ፈልግ

በጣሊያን ውስጥ ለታማሚ የሕክምና እርዳታ እየተሰጠ በጣሊያን ውስጥ ለታማሚ የሕክምና እርዳታ እየተሰጠ   (ANSA)

የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት፣ ሐኪሞችን እና የጤና ተንከባካቢዎችን አመሰገኑ

የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የካቲት 2/2014 ዓ. ም ለ30ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን በማስመልከት በአገሩ ለሚገኙት የጤና ባለሙያዎች በሙሉ የምስጋና መልዕክት አስተላልፏል። በጉባኤው ሥር የሚገኝ ሐዋርያዊ የጤና አገልግሎት መምሪያው በመልዕክቱ፣ የጤና ባለሙያዎቹ ከሕሙማኑ ጋር ተባብረው የሕይወት ጥያቄዎችን ለመመለስ በትዕግስት የሚሠሩ መሆናቸውን ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሕክምና አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ ለሚገኙ የጤና ባለሞያዎች ምስጋና፣ እውቅና እና ክብር ሊሰጣቸው እንደሚገባ የገለጸው የመምሪያው መልዕክት፣ እንክብካቤአቸውን በእነዚህ ሁለት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓመታት ብቻ ሳይሆን በቀኑ ሲያበረክቱ ለቆዩት የሕክምና ዶክተሮች እና የጤና ባለሙያዎች በሙሉ አድኖቆትን መግለጽ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል። ዘንድሮ ለ30ኛ ጊዜ የተከበረው ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን ፣ “የሰማይ አባታችሁ መሐሪ እንደ ሆነ እናንተም እንዲሁ መሐሪዎች ሁኑ” (ሉቃ.6:36-38) በሚለው የዘንድሮ መሪ ቃሉ፣ በሕመም ከሚሰቃዩት ጋር በመሆን ዕርዳታን መስጠት እንደሚገባ የሚያሳስብ መሆኑን መምሪያው ገልጾ፣ ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀንም ይህን ለመገንዘብ መልካም አጋጣሚ መሆኑን አስረድቷል።

የአእምሮ ሕመም እና የሕክምናው ውስብስብነት

የዛሬው የጤና አጠባበቅ የሕክምና ባለሞያዎች በስፋት በሚንቀሳቀሱበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መባባሱን የገለጹት ብጹዓን ጳጳሳቱ፣ በተለይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመጣው የቴክኖሎጂ እና የሰው ልጅ የልዩነት ጥያቄ አጽንዖት ሰጥተዋል። ጳጳሳቱ አክለውም፣ ክልላዊ ልዩነቶች፣ በአገራችን እና በሌላው የዓለማችን ክፍሎች መካከል ክፍተቶችን በመፍጠር፣ አቅመ ደካማነታቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው ያደረጋቸው መሆኑን ገልጸው፣ ከሁሉም በላይ የሕክምና አገልግሎትን በነፃ የማግኘት መብት ያላቸውም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

ሰብዓዊ ክብርን የማሳነስ አደጋዎች

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አቅመ ደካማነታችንን እንድንገነዘብ አድርጎናል ያሉት የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት፣ ያስገነዘበን ይህን ብቻ ሳይሆን በሥነ-ፍጥረታዊ እና ሰብዓዊ መዋደድ፣ በአዲስ ፍቅር ከሕይወት ጋር መተሳሰር እንዳለብን አስተምሮናል ካሉ በኋላ፣ ለዚህም የጤና ባለሙያዎች የምስክርነት ሚና በተግባር የታየበት እንደሆነ አስረድተዋል። ጳጳሳቱ በሕክምና ዶክተሮች እና በጤና ባለሙያዎች ላይ የሚደርሰውን "የማያቋርጥ የጥቃት ድርጊቶችን" መመልከት ያሳምማል ብለው፣ ተጠያቂ በማይሆኑበት ጉዳይ በኩል ጥቃት የሚደርስባቸው ከሆነ እና ይህም ከሰው ልጅ ባሕሪ ጋር የሚገናኝ ከሆነው፣ የሰውን ውስንነት የሚገልጽ የተሳሳተ መንገድ መሆኑን ገልጸው፣ በመጨረሻም አሳሳቢ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ እያደገ የመጣው የቢሮክራሲ ሥራ ሰብአዊ ክብርን ሊያሳጣው እንደሚችል አስረድተዋል።

ከሕመሙ በላይ ተስፋን ማድረግ ይስፈልጋል

ተስፋን ማድረግ እና በእግዚአብሔር መታመን በሕክምና ዶክተሮች እና በጤና ባለሙያዎች ሥራ መካከል የሚገኙ ሁለት ቋሚ መመሪያዎች መሆናቸው ተገልጿል። ተስፋ ማድረግ ዛሬ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ወጣቶች ራሳቸውን ለሙያው አሳልፈው በመሰጠት፣ መልካም ነገርን ለመሥራት ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም መሻሻል በሚታይባቸው ሁኔታዎች ላይ ተስፋን በማድረግ ላይ መሆናቸው ተገልጿል። ሐዋርያዊ የጤና አገልግሎት መምሪያው በምስጋና መልዕክቱ፣ ሐኪሞች የጤና፣ የውበት፣ የተስፋ እና የእንክብካቤ ቅዱሳን ምሳሌዎች መሆናቸውን ገልጾ፣ ሕመም ብዙውን ጊዜ ከሥጋዊ ጉዳት ይልቅ መንፈሳዊ ጉዳትን ስለምያስከትል ከሕክምና ዶክተሮች እና ታካሚዎች ጎን ለጎን ነፍስን በመንከባከብ የሚተባበሩ መንፈሳዊ አገልጋዮች እና ካህናት መኖራቸው አስፈላጊ እንደሆነ፣ ሕሙማን እንደ በሽተኛ ተቆጥረው ሰብዓዊ ማንነታቸው እንዳይቀንስ እና ክብራቸው መጠበቅ እንዳለበት አሳስቧል።

10 February 2022, 16:15