ፈልግ

በቅዱስ ወንጌል የሚገኝ ደስታ በቅዱስ ወንጌል የሚገኝ ደስታ  

እምነትን ከባህል ጋር የማዋሐድ ተግዳሮቶች

የአንዳንድ ሕዝቦች ክርስቲያናዊ መሠረት፣ በአብዛኛው በምዕራብ አገሮች ያለው፣ ሕያው እውነታ ነው፡፡ በተለይ እጅግ ድሃ በሆኑ ሕዝቦች መካከል፣ የእውነተኛ ክርስቲያናዊ ሰብአዊነትን እሴቶች የሚጠብቅ ግብረ ገባዊ ሀብት እናገኛለን፡፡ እውነታውን በክርሰቲያናዊ ዐይን ስንመለከት መንፈስ ቅዱስ የሚዘራውን ዘር ልንረሳ አንችልም፡፡ በርካታ ሕዝቦች በተጠመቁበትና እምነታቸውንና አንድነታቸውንም በተለያዩ መንገዶች ከሌሎች ጋር በሚገልጹበት ሁኔታ እውነተኛ ክርስቲያናዊ እሴቶች የሉም ማለት በእርሱ ንፍገት በሌለው ሥራው እምነት ማጣትን ያሳያል፡፡ ይህም የራሱ የሆነ መገለጫና ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት ማሳያ መንገድ የሆነውን እውነተኛ ክርስቲያናዊ እምነት የሚመለከት ስለሆነ አልፎ አልፎ የሚታየውን “የቃል ዘር” አምኖ ከመቀበል የበለጠ ነው፡፡ በእምነት የታተመ ባህል ያለውን ትልቅ ጠቀሜታ በቸልታ ማለፍ አይቻልም፤ የዘመናዊ ዓለማዊነት ጥቃት ባለበት ሁኔታ፣ ውስንነቶች ቢኖሩበትም፣ በስብከተ ወንጌል የታነጸ ባህል ከአማንያን ቁጥር የበለጠ ብዙ ሀብት አለው፡፡ በስብከተ ወንጌል የታነጸ ሕዝባዊ ባህል ይበልጥ ፍትሃዊና አማኝ ኅብረተሰብ እንዲፈጠር የሚያበረታቱ የእምነትና የአንድነት እሴቶችን ይዟል፤ በምስጋና ሊቀበሉት የሚገባ ልዩ ጥበብም አለው፡፡

