ፈልግ

5ኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በአሲሲ ከተማ  5ኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በአሲሲ ከተማ  

ሕይወት በእግዚአብሔር ዕርዳታ ሊለወጥ እንደሚችል ተገለጸ

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የነበረች ወጣት ጄኒፈር፣ ሕይወቷ በእግዚአብሔር ዕርዳታ ሊለወጥ መቻሉን ገለጸች። በትውልድ ናይጄሪያዊት ወጣት ጄኒፈር የ23 ዓመት ወጣት ስትሆን፣ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞች እጅ በመውደቅ መጀመሪያ ወደ ጣሊያን፣ ቀጥሎም ወደ ፈረንሳይ መወሰዷን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገችው ቆይታ ገላጻለች። ጄኒፈር ከነበረችበት የስቃይ ሕይወት በማምለጥ “ማዴሊን” ፋውንዴሽን በተሰኘ ድርጅት በመታገዝ ከኅብረተሰብ ጋር መቀላቀል መቻሏ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመካከለው ጣሊያን ከተማ አሲሲ፣ ከአውሮፓ አገራት የመጡት ወደ 500 የሚሆኑ ድሃ ማኅበረሰብ፣ ያለፈው ቅዳሜ ኅዳር 3/2014 ዓ. ም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በእመቤታችን ማርያም የመላዕክት ንግሥት ባዚሊካ ውስጥ ተገናኝተው የጋራ ጸሎት ማድረሳቸው እና ከቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ቡራኬን መቀበላቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ባሰቡት ንግግር “ዛሬ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት የሚያበቃበት፣ ሴቶች የሚከበሩበት ጊዜ ነው” በማለት ማሳሰባቸው ይታወሳል። ወጣት ጄኒፈርም በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞች እጅ በመውደቅ አብዛኛው ዕድሜዋን በሴትኛ አዳሪነት ሕይወት መኖሯ ታውቋል። በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ድህነት ሥር መስደዱን የገለጸው የዜና አገልግሎቱ፣ ድህነት ከኢኮኖሚ አንፃር ብቻ የሚታይ ሳይሆን ነፍስን በቀጥታ በመጉዳት የመኖር ፍላጎትን የሚቀንስ መሆኑን አስረድቷል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ እና በሌላ መንገድ የመከራ ሕይወት የሚኖሩ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን በመገንዘብ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. በአሲሲ ከተማ ከልዩ ልዩ የአውሪፓ አገራት ከመጡ 500 ከሚደርሱ ድሃ ማኅበረሰብ ጋር በእመቤታችን ማርያም የመላዕክት ንግሥት ካቴድራል ውስጥ ለጸሎት መሰብሰባቸው ታውቋል።

ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘት

በመካከለኛው የጣሊያን ከተማ አሲሲ በተዘጋጀው የአንድ ቀን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኘች ወጣት ጄኒፈር፣ በዕለቱ በእመቤታችን ማርያም የመላዕክት ንግሥት ባዚሊካ ውስጥ ከተገኙ ድሆች መካከል አንዷ እንደነበረች ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ባዚሊካው ሲደርሱ አቀባበል ካደረጉላቸው ስደተኞች መካከል ጄኒፈር አንዷ ስትሆን በዚህ ወቅት ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ሰላምታ በመለዋወጥ፣ የስቃይ እና የመከራ ሕይወት የሚታይባት ፊቷን በመግለጽ አጭር መልዕክቷን ለቅዱስነታቸው ማድረሷ ተመልክቷል።

ትናንት ጉዳት የደረሰባት፣ ዛሬ ግን ደስተኛ

ወጣት ጄኒፈር ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ባቀረበችው መልዕክት፣ ቅዱስነታቸው ለድሆች በሙሉ አባት መሆናቸዋን ገልጻ ድሆችን ለማግኘት ወደ አሲሲ በመምጣታቸው ምስጋናዋን አቅርባለች። መልዕክቷን በንባብ ያቀረበችው ወጣት ጄኒፈር፣ ስላሳለፈችው ሕይወት ስትገልጽ፣ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞች እጅ መውደቋን፣ ለስምንት ወራት ያህል በሊቢያ ውስጥ መቆየቷን እና በጀልባ ተሳፍራ የሜዲቴራኒያንን ባሕር በማቋረጥ ወደ ጣሊያን መድረሷን እና በጣሊያ ውስጥም ሁለት ዓመት መቀመጧን ገልጻ፣ በአሲሲ በተዘጋጀው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝታ ከቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ቡራኬን ለመቀበል መቻሏ ያስደሰታት መሆኑን አስታውቃለች።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከጄኒፈር ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ፤
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከጄኒፈር ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ፤

