ፈልግ

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት  (ANSA)

ስደት በቤተሰብ ሕይወት ላይ ተጽዕኖን እንደሚያሳድር ጥናቶች አረጋገጡ

በተባበሩት መንግሥታ ድርጅት አስተባባሪነት ግንቦት 7/2014 ዓ. ም. የተከበረውን የቤተሰብ ቀን ምክንያት በማድረግ፣ የካቶሊክ ዩኒቨርስቲዎች የምርምር ስትራቴጂ ጥምረት የተሰኘው ተቋም በቤተሰብ ፍልሰት ላይ ያተኮሩ አስተያየቶችን አቅርቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ያለውን ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማሳደግ በሚረዱ የምርምር ዘርፎች ላይ የሚንቀሳቀስ “የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ስትራቴጂያዊ ጥምረት “SACRU” የተሰኘ ተቋም፣ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በቤተሰብ ጉዳዮች ላይ ልዩ ልዩ ምርምሮችን ሲያካሂድ መቆየቱ ታውቋል። በተባበሩት መንግሥታት አስተባባሪነት እሑድ ግንቦት 7/2014 ዓ. ም ተከብሮ የዋለውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀንን ምክንያት በማድረግ፣ ፍልሰት በቤተሰብ ላይ በሚያደርሰው ተጽእኖ ላይ ያተኮሩ የአንዳንድ የምሁራን ጥናቶች መቅረባቸው ታውቋል። በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተጎዱ ሕጻናትን መርዳት የሚቻልበት መንገድ እና ቤተሰብን ለመደገፍ በሚያስችሉ መንገዶች ላይም ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ የስደት ሥነ ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ገጽታዎች፣ የቤተሰብ ግንኙነቶችን መጠበቅ እና በኅብረተሰብ ውስጥ የቤተሰብ ወሳኝ ሚና በሚሉ ርዕሠ ጉዳዮች ላይም ውይይት ተካሂዷል።

በጦርነት ተጎዱ ሕጻናትን ለመርዳት ቤተሰብን መደገፍ

በአሜሪካ በሚገኝ ቦስተን ኮሌጅ በሕጻናት ችግር ላይ ምርምር የሚያደርግ ተቋም ዳይሬክተር ተሬዛ ቤታንኩርት፣ በዩክሬን ውስጥ በጦርነት የተጎዱትን ሕጻናት ችግሮች ለመፍታት ጥረት በሚያደርግ ጥናታዊ ጽሑፋቸው፣ አሁን በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ከአራት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ ወይም ለስደት እንደተዳረጉ በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” መገመቱን አስታውቀዋል። እንዲሁም እ. አ. አ በ2020 ዓ. ም. በቀረበው የሕፃናት አድን ድርጅት ሪፖርት መሠረት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስድስት ሕጻናት መካከል አንዱ በግጭት ቀጠና ውስጥ እንደሚገኝ እና ይህም በአሐዝ ሲገለጽ ወደ 452 ሚሊዮን የሚደርስ እንደሆነ አስረድተዋል፣ ክስተቱ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ከታዩት መካከል ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

“ችግሮች ከሚታዩባቸው ሌሎች አገሮች መካከል አፍጋኒስታንን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን፣ ሶሪያን፣ የመንን፣ ሶማሊያን፣ ማሊን፣ ሰሜን ናይጄሪያን፣ ካሜሩንን፣ ሱዳንንና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክን መዘንጋት የለብንም” ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ግጭቶችን የተሻገሩ እንደ ሴራሊዮን እና ላይቤሪያን የመሳሰሉ አገራትን ጠቅሰዋል። በጦር መሣሪያ በታገዙ ግጭቶች ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን ሕጻናት በመርዳት ቤተሰቦች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የተቋሙ ዳይሬክተር ተሬዛ ቤታንኩርት አስታውቀዋል። 

