ተግባራት በስፋት ለመዘርዘር አልፈልግም፡፡ ይልቁንም፣ ከአሁኑ ሉአላዊ ባህላችን አንጻር ሁላቸውንም ስለሚገጥሙአቸው ተግዳሮቶች ለማውሳት እወዳለሁ፡፡ በመጀመሪያ በፍታሃዊነት ረገድ፣ የቤተክርስቲያን አስተዋጽኦ ውስጥ በዛሬው ዓለም ከፍ ያለ ነው እላለሁ፡፡ በአንዳንድ የቤተክርስቲያን አባላትና በራሳችን ኃጢአት ጭምር የደረሰብን ሥቃይና ውርደት ስንት ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን በፍቅር እየሰጡ እንደሆነ እንድንዘነጋ ሊያደርገን አይገባም፡፡

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

እነርሱ ብዙ ሰዎችን እንዲፈወሱ ወይም በመስክ ሆስፒታሎች ውስጥ በሰላም እንዲሞቱ ይረዳሉ፡፡ በምድር ላይ ድህነት እጅግ በተንሰራፋባቸው ቦታዎች ተገኝተው የልዩ ልዩ ሱሶች ተገዥ የሆኑትን ይረዳሉ፡፡ ሕፃናትንና ወጣቶችን በማስተማር ሥራ ተሰማርተዋል፡፡ ሌላ ሰው ሁሉ የተዋቸውን አረጋውያንን ይንከባከባሉ፡፡ በአስቸጋሪ አካባቢዎች እሴቶች የሚተላለፉባቸውን መንገዶች ይፈልጋሉ፡፡ ሰው የሆነው አምላክን ምሳሌ ተከትለው ለሰው ልጅ ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩባቸውን ሌሎች ብዙ መንገዶች በሙሉ ልብ ይከተላሉ፡፡ ሕይወታቸውንና ጊዜአቸውን በደስታ መሥዋዕት የሚያደርጉ ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ሰጡኝ ድንቅ ምሳሌ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ ይህ ምስክርነት ራስ ወዳድነትን ለማሸነፍና ራሴን በተሻለ መልኩ ሙሉ በሙሉ ለመስጠት በማደርገው ጥረት መጽናኛና ድጋፍ ይሆነኛል፡፡

የዚህ ዘመን ልጆች እንደ መሆናችን መጠን፣ ሁላችንም በሆነ መንገድ የአሁኑ ሉላዊ ባህል ተጽእኖ ደርሶብናል፡፡ ይህ ሉላዊ ባህል እሴቶችንና አዳዲስ ዕድሎችን ቢሰጠንም፣ ሊወስነን፣ ሊለውጠንና በመጨረሻም ሊጎዳን ይችላል፡፡ ስለሆነም፣ ሐዋርያዊ ሠራተኞች የሚረዱባቸውንና የሚፈወሱባቸውን ቦታዎች፣ ‹‹በተሰቀለውና ከሞት በተነሣው ኢየሱስ ያለን እምነት ራሱ የሚታደስባቸው፣ መሠረታዊ የሰው ልጅ ጥያቄዎችና ዕለታዊ ጭንቀቶችን የሚጋሩባቸው፣ የግልና ማኅበራዊ ውሳኔዎች ወደ መልካምና ውብ ነገር እንዲያተኩሩ ለማድረግ ስለ ተሞክሮአችንና ስለ ሕይወታችን ያለን ዕውቀት በወንጌል ብርሃን የሚመረመርባቸውን ቦታዎች መፍጠር እንዳለብን ይሰማኛል፡፡ ከዚሁ ጋር፣ ሐዋርያዊ ሠራተኞች ስለሚገጥሙአቸው አንዳንድ ልዩ ልዩ ፈተናዎች መናገር እፈልጋለሁ፡፡

