ፈልግ

የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሳምንት የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሳምንት 

የዘንድሮ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንት የሥነ-ምህዳርን ጽንሰ-ሀሳብ የሚያጎላ መሆኑ ተገለጸ

ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ፣ ከእሑድ ግንቦት 14–21/2014 ዓ. ም. ድረስ የሚከበረው “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሳምንት፣ የፍጥረታትን ደህንነት እና እንክብካቤ ለማረጋገጥ በሚያግዙ ሰባት ዓላማዎች ላይ የሚያተኩር መሆኑ ታውቋል። በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት የተዘጋጀውን የዘንድሮ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሳምንት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ካቶሊካዊ ምዕመናን እንደሚያከብሩት፣ በ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ የተጠቀሱ የተግባር መርሃ ግብሮችን እና እስካሁን የተገኙ አበራታች ውጤቶችን በማስታወስ የሚያከብሩት መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለፍጥረት ሊደረግለት የሚገባውን እንክብካቤ እና ጥበቃን የሚገልጽ፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቃለ ምዕዳን ሰባተኛ ዓመት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ ለአንድ ሳምንት የሚቆየው መሆኑ ታውቋል። በዚህ ዓለም አቀፍ ዝግጅት ላይ የበርካታ አገራት ሰዎች ድምጻቸውን በማሰማት ውይይታቸውን እንደሚካሄዱ፣ እንዲሁም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ሥነ-ምህዳር የገለጹትን ሃሳብ በቪዲዮ ፊልም ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ እንደሚቀርብ፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ እህት አሌሳንድራ ስሜሪሊ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ እና አካባቢያዊ ዝግጅቶች

በዓለም ዙሪያ በሚከበረው የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሳምንት ውስጥ ከሰባቱ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የድርጊት መርሃ ግብር እና ከአጠቃላይ ሥነ-ምሕዳር ጋር ግንኙነት ያላቸው ሃሳቦች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው መሆኑ ታውቋል። በሳምንቱ ውስጥ የሚዳሰሱ ወሳኝ ርዕሠ ጉዳዮች፥ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ የብዝሃ ሕይወት ውድቀትን እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ፣ ግጭቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትሉት ቀውሶች፣ የቅሪተ አካላት ሚና፣ እና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ድሆችን እንዴት ማቀፍ እንደምንችል” የሚሉ መሆናቸው ታውቋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ በኡጋንዳ፣ በጣሊያን፣ በአየርላንድ፣ በብራዚል እና በፊሊፒንስ ውስጥ የሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶች እንደሚኖሩ ታውቋል።

ከግንቦት 14 – 21/2014 ዓ. ም. ድረስ የሚከበረውን የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሳምንት በማስመልከት የተናገሩት

የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” እንቅስቃሴ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቶማስ ኢንሱዋ፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሳምንት ለጋራ መኖሪያ ምድራችን በታማኝነት ስሜት የበለጠ እንድንሠራ የሚያነሳሳን ዓለም አቀፍ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።አቶ ቶማስ አክለውም “በዓለም ዙሪያ የሚታየውን ብጥብጥ እና ጥፋት ለመከላከል ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ዕለት በዕለት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበው፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከሰት አደጋ እና በሥነ ምህዳር ቀውስ ላይ አስቸኳይ እርምጃን እንዲወስዱ አሳስበዋል። በማከልም “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሳምንት የእግዚአብሔርን ፍጥረት ከጥፋት ለማዳን ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች የሚያነሳሳ የጥበብ ምንጭ እንደሆነ አስረድተዋል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ እያንዳንዱ ሰው በ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሳምንት በብቃት ለመሳተፍ በሲኖዶሳዊነት ስሜት እንዲነሳሳ ጥሪውን አቅርቦ፣ በ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ የቀረቡ የሰባት ዓመት የድርጊት መርሃ ግብሮችን ለማሳካት መጠራቱን እንደሚገነዘብ ያለውን ተስፋ ገልጿል።

21 May 2022, 18:47