ፈልግ

የኅዳር 5 ቀን 2014 ዓ.ም ዘጽጌ 6ኛ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ የኅዳር 5 ቀን 2014 ዓ.ም ዘጽጌ 6ኛ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ 

የኅዳር 5/2014 ዓ.ም ዘጽጌ 6ኛ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ

የዕለቱ ንብብት

1.    ቆላ 1፥1-11

2.   ያዕ 1፥1-12

3.   ሐዋ.13፥6-15

4.   ማቴ 6፥25-34

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

አለመጨነቅ

“ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ኑሮአችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን? እስቲ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ለመሆኑ ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንዲት ሰዓት መጨመር የሚችል አለን?

“ደግሞስ ስለ ልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? እስቲ የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ ወይም አይፈትሉም። ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ያን ያህል ክብር የነበረው ንጉሥ ሰሎሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዲቱ አልለበሰም። እናንተ እምነት የጐደላችሁ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ በነጋታው እሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር ይህን ያህል ካለበሰ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ? ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት ይጨነቃሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያ ስፈልጓችሁ ያውቃል። ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል። ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና”።

የእለቱ አስተንትኖ

በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች  እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር የዘመነ ጽጌን 6ኛ ሰንበት እናከብራለን። በዚህም ዕለት መልካም ፈቃዱ ሆኖ በቤቱ ሰብሰቦን የቃሉ ተካፋይ እንድንሆን ያደረገን እግዚአብሔር አምላካችን ስሙ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን። በዛሬው ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የሚያስተላልፍልንን መልዕክት ልክ እንደ ወትሮው ሁሉ ወደ ተግባር ለመቀየር እንድንችል ልባችንን ይክፈትልን በቃሉም እንመላለስ ዘንድ መንፈሳችንንም ያነሳሳልን።

ዛሬ በመጀመሪያው ንባብ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስያስ ሰዎች በጻፈው መልእክት ውስጥ የቆላስያስ ሰዎች እርስ በርሳቸው ስላላቸው ፍቅር ስለ እምነታቸው ጠንካራነት ቃሉን በተግባር ለመኖር ስለሚያሳዩት ታታሪነት እግዚአብሔርን ሲያመሰግን ሰምተናል። እነዚህ ሁለቱ መንፈሳዊ እሴቶች ማለትም እምነትና ፍቅር አይነጣጠሉም እውነተኛ  እምነት በፍቅር ይገለጻል እውነተኛ ፍቅርም እንዲሁ ከእውነተኛ እምነት የሚመነጭ ነው ። እግዚአብሔርን የሚወድ ወንድሙንና እህቱን ይወዳል። ለእግዚአብሔር የሚታመን ወንድምና እህቱን ያፈቅራል በእነርሱም ይታመናል። በዐይን የሚታየውን ወንድሙን የሚጠላ በዐይን ያላየውን እግዚአብሔርን ግን እወዳለሁ ወይም አፈቅራለሁ የሚል ሰው  ሐሰት ይናገራል ይላል የመጀመሪያው የዮሐንስ መልእክት 4፥20 ላይ። እግዚአብሔርን መውደዳችን ማረጋገጫው መልካም አስተሳሰባችን ነው ፤ መልካም ሥነ ምግባራችን ነው  ፤ መልካም አካሄዳችን ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ፍቅር ምን መሆኑን ያውቃል ፤ ፍቅር በምን መልኩ እንደሚገለጽ ያውቃል በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ የፍቅር አምላክ የሆነውን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ይመለከታል።

ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ በ2፥14-17 መልእክቱ እንዲህ ይላል  ወንድሞቼ ሆይ  አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው ይችላልን?  አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት  የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ አጥተው ከእናንተ መካከል አንዱ በሰላም ሂዱ አይብረዳችሁ ጥገቡ ቢላቸው ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንዲሁ ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው ይላል። ስለዚህ እውነተኛ እምነት አለኝ የሚል ሰው ሕይወቱ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል።

