ፈልግ

ሰፊው መንገድና ጠባቡ መንገድ ሰፊው መንገድና ጠባቡ መንገድ  (AFP or licensors)

ሰፊው መንገድና ጠባቡ መንገድ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በጠባቧ በር ግቡ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚያሰገባው በር ሰፊ ወደ ጥፋት የሚያደርስ መንገድ ሰፊ ነው፣ ወደዚያ የሚገቡትም ሰዎች ብዙዎች ናቸው። ወደ ሕይወት የምታስገባው መንገድ ጠባብ ናት፣ መንገዷም አስቸጋሪ ናት። እራሷን የሚያገኙዋትም ጥቂቆች ናቸው” (ማቴ 7፡13) እያለ ይህችን ጠባብ መንገድ እንድንከተል ያበረታታናል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን  

ሰፊው መንገድ የዓለም ሲሆን ጠባብ ግን የእግዚአብሔር ነው፣ ፊተኛው መንገድ የኃጢአት በመሆኑ ወደ ገሃነመ እሳት ይወስዳል። ኋለኛይቱ መንገድ ግን የጽድቅ መንገድ ነች፣ ወደ መንግሥተ ሰማያትም ታደርሳለች። ሰፊው መንገድ ለጊዜው አመቺ ቢሆንም በመጨረሻም ግን መጥፎ ነው፣ ጠባቧ ግን ለጊዜው አስቸጋሪ ብትሆንም በመጨረሻ ግን አመቺና ደስ የምትል ይሆናል።

ሰፊው መንገድ ወደ ዓለም ይመራናል፣ እንደ ፈቃዳችን ለመሄድ ነጻነት ይሰጠናል፣ የሥጋችን ምኞትና ፍላጐት እንድንፈጽም በጊዜያዊ ምቾት እንድንፈነጥዝ ያደረግናል። ይህን መንገድ ከያዝን ከዓለም ሌላ ምንም አንፈልግም። ስለሆነም የሕይወታችን ዋና ሐሳብ “እንብላ፣ እንጠጣ፣ ሀብታሞች እንሁን፣ ተመችቶን እንኑር፣ እንጫወት፣ እንቀልድ … ብቻ” ይሆናል። ምድራዊ ነገር እንጂ መንፈሳዊ ነገር አናውቅም። ይኸውም ምድራውያን ነን ብለን ስለምናስብ ነው። መንፈሳዊ ነገር ከዚህ ዓይነት መንገድ አይስማማም፣ ሁለቱ ነገሮች እንደሞትና ሕይወት እንደጨለማና ብርሃን የተለያዩ ናቸው። የዚህ መንገድ መጨረሻ ዘለዓለማዊ ሞትና የሰይጣን መንፈስ ተገዢ መሆን ነው።

ጠባቧ መንገድ አስጨንቃ ትይዘናለች። ከእኛ ፈቃድ ይልቅ የአምላክን ፈቃድን እንድንወድ ታደርገናለች። የእግዚአብሔር መንፈስ ታሳድርብናለች። የደኀንነትን መንገድ ትገልጽልናለች። ይህችን መንገድ ከተከተልን ሰማያዊ ነገር ይስበናል መንፈሳውያን እንሆናለን፣ ስለ አምላክ ክብርና ስለ ነፍሳችን ደኀንነት ነፍሳችን በመላ ኃይላችን እንጥራለን። ከኃጢአት ከዓለም መንፈስ እንርቃለን። ይህቺን መንገድ ስንይዝ የዓለምን ከንቱነት ተረድተን እንንቀዋለን። ከምድራዊ ፍቅር ሰማያዊ ፍቅር ይስበናል። ይህ ሰማያዊ ፍቅር ደግሞ ሕይወትችንን ይለውጠዋል። ጠባቡ መንገድ ሥጋችንን እንደምንቀጣና እንደምናሸንፍ ከነፍሳችን በታች እንደምናደርጋት ታደርገናለች፣ ወደ ቅድስና ትወስደናለች።

በሰፊዋ መንገድ የሚሄድ ብዙዎች ናቸው፡፡ በጠባቧ መንገድ የሚጓዙ ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሰፊውን መንገድ የሚይዙ የዓለም ልጆች ናቸው፣ የኃጢአት ኑሮ ደስ የሚላቸው ናቸው፡፡ ሰይጣንን የሚከተሉ ጽድቅን ግን የሚጠሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ጠባቧን መንገድ የሚይዙ ግን የጽድቅ ወዳጆችና የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፣ እነዚህ በእውነት በመንፈስ አስተዋዮች ናቸው፡፡ እነዚያ ግን ሞኞች ናቸው፡፡ ሰፊዋን መንገድ የሚከተሉ ለጊዜው እንደለጐታቸው ቢሄዱም የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ቢያገኙ በውስጣቸው ግን ሰላም የላቸውም፡፡ ሀልጊዜ የመንፈስ መረሰሽና የሕሊና ወቀሳ ይሰማቸዋል፡፡ ኑሮዋቸው እሾክ የሞላበትና ከባድ ሆኖ ይታያቸዋል፡፡ በጠባቧ መንገድ የሚጓዙ ግን  በውጪ እንኳን ችግርና ስቃይ ቢያገኛቸውም በውስጣቸው ግን ደስተኞች ናቸው፡፡ ለሁሉም ጭንቃቸውን ታግሰው ይሸከሙታል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ብለው ይቀበሉታል፣ ሁልጊዜ በዚያች ጠባብ መንገድ ቀጥ ብለው ይጓዛሉ፡፡

ሰፊዋ መንገድ ጠማማና ጨለማ የኩነኔም መንገድ ናት፣ ጠባቧ መንገድ ግን ቀጥተኛና የበራች ናት፡፡ የሰማይ መንገድ ናት፣ ኢየሱስ የመጀመሪያዋን ትተን ሁለተኛይቱን እንድንይዝ ይማጸነናል፡፡ እንስማው፤ መዳን የምንፈልግ ከሆነ በጠባቧ መንገድ እንከተል።

28 January 2022, 13:07