ከ“ማዴሊን” ፋውንዴሽን የተገኘ ዕርዳታ       

በፈረንሳይ ውስጥ በሴትኛ አዳሪነት ሕይወት ይኖሩ የነበሩ ሴቶችን ተቀብሎ አዲስ ሕይወት ለማስጀምር ዕርዳታን የሚያደርግ “ማዴሊን” ከሚባል ፋውንዴሽን ዕርዳታ ማግኘቷን ወጣት ጄኒፈር ገልጻለች። ፋውንዴሽኑ መጠለያን፣ ሥራን እና ከሁሉም በላይ በሕይወቷ አጥታው የቆየችውን የእንክብካቤ እና የቸርነት አገልግሎቶችን ማግኘት መቻሏን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት በማከል ገልጻለች። ፋውንዴሽኑ ካደረገላት ዕርዳታ በተጨማሪ በፈረንሳይ ውስጥ በአንድ ቤተሰብ ዘንድ በእንግድነት መቆየቷንም አስረድታለች። ችግር ያጋጠማቸው ሴቶች እምነት ከማጣት የተነሳ ቶሎ ከማኅበረሰቡ ጋር ለመቀላቀል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን የገለጹት የፋውንዴሽኑ ፕሬዚደንት አቶ ኦሊቨር ባኔል፣ ወጣት ጄኒፈር ከድርጅታቸው ጋር ለመተዋወቅ የወሰዳት ጊዜ አጭር መሆኑን ገልጸዋል። 

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ቡራኬ

ሕይወቷ መከራ የበዛበት እንደነበር የገለጸችው ወጣት ጄኒፈር፣ “ዛሬ ግን በእግዚአብሔር ዕርዳታ ሁሉ ነገር ስለተለወጠ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፣ ወደ አገሯ ከመመለስ ይልቅ የእግዚአብሔርን ዕርዳታ መለመን መርጫለሁ” በማለት ለፋውንዴሽኑ ፕሬዚደንት ለአቶ ኦሊቨር ባኔል መናገሯን አስታውሳ፣ በፋውንዴሽኑ ውስጥ ቤተሰባዊ ፍቅር ማግኘቷን አስረድታለች። ወጣት ጄኒፈር ሥራን ለማግኘት የሚያስችላትን የሞያት ትምህርት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መከታተል መጀመሯን ገልጻለች። ወጣት ጄኒፈር በንባብ ያቀረበችውን መልዕክት ካጠቃለለች በኋላ ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቡራኬን መቀበሏ ተመልክቷል። በሥፍራው የነበሩት የፋውንዴሽኑ ሃላፊ አቶ ሮዶልፍ ባሮን በንግግራቸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ድሆችን የሚያጋጥሟቸው በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ደስታን እና ተስፋን ይሰጧቸዋል ብለዋል።

ከመንገድ ውጪ

የ“ማዴሊን” ፋውንዴሽን ፕሬዚደንት የሆኑት አቶ ኦሊቨር ባኔል በበኩላቸው፣ ወጣት ጄኒፈር በማዕከላቸው ስላሳየችው መልካም ስነምግባር እና ልምዶቿ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ወጣቷ ሥራን ማግኘት የሚያስችል የሞያ ትምህርት ባሁኑ ጊዜ በመከታተለ ላይ መሆኑኗን ገልጸው፣ የጄኒፈር ምስክርነት በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞች እጅ ወድቀው፣ መከራ እና ስቃይ በበዛበት የሴትኛ አዳሪነት ሕይወት ውስጥ ለሚገኙት በሙሉ ተስፋን እና ብርታትን የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል። ወጣት ጄኒፈር ከአንድ ዓመት በኋላ ትምህርቷን ስትጨር ሥራ እንደምትቀጠር የገለጹት አቶ ኦሊቨር ባኔል፣ ጄኒፈር ሌሎች በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የወደቁ ሴቶች በማኅበር ተደራጅተው ዕርዳታን እንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኗን ገልጸው፣ በአደጋው የወደቁ ሴቶች ችግር ከፍተኛ ቢሆንም ተስፋ ካልቆረጡ ማሸነፍ የሚቻል መሆኑን አቶ ኦሊቨር ካቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።    

15 November 2021, 15:08