እሺ ለተልእኮ ፈተና

ዛሬ፣ መነኮሳትና ደናግላንን ጨምሮ፣ በብዙ ሐዋርያዊ ሠራተኞች ዘንድ ለግል ነጻነት እርካታ የመጨነቅ ሁኔታ መኖሩን እናያለን፡፡ ይህም ሥራቸውን የማንነታቸው መለያ ሳይሆን የሕይወታቸው ተቀጥላ ብቻ አድርገው እንዲመለከቱ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር፣ መንፈሳዊ ሕይወት ከጥቂት ሃይማኖታዊ ልምዶች ጋር የተያያዘ እንጂ የተወሰነ ምቾት ከሚሰጡ ከሌሎች ጋር መገናኘትን፣ ከዓለም ጋር መተባበርን ወይም ለስብከተ ወንጌል ቀናኢ መሆንን የማያበረታታ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ከዚህ የተነሣ፣ ብዙ የስብከተ ወንጌል ወኪሎች፣ ቢጸልዩም እንኳ፣ ከፍ ያለ ግለኝነት፣ የማንነት ቀውስና የመንፈሳዊ ግለት መቀዝቀዝ ይታይባቸዋል፡፡ እነዚህም እርስ በርስ የሚቀጣጠሉ ሦስት ክፉ ነገሮች ናቸው፡፡

አልፎ አልፎ የመገናኛ ባህላችንና አንዳንድ ምሁራን የቤተክርስቲያንን መልእክት ሽሙጥ በታጀበ የጥርጣሬ ስሜት ያስተላልፋሉ፡፡ ከዚህ የተነሣ፣ ብዙ ሐዋርያዊ ሠራተኞች፣ ቢጸልዩም እንኳ፣ አንድ ዓይነት የበታችነት ስሜት ስለሚያድርባቸው ክርስቲያናዊ ማንነታቸውንና እምነታቸውን ያነጻጽራሉ ወይም ይደብቃሉ፡፡ ይህም ዙሪያ ጥምጥም ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ይህም ማለት በማንነታቸውና በሚሠሩት ሥራ ደስተኞች አይሆኑም፤ ራሳቸውን ከስብከተ ወንጌል ተልእኮአቸው ጋር ስለማያመሳስሉ ዝግጁነታቸው ይቀንሳል፡፡ እንደ ማንኛውም ሌላ ሰው ያለውን ነገር በማግኘት አባዜ ስለሚጠመዱ የተልእኮ ደስታን ያፍኑታል፡፡ ስለዚህ፣ የስብከተ ወንጌል ሥራቸው በግዴታ መልክ የሚከናወን ስለሚሆን ለእርሱ የሚያጠፉት ጉልበትና ጊዜ ያነሰ ይሆናል፡፡

ስለዚህ፣ ሐዋርያዊ ሠራተኞች፣ የመንፈሳዊነት ስልታቸውም ሆነ የአስተሳሰብ ዘይቤአቸው ምንም ዓይነት ቢሆን፣ ከእምነታዊ (ሃይማኖታዊ አስተምህሮ) ንጽጽራዊነት ይበልጥ አደገኛ ወደ ሆነ ንጽጽራዊነት ይወድቃሉ፡፡ ይህም የአኗኗር ሁኔታቸውን ከሚቀርጹ ጥልቅና የመጨረሻ ውሳኔዎች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ ተጨባጭ ንጽጽራዊነት እግዚአብሔር እንደሌለ፣ ውሳኔዎች ሲወሰኑ ድሆች እንደሌሉ፣ ግቦች ሲጣሉ ሌሎች እንደሌሉ፣ ወንጌልን ያልተቀበሉ ሰዎች እንደሌሉ አድርጎ መሥራትን ያካትታል፡፡ ግልጽ የሆነና ጽኑ እምነትና መንፈሳዊነት ያላቸው አንዳንድ ሰዎች እንኳ የራሳቸውን ሕይወት በወንጌል ተልእኮ አማካይነት ለሌሎች በመስጠት ፈንታ ወደ ገንዘብ ዋስትና፣ ወይም በማናቸውም ኪሳራ ሥልጣን ወይም ሰብአዊ ክብር ፍለጋ ወደሚያመራ የአኗኗር ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ስለዚህ፣ ለወንጌል ተልእኮ ያለንን ጽኑ ፍላጎት ወደሚሠርቅ ነገር አንግባ፡፡

ምንጭ፣ የወንጌል ደስታ ከተሰኘው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው ዓለም ወንጌልን መስበክ በተመለከተ ለጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለደናግልና ለምእመናን ካስተላለፉት ሐዋርያዊ  ምክር ከአንቀጽ 76-85 ላይ የተወሰደ።

06 May 2022, 12:11