ፈልግ

የሶርያ ክርስቲያኖች አስቸኳይ እርዳታ በመጠየቅ ላይ መሆናቸው ተገለጸ

በሶርያ ውስጥ የከለዳዊያን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ካህን የሆኑት ክቡር አባ ኒዳል አብደል ማሲ ቶማስ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በሰሜን ምስራቅ ሶርያ ያለው ሁኔታ በርካታ ክርስቲያኖችን ለስደት መዳረጉን አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሰሜን ሶርያ ግዛት የሆነው የጃዚራ ግዛት ከቱርክ እና ከኢራቅ ጋር የሚዋሰን ሲሆን አካባቢው በስፋት በኩርድ ኃይሎች ቁጥጥር የሚገኝ መሆኑ ታውቋል። በግዛቱ የሚኖሩ በቁጥር በርካታ አሦራውያን ክርስቲያኖች አካባቢያቸውን ለቀው መሰደዳቸው ክቡር አባ አብደል ማሲ ቶማስ ገልጸዋል። በግዛቲቱ በሚገኙ 38 መንደሮች ውስጥ ብዙ ቤተክርስቲያኖች መኖራቸው ቢታወቅም፣ በርካታ ክርስቲያኖች ከመንደሮቹ በመሰደዳቸው ምክንያት ባሁኑ ጊዜ ሁለት ቁምስኖዎች ብቻ አገልክሎት በመስጠት ላይ መሆናቸው ታውቋል። ከጦርነቱ በፊት በግዛቲቱ ይኖሩ ከነበሩ 21,000 የሶርያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መካከል ዛሬ  800 ብቻ መቅረታቸው ታውቋል።

የስደቱ ምክንያቶች

በርካታ ክርስቲያኖች የሰሜን ሶርያ ግዛት የሆነችውን የጃዚራ ግዛት ለቅቀው መውጣት የጀመሩት ከአራት ዓመት በፊት የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂ ኃይል 150 ክርስቲያኖችን፣ ከእነዚህ መካከል አምስት የከለዳዊያን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን አግተው በመወሰዳቸው ምክንያት መሆኑ ታውቋል። ክርስቲያኖቹን ካገቷቸው ከ15 ቀናት በኋላ አሸባሪዎቹ የገንዘብ ክፍያን የጠየቁ ሲሆን፣ ክፍያው ባለመፈጸሙ ከታጋቾቹ መካከል ሶስቱ ላይ ግድያ እንደተፈጸመባቸው የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል መሰራጨቱ ይታወሳል። ይኸው የቪዲዮ መልዕክት፣ የከለዳውያን ቤተሰብ አባል የሆኑትን ጨምሮ ሌሎች ሦስት ታጋቾች ለከለዳውያን ሃይማኖታዊ መሪዎች ገንዘብ እንዲከፍሉ በማለት መጠየቃቸው ይታወሳል። የጠየቁት ገንዘብ ተከፍሎላቸው ታግተው ከቆዩት 147 ክርስቲያኖች መካከል 146ቱ ሲለቀቁ አንዷ እናት ለጋብቻ ተመርጣ ከአጋቾቹ ጋር እንድትቆይ መገደዷ ይታወሳል።

ገንዘብ የሚገኝበት የአፈና ተግባር መስፋፋቱ

አሸባሪ እስላማዊ ታጣቂዎች ከጃዚራ ግዛት ክርስቲያኖችን እያገቱ መውሰድ መጀመራቸውን ተከትሎ 80 ከመቶ የሚደርሱ ክርስቲያኖች አካባቢያቸውን ለቅቀው ወደ ጎረበት አገር ሊባኖስ መሰደዳቸው ታውቋል። በሰሜን ሶርያ ጃዚራ ግዛት ውስጥ ክርስቲያኖችን ማገት ከፍተኛ ገንዘብ የሚገኝበት ሥራ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት ክብር አባ ክቡር አባ ኒዳል አብደል ማሲ ቶማስ፣ አጋቾቹ አል-ሃሳካ ከተባለች ሌላ መንደርም ክርስቲያኖችን አግተው በመውሰዳቸው ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘታቸውን ገልጸው፣ በወቅቱ በክልሉ ውስጥ ካሉት ተዋጊዎች መካከል አንዳቸውም ክርስቲያኖችን ኵጥቃት መከላከል እንደማይችሉ አባ ኒዳል አብደል ማሲ ቶማስ ገልጸው፣ በዚህ ምክንያት በርካታ ክርስቲያኖች መኖሪያ አካባቢያቸውን ትተው መሄድ መጀመራቸውን አስረድተዋል።

በሰሜኑ የሶርያ ግዛቶች ዛሬ ልዩ ልዩ የጦር ኃይሎች መኖራቸውን የገለጹት ከቡር አባ ኒዳል አብደል ማሲ ቶማስ፣ ከነዚህም ውስጥ ከድንበር አካባቢ መሬትን የተቆጣጠረው የቱርክ ጦር ኃይል፣ የኢራን ደጋፊ ሂዝቦላህ ተዋጊ ቡድን፣ አንዳንድ የፈረንሳይ እና የኢራን ወታደሮች፣ ሩሲያ አጋሩ የሆነችለት የሶርያ ጦር እና በአሜሪካ ጦር የሚደገፉት ኩርዶች እንደሚገኙ፣ የኩርድ ኃይሎች ከኢራቅ አዋሳኝ አካባቢ የሚገኘውን የነዳጅ ፋብሪካዎችን መቆጣጠራቸውን አስረድተዋል። በዚህ አውድም አንዳንድ ክርስቲያናዊ ቡድኖች ከኩርዶች ጋር ሲተባበሩ ሌሎቹ ደግሞ ከሶርያ ጦር ጋር ማበራቸው ታውቋል። 

ይህም ክርስቲያኖች አንዱ ሌላውን ይደግፋሉ በማለት የጥቃት ኢላማ ስለሚያደርጋቸው በአካባቢው ለመቆየት የበለጠ አስቸጋሪ እንደሚሆን ክቡር አባ ቶማስ ገልጸው፣ ከዚህ በተጨማሪም የኩርድ ታጣቂ ሃይሎች አቅማቸውን ለማሳደግ ወጣቶችን ከክርስቲያኖች መካከል በመመልመል ላይ መሆናቸውን ክቡር አባ ቶማስ አክለው አስረድተዋል።

ከአሥሩ መካከል ሰባቱ ለስደት ተጋልጠዋል

በሰሜን ምስራቅ ሶርያ በጃዚራ ግዛት እና በሌሎችም የአገሪቱ ግዛቶች ሕይወት ለክርስቲያኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበደ በመምጣቱ በአአካባቢው ከሚገኙ ከአሥሩ መካከል ሰባቱ ለስደት መጋለጡ ታውቋል። ጦርነቱ ባልተጠናቀቀባቸው የሶርያ ክልሎች ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ሕይወት የተወሳሰበ መሆኑ ሲነገር፣ በውጭ ከሚኖሩ የቤተሰብ አባላት የሚላክ ገንዘብም እንደሚያዝባቸው፣ የገንዘብ ዕርዳታው በሥራ እጦት ለሚቸገር ቤተሰብን እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም ማግኘት እንደማይችሉ ታውቋል።   

21 December 2021, 16:39