ዛሬ እያንዳዳችን በውስጣችን ያለው እምነት በየትኛው አቅጣጫ እየተጓዘ መሆኑን ለመረዳት የማንንም አስተያየት መጠየቅ አያስፈልገንም። ስለ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያለንን አመለካከትና ለእነርሱ የምንሰጠው ፍቅር ምን ያህል መሆኑን ሕሊናችንን መፈተሹ ብቻ በቂ ነው። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስያስ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች እምነትና ፍቅር በማየት እግዚአብሔርን አመስግኗል ምክንያቱም እነርሱ እምነታቸው ከቀን ወደ ቀን እየጎለበተ ለቅዱሳኑና በመካከላቸውም ያለ ፍቅር ያለ መተሳሰብና መከባበር እጅጉን እየጨመረ የሚተገብሩት በጎ ተግባር ሁሉ ፍሬ እያፈራ በመሄዱ ነው። ወደ እኛ ህይወት መለስ ብለን ስንመለከት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ዛሬ እኛ ባለን እምነትና ፍቅር እግዚአብሔርን ያመሰግን ይሆን? ልክ በቆላስያስ እንደነበሩት ክርስቲያኖች እምነታችን ከቀን ወደ ቀን እያደገ በመካከላችን ያለ ግንኙነት ይበልጡን እየጎለበተ የምናከናውነው መልካም ተግባር ሁሉ አመርቂ ፍሬ እያፈራ ይገኛልን? በእምነታችን ጠንካሮችና እምነታችንንም በተግባር የምናውለው ከሆነ በእርግጥም እግዚአብሔርን ያመሰግናል ፤ በፍቅር የምንኖር ከሆነ እርስ በርሳችን የምንተሳሰብ ከሆነ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ፤ መልካምነታችንን ለማጎልበት መልካምና አመርቂ ፍሬ ለማፍራት ዘወትር ያለመታከት  የምንጥር ከሆነ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ።

ምን አልባት በእምነታችን ጠንካሮች ካልሆንንና ፤ እምነታችንንም በተግባር የማናውለው ከሆነ መልካም ፍሬ ለማፍራት የማንጥር ከሆነ በመካከላችን ያለን መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የማንተጋ ከሆነ   ዛሬ ነገ ሳንል ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባን ምክሩን ይለግሰናል። በእምነቱ ጠንካራ የሆነ ሰው ፤  እግዚአብሔር በሚሰጠው ጸጋና ኃይል ስለሚመራ ፤ ሕይወቱ ዘወትር የተቀደሰና የተስተካከለ ነው ይህ ደግሞ ለሌሎችም አብነትና መንፈሳዊ ኃይል ሰጪ ነገር ነው።

በሁለተኛው ንባብ ፤ ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ በእምነታችን ጠንካሮች መሆን እንዳለብን ያሰምርበታል። በማቴዎስ ወንጌል በ7፥ 24-27 ላይ ያለውን የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ቃል በአሸዋና በዓለታማ መሠረት ላይ የተሠራውን ቤት እናስተውስ። ዝናብም ወረደ  ፤ ጎርፍም ጎረፈ ፤ ነፋስም ነፈሰ  ያንን ቤት መታው ቤቱ ግን መሠረቱ ዓለት ነበረና ምንም አልሆነም። ነገር ግን ይህንን ቃሌን ሰምቶ በተግባር ላይ የማያውለው ሰው ቤቱን በአሸዋ ላይ የገነባ ሰነፍ ሰውን ይመስላል ዝናብም ወረደ  ፤ ጎርፍም ጎረፈ ፤ ነፋስም ነፈሰ  ያንን ቤት መታው ቤቱም መሠረቱ አሸዋ ነበረና ወዲያውኑ ወደቀ አወዳደቁም እጅግ የከፋ ሆነ።

እንግዲህ ከአሁኑ ጀምረን እምነታችን የተመሠረተው በአሸዋ ላይ ይሁን በዓለት ላይ ልብ ልንለው ይገባል። አንዳንድ ጊዜ መሠረቱ ዓለት ቢሆንም እንኳን ይህ ዓለት ያለ ምንም ውስጣዊ መሰነጣጠቅና መሸርሸር ጸንቶ መቆሙን መከታተልና እንደየሁኔታው አስፈላጊውን ጥገና ልናደርግለት ያስፈልገናል። አብዛኛውን ጊዜ በክርስትና ሕይወት ውስጥ ልብ ልንለው የሚገባን ነገር በመንፈሳዊ አካሄዳችን ጠንክረን ለመገኘትና ወደፊት ለመጓዝ ስናስብ ብዙ እንቅፋቶችና በሰናክሎች ከፊታችን ይደቀናሉ። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በፍጹም ልባችን በፍጹም ሓሳባችን በፍጹም ኃይላችን ለመከተል ስናስብ  እጅግ በጣም ብዙ ፈተናዎች ሊገጥሙን ይችላሉ የሆነ ሆኖ ግን ሁሉንም በትእግስትና በፅናት የምናልፍ ከሆንን አሸናፊዎቹ እኛ ነን አሸናፊ የሆነ ሰው ደግሞ ሽልማትን ይቀበላል ሽልማቱም በዚህ በምድራዊ ኑሮ መቶ እጥፍና በመጪዉም ደግሞ የዘለዓለማዊ ሕይወትን መውረስ ነው፡፡  በማቴዎስ ወንጌል 24፥13 በማርቆስ ወንጌል13፥13 እንዲሁም በሉቃስ ወንጌል 21፥19 ላይ እስከ መጨረሻ የሚፀና እርሱ ግን ይድናል በትዕግስታችሁ ዓለምን ታድናላችሁ የሚለውም ይህንኑ ለማመልከት ነው።