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ 

ወንጌልን ከባህል ጋር ለማዋሐድ ባህልን በስብከተ ወንጌል ማነጽ የግድ ይላል፡፡ ካቶሊካዊ ወግና ልማድ ባላቸው አገሮች አሁን ያለውን ባህላዊ ሀብት ማበረታታት፣ ማሳደግና ማጠናከር ማለት ይሆናል፡፡ ሌሎች ሃይማኖታዊ ልማዶች ባሉአቸው ወይም ዓለማዊነት ሥር በሰደደባቸው አገሮች ይህ የረዥም ጊዜ ዕቅድን የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ባህልን በስብከተ ወንጌል ለማነጽ አዲስ ሂደቶችን መጀመርን ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የማያቋርጥ ዕድገት እንደሚያስፈልገን መዘንጋት የለብንም፡፡ በሕዝቡ የሚወደደውን የካቶሊካዊያን ባሕሎችን በተመለከተ፣ በወንጌል መዳን ያለባቸውን ጉድለቶች መኖራቸውን መገንዘብ እንችላለን ማለትም የወንዶች ትምክህተኛነትን፣ የአልኮል ሱሰኝነትን፣ የቤት ውስጥ ሁከትን፣ መሥዋዕተ ቅዳሴ አለማዘውተርን፣ ወደ አስማት የሚመሩ በዕድል የማመን ወይም የጥንቆላ አስተሳሰቦችንና የመሳሰሉትን እናያለን፡፡ ሕዝባዊ  መንፈሳዊነት በራሱ ከእነዚህ ጉድለቶች ለመፈወስና ነጻ ለመውጣት መነሻ ይሆናል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ከክርስቲያናዊ መንፈሳዊነት ግፊት ይልቅ ለአንዳንድ ቡድኖች ውጫዊ መገለጫዎችና ልማዶች ወይም ሌሎች ነገሮችን ይተካሉ ለሚባሉ የግል ራእዮች የበለጠ ትኩረት የመስጠት ሁኔታ መኖሩ የታወቀ ነው፡፡ በመሠረቱ፣ ከእውነተኛ “ሕዝባዊ መንፈሳዊነት” ጋር የማይጣጣም ግላዊና ስሜታዊ የእምነት ሕይወትን በሚያንፀባርቁ ጸሎቶች የተሞላ የክርስቲያናዊነት ዓይነት አለ፡፡ አንዳንድ ሰዎች እነዚህን መገለጫዎች እያበረታቱ ነገር ግን ለህብረተሰብ ዕድገት ወይም ለምእመናን ሕንጸት እምብዛም ትኩረት የማይሰጡ አሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህን የሚያደርጉት ኢኮኖሚአዊ ጥቅም ለማግኘት ወይም በሌሎች ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው ነው፡፡ ከቅርብ አሠርት ዓመታት ወዲህ ካቶሊኮች የክርስትና እምነትን ለወጣቶች በሚያወርሱበት መንገድ ክፍተት ስላለ ይህንን ጉዳይ በቸልታ መመልከት አንችልም፡፡ ብዙ ሰዎች ግራ መጋባታቸውና ካቶሊካዊ ባህልን መተዋቸው አይካድም፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን ማስጠመቅ ወይም እንዴት እንደሚጸልዩ ማስተማር ትተዋል፡፡ ወደ ሌሎች ቤተ እምነቶች የመፍለስ ሁኔታም አለ፡፡ ለዚህ ክፍተት የሚጠቀሱ ምክንያቶች በቤተሰቦች ውስጥ የውይይት ዕድል አለመኖር፣ የመገናኛ ብዙሃን ተጽእኖ፣ ንጽጽራዊ ግለኝነት፣ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ በድሆች ዘንድ ሐዋርያዊ እንክብካቤ አለመኖር፣ የተቋሞቻችን ሳቢ አለመሆን እና ብዙ ሃይማኖቶች ባሉበት እምነትን አጥብቆ የመያዝ መንፈሳዊነትን እንደገና ለማደስ አለመቻላችን ናቸው፡፡

የከተማ ባሕል ተግዳሮት

አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፣ ቅድስቲቱ ከተማ (ንጽ.ራእይ.21፡2-4) የሰው ልጅ በሙሉ መዳረሻ ግብ ናት፡፡ የሰው ልጅና የታሪክ ሙላት እውን የሚሆነው በአንድ ከተማ እንደሚሆን የእግዚአብሔር ራእይ ለእኛ መናገሩ አስገራሚ ነገር ነው፡፡ ስለሆነም ከተሞቻችንን በማስተዋል መመልከት ያስፈልገናል፡፡ የእግዚአብሔር መኖር፣ መገኘት ግለሰቦችና ቡድኖች በሕይወታቸው ውስጥ ብርታትንና ትርጉም ለማግኘት ከሚያደርጉአቸው እውነተኛ ጥረቶች ጋር ይያያዛል፡፡ እርሱ በመካከላቸው ይኖራል፤ አንድነትን፣ ወንድማማችነትንና ደግነትን፣ እውነትንና ፍትህን  ያበረታታል፡፡ ይህ መኖር  ሊገለጥ እንጂ ሊወጠን፣ ሊታቀድ አይገባም፡፡ ለጊዜው፣ በተድበሰበሰና ባልታሰበ አኳኋን ቢሆንም እርሱን በእውነተኛ ልብ ለሚሹት እግዚአብሔር ራሱን አይደብቅም፡፡

