ፈልግ

አረጋውያን አረጋውያን 

ሊባኖስ የሰላም መልዕክተኛ አገር ልትሆን ይገባል ተባለ

በሊባኖስ ለሚካሄደው ምርጫ ድምፅ ሊሰጥ ጥቂት ቀናት በቀሩበት በዚህ ወቅት፣ ዜጎች በምርጫው በመሳተፍ አዲሱ የፖለቲካ መደብ የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንደሚያስከብር ያላቸውን ተስፋ አቶ ማርዋን ሴህናውይ ገልጸዋል። በሊባኖስ የሚገኝ “የማልታ ሠራዊት ማኅበር” ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ማርዋን ሴህናውይ፣ በአገሪቱ የሚታየው ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ ትውስታ ብቻ ሆኖ እንዳይሆን ያላቸውን ስጋት ገልጸው፣ ለመጭው ትውልድም ሰፊ የጥናት ርዕሠ ጉዳይ ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ሊባኖስ የሰላም መልዕክት የሚመነጭባት፣ ያለ ጦርነት የምትኖርበት፣ ደኅንነቷ የተጠበቀ እና ድንበሮቿም እውቅናን የሚያገኙበት ጊዜ አሁን ነው! የህዝቧ ምኞት ይህ ቢሆንም ብቻውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አቅም እንደሌለው፣ በሊባኖስ የሚገኝ “የማልታ ሠራዊት ማኅበር” ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ማርዋን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት አስረድተዋል። ከሊባኖስ መዲና ቤሩት አቤቱታዎች የሚቀርቡ ቢሆንም፣ ነገር ግን የአገሩ ሕዝብ በጠንካራ ተስፋ የተሞላ እንደሆነ የገለጹት አቶ ማርዋን፣ ባለፉት ዓመታት ውስጥ አገሪቱን ለመከራ የዳረጉ በርካታ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል። እ. አ. አ ከ1973 ዓ. ም ሊባኖስን ጦርነት፣ የሕይወት መጥፋት እና የንብረት መውደም አልተለያትም ያሉት አቶ ማርዋን፣ እ. አ. አ በ2019 ዓ. ም. እስካጋጠማት ቀውስ ድረስ የበርካታ ንጹሐን ሰዎች ደም መፍሰሱን አስታውሰዋል። ዛሬ ሊባኖስ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የማይታባት አገር ሆናለች ያሉት አቶ ማርዋን፣ ዜጎቿ ላይ ለሚደርስ ስቃይ ተጠያቂው የፖለቲካ መደብ መሆኑን ገልጸዋል። በዩክሬን ውስጥ ተባብሶ እየተካሄደ ያለውን የጦርነት ድራማን መረዳት ያቃተው የፖለቲካ መደብ፣ የፖለቲካ ሰለባ የሆነውን ሕዝብ እና ሁሉን ነገር ያጣችውን አገር የበለጠ ከማደሄየት በቀር የሚፈይደው ምንም ነገር የለም ብለዋል። 

አስከፊ ሁኔታን አለማውገዝ የሀገር ክህደት ነው

አንድ ሀገር 80% የሚሆን ዜጎቿ ከድህነት ወለል በታች መሆኑ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ሁለት አስገራሚ ምሳሌዎችን መመልከት በቂ ይሆናል ያሉት አቶ ማርዋን፣ አንድ ሠራተኛ መኪናውን ቤንዚን ለመሙላት ወርሃዊ ደሞዙን በሙሉ እንደሚከፍ ገልጸው፣ በቀን የአንድ ወይም የሁለት ሰዓት የመብራት አገልግሎት ለማግኘት ከሞላ ጎደል የወር ደሞዙን ይከፍላል ብለዋል። “በሊባኖስ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ያለው የሚባል የለም” ያሉት አቶ ማርዋን፣ የሊባኖስ መጪው ጊዜ በጨለማ የተዋጠ መሆኑን አስረድተዋል። ቅድስት አገር የምትባል ሊባኖስ ብዙ መከራ እንደደረሰባት እና የሚጠብቃት ዕድልም ሙሉ በሙሉ መጥፋት ሊሆን ይችላል ብለዋል። ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች፣ የዶክተሮች፣ የኢንጂነሮች ስደት የዕለት ተዕለት እውነታ እንደሆነ የገለጹት አቶ ማርዋን፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ለዓለም በሙሉ የሰላም መልእክት አድርገው ያቀረቧት ሊባኖስ፣ በሰውም ሆነ በባሕል በየደረጃው ድህነት ያጋጠማት መሆኑን አቶ ማርዋን ገልጸዋል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛም ለመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ያዘጋጁትን ሐዋርያዊ መግለጫቸውን ለማቅረብ ወደ ሊባኖስ መምጣታቸውን አስታውሰው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም እንደ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሊባኖስን የሰላም መልዕክተኛ አድርገው መግለጻቸውን አስታውሰው፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚታዩ አስከፊ ሁኔታዎችን አለማውገዝ የሀገር ክህደት እንደሆነ አቶ ማርዋን አስረድተዋል።

ሉዓላዊነትን ማደስ

መጭው ግንቦት 7/2014 ዓ. ም. ለሁሉም የሊባኖስ ዜጎች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ወሳኝ ጊዜ እንደሚሆን ሲነገር፣ እ. አ. አ በ2019 ዓ. ም. ከተቀሰቀሰው ብሔራዊ የሕዝብ አመፅ በኋላ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፓርላማ ምርጫ የሚካሄድበት ዕለት እንደሚሆን ታውቋል። ከ200 በላይ ሰዎች የሞቱበት፣ የቤይሩት ወደብ ፍንዳታ ከተከሰተ እና በርካታ የዋና ከተማዋ ሠፈሮች ከወደሙበት ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ የሊባኖስ ሕዝብ ተጠያቂው ማን እንደሆነ ለማወቅ እና ፍትህን እየጠየቀ ባለበት ወቅት የሚካሄድ ምርጫ መሆኑ ታውቋል።

የብጹዓን ጳጳሳት ይግባኝ

ከቅርብ ቀናት በፊት የአገርቱ ብጹዓን ጳጳሳት ለተቋማት እና ለፖለቲካ መሪዎች ጥሪ ማቅረባቸው ታውቋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ ለባለሥልጣናቱ ባቀረቡት ጥሪ፣ የድምፅ አሰጣጡ ሂደት በትክክል ስለ መፈጸሙ ዋስትናን እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርበው፣ የማሮናዊት ሥርዓተ አምልኮን የምትከተክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ቡትሮስ ራይ እሁድ ሚያዝያ 23/2014 ዓ. ም. ባደረጉት ንግግር፣ የሊባኖስ ሕዝብ ​​የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱ እንዲጠበቅለት እና የሊባኖስ የወደፊት እጣ ፈንታ እንዲፈርስ፣ ታሪካዊ ማንነቱ እንዲሸረሸር የሚፈልጉ አካላትን ማገድ እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል። በሊባኖስ “የማልታ ሠራዊት ማኅበር” ፕሬዝዳንት፣ ክቡር አቶ ማርዋን ሴህናዊ፣ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር የነበራቸውን ቆይታ ሲፈጽሙ፣ "ሀገሬ ለሰው ልጆች ስቃይ ትኩረትን የሚሰጡ ወይም ደግሞ ለሰው ልጅ ክብር የሚሰጡ የተሻሉ ፖለቲከኞች ቢኖሯት ኖሮ ከዚህ ደረጃ ላይ አንደርስም ነበር" ብለዋል።

11 May 2022, 14:23