ፈልግ

የጋብቻ ሕይወት፣ የቤተሰብ ሕይወት የጋብቻ ሕይወት፣ የቤተሰብ ሕይወት 

የጋብቻ ሕይወት የዘወትር እንክብካቤን የሚጠይቅ የፍቅር ሕይወት ነው!

የአውሮፓውያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉት ምዕመናን ዘንድ የሕማማት ሳምንት ከሚያዝያ 3 - 8/2014 ዓ. ም. ድረስ መሆኑ ታውቋል። በዚህ መሠረት በሮም ከተማ “ኮሎሴዮ” በተባለ ሥፍራ በርካታ ምዕመናን የሚካፈሉበት የመስቀል መንገድ ጸሎት ዓርብ ማታ ሚያዝያ 7/2014 ዓ. ም. እንደሚቀርብ የዕለቱ መርሃ ግብር አመልክቷል። የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን መስቀል ይዘው የሚመሩት ባለትዳሮች፣ ወ/ሮ አሌሲያ እና አቶ ገብርኤሌ፣ የትዳር ሕይወታቸው ፍቅርን የሚያጣጥሙበት ብቻ ሳይሆን በቃል ኪዳናችን መሠረት በአስቸጋሪ ቀናት ውስጥም መታደስ አለበት ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሞያቸው መምህርት እና የኮምፒዩተር ባለ ሞያ የሆኑት ወ/ሮ አሌሲያ እና አቶ ገብርኤሌ፣ የአሥር ዓመት ሴት ልጅ እንዳለቻቸው ይናገራሉ። የተዋወቁበት አጋጣሚም ቁምስናቸው ባስተባበረው የበጋ ወራት ዝግጅት፣ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እና የዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበሩበት በ2005 ዓ. ም. መሆኑን አስታውሰዋል። በጋብቻ ሕይወት ውስጥ ያጋጠሟቸው አንዳንድ ችግሮች እንደነበሩ የገለጹት ወ/ሮ አሌሲያ፣ የቤት ዕዳን መክፈል፣ ለልጃቸው የሚያስፈልጉ ወጪዎችን መሸፈን እና ሌሎች ወጪዎችን መቻል ከሚጠበቅባቸው ሃላፊነቶች መካከል ጥቂቶቹ እንደሆኑ ተናግረዋል።

“ጭንቀቶች እና የብዙ እቅዶች አለመሳካት የጋብቻ ሕይወታችን እንዳይፈርስብን ፍርሃት ውስጥ እንድንገባ ያደረገን ቢሆንም በሌላ ወገን የበለጠ ጥረት ማድረግ እንዳለብን አስተምሮናል” ያሉት ወ/ሮ አሌሲያ፣ ለችግራቸው ዕለት ዕለት መፍትሄን የሚያዘጋጅ አባት እንዳላቸው መዘንጋታቸውን ያስታወሱት ወ/ሮ አሌሲያ፣ እግዚአብሔር ግን ለሌሎች ችግሮችም መልስ እንደሆናቸው፣ የመኖሪያ ቤት ችግርን ጨምሮ ለሌሎች በርካታ መሻቶች የእግዚአብሔርን ድጋፍ በሕይወታቸው ያልተለያቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የሕይወት ምርጫቸው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተገደበ እንዳልሆነ የገለጹት ወ/ሮ አሌሲያ፣ የልጃቸው ኪያራ መወለድ የዕቅዳቸው ወይም የስሌታቸው ውጤት ሳይሆን ነገር ግን የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን አስረድተው፣ አሁንም በእግዚአብሔር ከታመኑ ልጃቸውን ለመንከባከብ እና ለማሳደግ የሚበቃ ሀብት እና ጥንካሬን እግዚአብሔር እንደሚሰጣቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። “በችግር ወቅት በእግዚአብሔር በመታመን እርግጠኛ መሆናችን ሴት ልጃችንን በምስጋና እንድንቀበል አድርጎናል” ያሉት ወ/ሮ አሌሲያ፣ ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት እና አሁን ባለው የጦርነት ጊዜ በእግዚአብሔር መታመንን እንደማያቋርጡ ተናግረው፣ ጊዜው የስጋት እና የፍርሃት ቢሆንም እግዚአብሔር ባዘጋጀላቸው ጓደኞች እና ዘመዶች ልግስና በመታገዝ የሚያጋጥሙአቸውን ችግሮች በሙሉ በመቋቋም ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ጋብቻ የአንድነት ሕይወት ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ የብቸኝነት ሕይወት እንደሚሆን የገለጹት አቶ ገብርኤሌ፣ ሌላኛው ወገን የሌላኛውን ምኞት እና ስሜት የማይረዳ ከሆነ፣ በተለይም የሥራ ዘርፍን በሚመለከት በሚወሰዱ አንዳንድ አስፈላጊ ውሳኔዎች ላይ መግባባት ከሌለ፣ በጋብቻ ሕይወት ውስጥ የብቸኝነት ወቅት ሊያጋጥም እንደሚችል አስረድተው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለአባቱን ፈቃድ በመተው በጌቴሴማኒ የሚሰቀልበትን መስቀል መቀበሉን አስታውሰዋል። የትዳር ሕይወታቸውን ከጌቴሴማኒ ጋር ያመሳሰሉት አቶ ገብርኤሌ፣ ፍቅራቸው እና የዕለት ምርጫቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚፈተን ቢሆንም በተክሊላቸው ዕለት የገቡትን ቃል ኪዳን በችግር እና በፈተና ጊዜ መታደስ እንደሚገባ እና ለሌሎች ባለ ትዳሮች ዓርዓያ ሆኖ መገኘት እንዳለበት አስረድተዋል።

13 April 2022, 16:23