ከገጠር በተለየ መልኩ በከተሞች ያለው የሕይወት መንፈሳዊ ገጽታ የሚገለጸው በልዩ ልዩ የአኗኗር ስልቶች፣ ከቦታዎችና ከሕዝብ ጋር በተያያዙ ዕለታዊ እንቅስቃሴዎች ነው፡፡ ሰዎች በዕለታዊ ኑሮአቸው ውስጥ ብዙውን ጊዜ በሕይወት ለመኖር ይፍጨረጨራሉ፤ ይህ የኑሮ ትግል በውስጡ ብዙውን ጊዜ ጥልቅ መንፈሳዊ ስሜትን ያካተተ ጥልቅ የሕይወት ግንዛቤ ያለበት ነው፡፡ ጥማትዋን ለማርካት በፈለገችና በውሃ ጉድጓድ አጠገብ በተገኘች ሳምራዊት ሴትና በጌታችን መካከል የተደረገውን ዓይነት ውይይት ለማካሄድ (ንጽ.ዮሐ.4፡1-15) ይህንን ሁኔታ በቅርበት መመርመር ይኖርብናል፡፡

ክርስቲያኖች መደበኛ ተርጓሚዎች ወይም የትርጉም ጠንሳሾች መሆናቸው በቀረባቸው አዳዲስ መስኮች አዳዲስ ባህሎች ያለ ማቋረጥ እየፈለቁ ናቸው፡፡ በመሆኑም እነሱ ራሳቸው ከእነዚህ ባህሎች ውስጥ አዳዲስ ቋንቋዎችን፣ ምልክቶችን፣ መልእክቶችንና ብዙውን ጊዜ ለኢየሱስ ወንጌል ተቃራኒ የሆኑ አዳዲስ የሕይወት አመለካከቶችን የሚያስከትሉ ሥር ነቀል ለውጦችን ይወስዳሉ፡፡ በከተሞች ውስጥ ፍጹም አዲስ ባህል ተፈጥሮ ያለ ማቋረጥ እያደገ ነው፡፡ ሲኖዶሱ እንዳመለከተው፣ ዛሬ በእነዚህ መስኮች እየተካሄዱ የሚገኙ ለውጦችና የሚፈጥሩአቸው ባህሎች ለአዲስ ስብከተ ወንጌል ምቹ ሥፍራዎች ናቸው፡፡ ይህም ለከተማ ነዋሪዎች ይበልጥ ሳቢና ትርጉም የሚሰጡ፣ ለጸሎትና ለሱታፌ የሚሆኑ አዲስ ቦታዎችንና  ዕድሎችን እንድናሰላስል ያስገድደናል፡፡ እነዚህ ተመሳሳይ ባህላዊ ለውጦች የገጠር አካባቢዎችን በመገናኛ ብዙሃን ተጽእኖ  አማካይነት የአኗኗር ዘይቤአቸውን በእጅጉ እንዲለውጡ እያደረጉዋቸው ነው፡፡

ለዚህም የሚያስፈልገው፣ ለእነዚህ ከእግዚአብሔር፣ ከሌሎች ሰዎችና በዙሪያችን ከሚገኙት ጋር ሊኖሩን የሚገቡ አዳዲስ የግንኙነት ዘዴዎችን የሚያሳየንንና መሠረታዊ እሴቶችን የሚያበረታታ ስብከተ ወንጌልን ማካሄድ ነው፡፡ ስብከተ ወንጌል አዳዲስ ታሪኮችና ሥር ነቀል ለውጦች ወደሚካሄዱባቸው ስፍራዎች መስፋፋትና የኢየሱስን ቃል ለከተሞቻችን ማዳረስ ይኖርበታል፡፡ ከተሞች ባለ ብዙ ባህል ናቸው፤ በትላልቅ ከተሞች የተወሰኑ ቡድኖች ስለ ጋራ ሕይወት ያላቸውን ሃሳብና ሕልም፣ እንዲሁም ስለሚነሡ አዳዲስ ሰብአዊ ግንኙነቶች፣ አዳዲስ ባህሎችና ስለማይታዩ ከተሞች የሚነጋገሩባቸው የግንኙነት መረቦች አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ጎን ለጎን የሚኖሩ፣ ብዙውን ጊዜ ገለልተኝነትንና ሁከትን የሚያስከትሉ የተለያዩ ዝቅተኛ ባህሎችም አሉ፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን ጠንካራ ውይይት እንዲደረግ ማገዝ አለባት፡፡ በአንድ በኩል የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ለማዳበር የሚያስችል ዘዴ ያላቸው ሰዎች አሉ፤ በአንጻሩ “ዜጎች ያልሆኑ”፣ “ግማሽ ዜጎች” እና “የከተማ ቅሪቶች” አሉ፡፡

ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው አያሌ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ለብዙ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን በሙላት እንዳያሳድጉ በርካታ መሰናክሎችን ስለሚደቅኑባቸው ዘላቂ የማመንታት ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ፡፡ ይህ ንጽጽር ከፍተኛ ስቃይን ያስከትላል፡፡ በብዙ የዓለም ክፍሎች ውስጥ  ከተሞች በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ ነጻነት፣ ስለ ሕዝባዊ ድምፅ፣ ስለ ፍትህና ስለ ሌሎች ጥያቄዎች የተቃውሞ ሰልፍ የሚያደርጉባቸው መድረኮች ናቸው፡፡ እነዚህንም ጥያቄዎች በአግባቡ ካልተረዱአቸው በኃይል ዝም ማሰኘት አይቻልም፡፡

በከተሞች ውስጥ ሰዎችን ያለ አግባብ ከቦታ ቦታ ማዘዋወር፣ የአደንዛዥ ዕጽ ንግድ፣ ሕፃናትን መበደልና ጉልበታቸውን መበዝበዝ፣ አረጋውያንንና ደካሞችን ያለ ረዳት መተው፣ እና የተለያዩ የሙስናና የወንጀል ተግባራት መኖራቸውን መካድ አንችልም፡፡ ከዚሁ ጋር፣ ከተሞች ደንበኛ የመገናኛና የአንድነት ስፍራዎች መሆን ሲችሉ ብዙውን ጊዜ የብቸኝነትና የአለመተማመን ቦታዎች ይሆናሉ፡፡ መኖሪያ ቤቶችና አካባቢዎች ብዙውን ጊዜ የሚገነቡት ለመገናኘትና ለመዋሐድ ሳይሆን ከሌሎች ለመለየትና ለመጠበቅ ነው፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ወንጌልን መስበክ የሰብአዊ ሕይወትን ክብር እንደገና ለመመለስ መሠረት ይሆናል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ለከተሞቻችን የተትረፈረፈ ሕይወት ሊሰጣቸው ይፈልጋልና (ንጽ.ዮሐ.10፡10)፡፡ ልማዳዊ ለውጥ የሌለው የስብከተ ወንጌል ፕሮግራም ለዚህ ውስብስብ እውነታ ተስማሚ እንደማይሆን መገንዘብ ቢኖርብንም፣ ወንጌል ስለ አንድና ምሉእ ሰብአዊ ሕይወት የሚያቀርበው ሃሳብ ለከተሞቻችን በሽታዎች ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡  ሆኖም፣ ሰብአዊ ሕይወታችንን በተሟላ ሁኔታ መኖርና በማንኛውም ባህልና በማናቸውም ከተማ የወንጌል ምስክርነት እርሾ የመሆን ተግዳሮትን መቋቋም የተሻልን ክርስቲያኖች እንድንሆንና በከተሞቻችን ውስጥ ፍሬ እንድናፈራ ያደርገናል፡፡

ምንጭ፣ የወንጌል ደስታ ከተሰኘው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው ዓለም ወንጌልን መስበክ በተመለከተ ለጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለደናግልና ለምእመናን ካስተላለፉት ሐዋርያዊ  ምክር ከአንቀጽ 68-76 ላይ የተወሰደ።

04 May 2022, 11:14