ሌላው ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ የሚነግረን ነገር ቢኖር እግዚአብሔርን ስንለምን ወይንም አንድ ነገር እንዲፈጽምልን ስንጠይቅ አስቀድመን እንደሚያደርግልን ሙሉ በሙሉ እምነታችንን በእርሱ ላይ መጣል ያስፈልጋል። ሙሉ እምነት የታከለበት ልመና መልሱም እንዲሁ የፈጠነ ነው። በማቴዎስ ወንጌል 9፥27 ጀምሮ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን እነዛ ሁለቱ እውሮች እባክህ ራራልን ብለው ሲጠይቁት ምን ዓይነት መልስ እንደሰጣቸው ይተርካል ይህን ማድረግ እንደምችል ታምናላችሁን? አላቸው እነርሱም አዎ እናምናለን አሉ እርሱም እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ አላቸው ወዲያውኑም ተፈወሱ። ዛሬም እኛ የምንሻውን ሁሉ በሙሉ እምነት ከጠየቅነው በሙሉ እምነት እንደሚያደርግልን ከተማመንን እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ይለናል። ስለዚህ በውስጣችን ያለው የእምነታችን ጥንካሬ በሕይወታችን ብዙ ነገሮችን ለመቀየር ዓይነተኛ ሚና ይጫወታልና የእምነታችንን ነገር ችላ ልንለው አይገባም።

ከእግዚኣብሔርና ከወንድም እህቶቻችን ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረን ከፈለግን ለእግዚአብሔርም ሆነ ለወንድም እህቶቻችን ያለንን እውነተኛ ፍቅር በተገቢ መልኩ መግለጽ ከፈለግን እንዲሁም ሁልጊዜ መልካም የሆነ አስተሳሰብ እንዲኖረን ቀና የሆነ አካሄድ እንዲኖረን ከፈለግን በውስጣችን ያለውን እምነት ማሳደግ ይኖርብናል። እግዚአብሔር ከእኛ የሚጠይቀው የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነትን እንዲኖረን ብቻ ነው ምክንያቱም የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነት ቢኖረን ይህንን ታላቅ የሾላ ዛፍ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብንለው እንደሚከናወንልን በሉቃስ ወንጌል 17፥6 ላይ ይናገራል።

በዛሬው በማቴዎስ ወንጌል 6፥25-34 ያለው ስለምትበሉትና ስለምትጠጡት ነገር አትጨነቁ ይለናል። ይህ ማለት ስለ ወደፊት ኑሮአችሁ አታስቡ እቅድ አታውጡ ማለት አይደለም። ወይንም ደግሞ እጃችንን አጣምረን ተቀምጠን እግዚአብሔር የሚያደርገውን ተዓምር እንጠባበቅ ማለት ዓይደለም ነገር ግን በሚቻለን ሁሉ እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋና ጥበብ እንዲሁም ዕውቀት እየሠራን እንድንኖር ነው። ለሠራተኛ ደሞዝ የስፈልገዋለና ከምንሠራው ሥራችን ደግሞ የዕለት እንጀራችንን እናገኛለን።

የዛሬ ወንጌል እንደ ምሳሌ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ ብሎ አስቀምጦልናል ፤ እነርሱ እርግጥ ነው አይዘሩም አያጭዱም ፤ ሰብስበውም በጎተራ አይከቱም ነገር ግን የሰማይ አባታቸው ይመግባቸዋል ይላል እንጂ እግዚአብሔር የሚበሉትን ጥራጥሬ ከሚኖሩበት ከጎጇቸው ድረስ ሄዶ ያድላቸዋል አይልም። እነዚህ ወፎችም ቢሆኑ የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት እግዚአብሔር የሚያዘጋጅላቸውን ለመልቀም ከቦታ ቦታ መዘዋወር አለባቸው።

እንዲሁም እኛ በተመሳሳይ መልኩ የእለት ምግባችንን ለማግኘት መትከል መኮትኮት ውኃ ማጠጣት ያስፈልገናል ፤ እግዚአብሔር በሰጠን በየትኛውም የሥራ መስክ ተሰልፈን ልንሠራ ይገባናል በተገቢ መልኩ እግዚአብሔር በቸረን አቅምና ችሎታ መንቀሳቀስ ያስፈልገናል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሲናገር ፤ አባቴ ይሠራል እኔም እሠራለሁ ይላል ፤ ሐዋርያቶችም ይሠሩ እንደነበር በተሰሎንቄ መልእክት አይተናል ፤ ስለዚህ እኛም የዕለት ጉርሳችንን ለማግኘት ሥራን መሥራት ግድ ይለናል። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ መልዕክቱ እንዲህ ሲል ያዛል ፤ ሊሠራ የማይወድ አይብላ ፤ እኛም ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖር ነበር 2ተሰሎንቄ 3፥10

