ፈልግ

በአሜሪካ ውስጥ የአየር ጣቢያ ሰልፍ በአሜሪካ ውስጥ የአየር ጣቢያ ሰልፍ  

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስደትን ቢቀንስም ያላገደው መሆኑ ተገለጸ

የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በአገሩ ዜጎች ላይ የሚደርስ ስደትን አስመልክቶ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የስደት ጉዞን ቢቀንስም ነገር ግን እንዳላስቆመው ገለጿል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በውጭ አገራት የሚኖሩ ወጣት ጣሊያን ዜጎች ጉዳይ ቤተክርስቲያንን ያሳሰባት መሆኑን ብጹዕ አቡነ ፐሬጎ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ስደትን አስመልክቶ በጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የስደተኞች መምሪያ እየታተመ የሚወጣ ዓመታዊ ሪፖርት፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በማያያዝ ዘንድሮ ባወጣው ሪፖርቱ፣ በውጭ አገራት የሚኖሩ ጣሊያን ዜጎች ሕይወትን መመልከቱ ታውቋል። ዓመታዊ ሪፖርቱ እንዳስታወቀው፣ ወረርሽኙ በተሰራጨባችው ዓመታት ውስጥ አገራቸውን ለቀው የተሰደዱ የጣሊያን ዜጎች ቁጥር ቢቀንስም ያልተገታ መሆኑን አስታውቋል። በዚህም መሠረት እ. አ. አ 2020 ዓ. ም. አገራቸውን ለቀው ወደ አውሮፓ አገራት የተሰደዱ ጣሊያን ዜጎች ቁጥር 109,000 መሆኑን ሪፖርቱ አስታውቋል። እንደ ዓመታዊ ሪፖርቱ ገለጻ መሠረት፣ ጣሊያንን ለቅቀው የሚወጡ ሰዎች በዕውቀት ያደጉ ብቻ ሳይሆን በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እና በትምህርታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ መሆናቸው ታውቋል። የዜጎቹ ስደት ዋና ምክንያት እ. አ. አ ከ2007 – 2012 ዓ. ም. ድረስ ጣሊያንን ያጋጠማት ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ መሆኑን ሪፖርቱ አስታውቋል። የስደተኞችን ሕይወት በጥልቀት የተመለከቱት የሪፖርቱ አዘጋጅ ወ/ሮ ዴልፊና ሊካታ እንደገለጹት፣ የተማሩ የጣሊያን ወጣት ዜጎች ወደ ውጭ አገራት የሚሰደዱበት ምክንያት፣ ከፍተኛ ክፍያ ያለው የሥራ ዕድል ፍለጋ መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህ በተጨማሪም የሚወዱትን የሥራ ዓይነት በተማሩት የትምህርት ዓይነት በመታገዝ ተግባራዊ ለማድረግ ካላቸው ጥልቅ ፍላጎት የተነሳ መሆኑን አስረድተዋል።

በዘንድሮ የክረምት ወራት የታየው የስደተኛ ብዛት

በውጭ አገራት የሚኖሩ የጣሊያን ዜጎች ቁጥር አስመልክቶ የወጣው ሪፖርት፣ እ. አ. አ ጥር ወር 2021 ዓ. ም. የጣሊያን ስደተኞች ቁጥር ከ5.6 ሚሊዮን በላይ መሆኑን ገልጾ፣ ይህ ቁጥር ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ሦስት ከመቶ አድጎ መገኘቱን በጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የስደተኞች መምሪያ አስታውቋል። መምሪያው አክሎም ከአገር ውጭ የሚገኝ የጣሊያን ዜጎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አስታውቋል። በውጭ አገራት የሚኖሩ ጣሊያናዊ ዜጎች ቁጥር በጣሊያን ውስጥ ከሚገኙ የሌሎች አገራት ስደተኞች ጋር እኩል መሆኑን ያገለጸው ሪፖርቱ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጣሊያን ውስጥ በሚገኙ የአገሪቱ ዜጎች እና በውጭ አገር ዜጎች ላይ ለውጥ ማስከተሉን አስታውቋል። በጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የስደተኞች መምሪያ ፕሬዚደትን የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጃን ካርሎ ፐሬጎ፣ በጣሊያን ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞች ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱ ምክንያት ከጣሊያን የሚሰደዱ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥርን ሊተካ አለመቻሉን አስረድተዋል። በራስ ጉዳይ ላይ ብቻ ከማትኮር ይልቅ ሌሎችንም ማሰብ እና ማካተት እንደሚገባ ያሳሰቡት ብጹዕ አቡነ ጃን ካርሎ ፐሬጎ፣ ስለ ጋራ ሰብዓዊ መብት፣ ዕድሎች እና ዜግነት ጉዳይ መወያየት ያስፈልጋል ብልዋል።

በደቡብ ጣሊያን ችግሩ እጥፍ ነው

በጣሊያን ውስጥ የሚታየውን የዜጎች ስደት በቅርበት የተከታተሉት የዓመታዊ ሪፖርት አዘጋጅ ወ/ሮ ዴልፊና ሊካታ፣ ከጣሊያን የሚሰደዱ ሰዎች ማን እና ከየትኛው የአገሪቱ ክፍሎች እንደሆነ ሲገልጹ፣ ከጣሊያን የሚሰደዱት ዕድሜአቸው ከ18 – 34 የሆናቸው እንደሆኑ ገልጸው፣ ከእነዚህም መካከል 78 ከመቶ በላይ ወደ ጎረቤት የአውሮፓ አገራት እንደሚሰደዱ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ የመጨረሻዎቹ ዓመታት መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ የጣሊያን ዜጎች ከሚሄዱባቸው 180 የመዳረሻ አገራት መካከል የመጀመሪያዎቹ አሥሩ የአውሮፓ አገራት መሆናቸውን ገልጸዋል። በጣሊያን ውስጥ ከፍተኛ የሰዎች መሰደድ የተመዘገበው በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል መሆኑን ገልጸው፣ የአገር ውስጥ እንቅስቃሴን የተመለከቱ እንደሆነ ብዛት ያለው የሰው ቁጥር ወደ ሰሜኑ የአገርቱ ክፍል እንደሚሄድ እና ከዚያም ወደ ሌሎች አገራት እንደሚሰደዱ አስረድተዋል።      

የወጣቶች ጉዳይ ቤተክርስቲያንን አሳስቧታል

በጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የስደተኞች መምሪያ ፕሬዚደትን የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጃን ካርሎ ፐሬጎ፣ ከጣሊያን ተሰደው በውጭ አገራት ሥራን በቀላሉ ማግኘት ከሚችሉ እና በዕውቀት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ሌላ፣ በአገር ውስጥ የሚገኙ እና በዝቅተኛ የዕውቀት እና የሞያ ደረጃ ላይ የሚገኙ በቁጥር በርካታ ወጣቶች መኖራቸውን አስረድተው፣ በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ትላልቅ ከተሞች በመሄድ በሕገወጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችም ቤተክርስቲያንን የሚያሳስባት ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ አቡነ ጃን ካርሎ በመጨረሻም አደንዛዥ ዕፅ የሚያዘወትሩ እና ሕገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ የሚያዙ በርካታ የጣሊያን ወጣቶች በብሪታንያ እስር ቤት ውስጥ መኖራቸውን እንደ ምሳሌ ጠቅሰው፣ በውጭ አገራት የሚኖሩ ወጣት የጣሊያን ዜጎች በብዙ ችግሮች ውስጥ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

10 November 2021, 14:39