በሥነ-ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ የሚመጡ ውጤቶች

በጣሊያን ዩኒቨርሲቲ ጥናት ማዕከል የቤተሰብ ጥናት ዳይሬክተር የሆኑት ካሚሎ ሬጋሊያ፣ እና እንዲሆም በጣሊያን ውስጥ በሚገኝ የልብ ኢየሱስ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ሳይንስ ፕሮፌሰር ላውራ ዛንፍሪኒ፣ ስደት በቤተሰብ ሥነ-ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ በሚያስከትለው ተጽዕኖ ላይ በማትኮር ጥናታቸውን ያካሄዱ ሲሆን፣ በቤተሰብ ውስጥ ያለው የግንኙነት ጥራት የሚያመጣቸውን ለውጦች ተመልክተው፣ የቤተሰብ አባላት ሚናን እንደገና በመመልከት በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ለመገንባት እና ለማቆየት አዳዲስ ተስማሚ መንገዶችን መፈለግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ለመጥፋት የሚሰጠው ምላሽ የሀዘን ሂደት ነው።

የስደት መንስኤ በዋነኛነት ኢኮኖሚያዊ ችግር መሆኑ ሲታወቅ፣ ቤተሰብ ከድህነት ለመትረፍ ከመሰደድ ውጪ ሌላ አማራጭ እደሌለው፣ በሁለተኛ ደረጃ፣ ከፖለቲካዊ ባህሪ አንፃር፣ ቤተሰብ በያዘው የፖለቲካ አቋም ምክንያት ስጋት ሲሰማው፣ ለሰዎች ነጻ ሃሳብ ክብርን ወደሚሰጡ አገሮች መሰደድ እንደሚመርጥ ታውቋል። በሶስተኛ ደረጃ፡ ስደት በትምህርት ወይም በሥራ ፍለጋ ጋር የተያያዘ እንጂ ከኢኮኖሚ እና ከሕግ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደማይችል ታውቋል።

በስደት አውዶች ውስጥ የአእምሮ ጤና ችግሮች

በቺሊ በሚገኝ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጥናት መምህራን የሆኑት ማርያ ኦላያ እና ኒኮላ አላሞ፣ መንግሥት ተግባራዊ ማድረግ ስላለበትን አስቸኳይ ተግባር ሲገልጹ፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ሲቪል ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር፣ በስደተት አውድ ውስጥ በቤተሰብ መለያየት ምክንያት የሚፈጠሩ የአእምሮ ጤና ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ጣልቃ በመግባት ፖሊሲዎችን ለማውጣት የሚያግዙ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ኣሳስበዋል። 

የወደፊቱን ትውልዶች ዕድል መጠበቅ

በጃፓን የሚገኘው ሶፊያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥናት ትምህርት ቤት በኩል ሃሳባቸውን ያካፈሉት ኬይኮ ሂራኦ፣ ቤተሰብ በኅብረተሰብ ውስጥ ያለውን ወሳኝ ሚና አስታውሰው፣ ቤተሰብ ምንም እንኳን በግለሰብ ሕይወት ውስጥ ያለውን ጠቀሜታ እያጣ ቢሆንም፣ ልጆችን የሚያፈራ ብቸኛው ተቋም መሆኑን አስረድተዋል። “ሕዝቦቻቸው ካልታደሱ ማኅበረሰቦች ዘላቂ ሊሆኑ አይችሉም” ከሚለው እውነታ አንጻር፣ የሕዝቦቿ መታደስ ለጃፓን በጣም አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው፣ ጃፓን በሕዝብ ቁጥር መጨመር ዝቅተኛ ደረጃ ካላቸው የመጀመሪያዎቹ አገራት መካከል አንዷ ስትሆን፣ በጃፓን ውስጥ ከሚገኙ 1,799 ማዘጋጃ ቤቶች ውስጥ በሕዝብ መመናመን ምክንያት እ. አ. አ. በ2040 ዓ. ም. 896 የሚያህሉ ማዘጋጃ ቤቶች እንደሚጠፉ ታውቋል።

16 May 2022, 15:17