ብዙውን ጊዜ ሥራ መሥራት በአዳምና በሔዋን ኃጢአያት ምክንያት ለሰው ልጅ የተሰጠ እዳ ተደርጎ ሲቆጠር ይስተዋላል ፤ ነገር ግን እውነታው ይህ አይደለም ፤ አዳምና ሔዋን በኤደን ገነት ሥራ ይሠሩ እንደነበር በኦሪት ዘፍጥረት 2፥15 ላይ ይገልጻል “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ማለትም አዳምና ሔዋንን ወስዶ ያበጁትም ይጠብቁትም ዘንድ በኤደን ገነት አኖራቸው” ይለናል። ስለዚህ ሥራ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠው ልዩ ፀጋ ነውና ፤ ሁላችን የየድርሻችንንና የየአቅማችንን እንድንሠራ በላባችንም እንድንበላ ያስፈልጋል።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ የሚያዘን ፤ ጭንቀትን እንድናስወግድና በቅድሚያ የእግዚአብሔርን ጽድቅ እንድንፈልግ እንጂ ፤ ሥራ ከመሥራት እንድንቆጠብ አይደለም እጃችንን አጣጥፈን እንድንቀመጥና እግዚአብሔር በተዓምር እንዲመግበን እርሱን ብቻ እንድንጠብቅ አይደለም። እርግጥ ነው እግዚአብሔር ለሰው ልጅ አእምሮን ሰጥቶታል ስለዚህ በዚህ በተሰጠው አእምሮ ተጠቅሞ ምን ማድረግ እንዳለበትና እንደሌለበት ሊረዳ ያስፈልጋል ተጠያቂነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ኃላፊነቱን በሚገባ ሊወጣ ይገባል። እያንዳንዱ ሰው በየዕለቱ ከእግዚአብሔርና ከወንድም እህቶቹ ጋር ያለውን ግንኙነት በመገምገም ማስተካከል ያለበትን በማስተካከል ቆርጦ መጣል ያለበትን ቆርጦ በመጣል ማሳደግ ያለበትን ይበልጥ በማሳደግ በዕለታዊ ሕይወቱ ደስተኛ ሆኖ እንዲኖር ይገባል። እግዚአብሔርም በዚህ መልኩ ወደ እርሱ የሚቀርቡትን በሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ገና ሳይጠይቁት አስቀድሞ ያከናውንላቸዋል። የእግዚአብሔር ጸጋ ፤ የእግዚአብሔር ጽድቅ በመካከላችን ካለ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ አስቀድሞ ያውቃልና በሙላት ይሰጠናል። ይህም ደግሞ ካላስፈላጊ ጭንቀትና ውጥረት ይታደገናል። ሰው ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረው መልካም ግንኙነት እንጂ በራሱ በመጨነቅና በመጠበብ ምንም የሚጨምረው የሚቀይረውም ነገር አይኖረዉም።

ምን አልባት ሰው ከመጠን በላይ በመጨነቅ የሚያሻሽለው ነገር ባይኖርም ፤ የሚያባብሰው ነገር ግን አለ ፤ ይኸውም ክፉ ሀሳብን ፣ ተስፋ መቁረጥን ብስጭትን ንዴትንና ኃዘንን ይጨምራል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ፤ ሰውን ወደ አላስፈላጊ ህመምና ወደ ሞት ይወስዳሉ ፤ በዕለታዊ የኑሮው እንቅስቃሴ ብቻም ሳይሆን በእምነቱም ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድራሉ። ስለዚህ ከሁሉ አስቀድመን የእግዚአብሔርን ጽድቅ በመሻት ከእርሱም በምናገኘው ጸጋ ጭንቀትንና አጉል ሓሳብን አስወግደን በተቻለን አቅም ሁሉ በመሥራት ራሳችንንና በዙሪያችን ያሉትን ሁሉ ደስተኛ አድርገን እንድንኖር ያስፈልጋል።

ለዚህም የጭንቅ አማላጅ የሆነችው እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፤ ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጭንቀታችንን ሁሉ የምናራግፍበትና በእርሱ ብቻ ተመክተን መኖር የምንችልበትን ጸጋን ፣ በረከትን፣ ብርታትንና የእምነት መጠንከርን ከአንድያ ልጇ ታሰጠን። የሰማነውን በልባችን ያሳድርልን በልባችን ያደረውን ቃል ደግሞ በዕለታዊ ኑሮአችን ለመተግበር እንድንችል መንፈሳችንን ያነሳሳልን።

 

 

 

 

 

13 November 2021, 11:23