ፈልግ

ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም 

ለመካከለኛው ምስራቅ ቤተክርስቲያናት አዲስ የሐዋርያዊ አገልግሎት መመሪያ መዘጋጀቱ ተገለጸ

በፍልስጤም፣ በእስራኤል፣ በዮርዳኖስ እና በቆጵሮስ የሚገኙ ልዩ ልዩ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናንን የሚያሳትፍ አዲስ ሐዋርያዊ አገልግሎት መመሪያን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ይፋ ማድረጓ ታውቋል። ሐዋርያዊ አገልግሎቱ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮን እና የላቲን ሥርዓተ አምልኮን ለሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን በጋራ የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል። የጋራ ሐዋርያዊ አገልግሎቱ በሚቀርብለት ጥያቄ መሠረት ለአብያተ ክርስቲያናቱ ምዕመናን አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን በማመቻቸት አንዱ የሌላውን ሥርዓተ አምልኮ ወጎችን በማክበር ቅዱስት ምስጢራትን ለመቀበል የሚያስችል ሲሆን፣ አዲሱ የሐዋርያዊ አገልግሎት በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በሚገኙ ካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያን እና በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ወይም ክርስቲያን ማህበረሰቦች ዘንድ ተፈጻሚ እንደሚሆን ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሐዋርያዊ አገልግሎቱ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ውስጥ የሚገኙ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ካህናት እና ሐዋርያዊ አገልጋዮች ቅዱሳት ምስጢራትን መቀበል ፈልገው ጥያቄ ለሚያቀርቡ የምሥራቅ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮን ለሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ምስጢረ ንስሐን፣ ምስጢረ ቁርባን እና ምስጢረ ቀንዲልን ለመቀበል የሚያስችል መሆኑ ታውቋል። እንደዚሁም አንድ ካቶሊካዊ ምዕመን በአካል ሆነ በሥነ ምግባር ችግር ምክንያት ቅዱሳት ምስጢራትን ሳይቀበል የቆየ ከሆነ የምሥራቅ ቤተክርስትያን ሥርዓተ አምልኮን ከሚከተሉ ካህናት ወይም ሐዋርያዊ አገልጋዮች ከላይ የተጠቀሱ ቅዱሳት ምስጢራትን ለመቀበል ጥያቄ ማቅረብ የሚችል መሆኑ ታውቋል። የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናንን በተመለከተ ግን የሞት አደጋ ሲያጋጥማቸው ወይም ከቤተክርስቲያናቸው በኩል ፈጣን የቅዱሳት ምስጢራት አገልግሎቶችን ማግኘት በማይችሉበት ወቅት ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህናት እና አገልጋዮች በኩል ምስጢረ ንስሐን፣ ምስጢረ ቁርባን እና ነፍስ ለዘለዓለማዊ ዕረፍት በተቃረበችበት ወቅት የሚሰጠውን የቅዱስ ቀንዲል ምስጢርን  መስጠት የሚችል መሆኑ ታውቋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ለሚገኙ የምሥራቅ እና የላቲን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚያገለግል አዲሱ የሐዋርያዊ አገልግሎት መመምሪያ በኢየሩሳሌም በሚገኙ የላቲን ሥርዓት አምልኮ ፓትሪያርክ ተዘጋጅቶ በምሥራቅ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጉባኤ መጽደቁ ታውቋል። አዲሱ ሐዋርያዊ መመሪያ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለማበረታታት ለመምራት እና ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያለውን አንድነት ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተገልጿል። በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ፒዬር ባቲስታ ፒዛባላ አዲሱን የሐዋርያዊ አገልግሎት መመሪያን አስመልክተው በጻፉት መልዕክታቸው፣ የሐዋርያዊ አገልግሎት መመሪያዎቹ፣ የክርስቲያናዊ አንድነት ፍለጋ ሕያው አካል መሆናቸውን ገልጸው፣ በየጊዜው የሚታዩ አዳዲስ ክስተቶችን ለመገንዘብ የሚያግዝ እና ይህን በመረዳት በየጊዜው ማሻሻያዎን ለማድረግ የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል።

በቅድስት ሀገር ያለው አንድነት ፍጹም ሊሆን ይገባል

የክርስትና እምነት ምንጭ የሆኑ አካባቢዎች በመካከለኛው ምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ውስጥ የተገለጹ ሲሆን እነርሱም በምሥራቅ ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ፓትሪያርኮች የሚመሩ የአርሜኒያ፣ የሶርያ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት ሲሆኑ ሌሎች የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት፣ በኢየሩሳሌም የሚገኝ የግሪክ ፓትሪያርካዊ ኦርቶዶክስ እና የቆጵሮስ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት መሆናቸው ይታወቃል። የምሥራቅ ካቶሊክ ቤተክርስቲያናትም በኢየሩሳሌም የሚገኝ ፓትሪያርካዊ ቤተክርስቲያን፣ የግሪክ መልቃይት፣ የማሮናይት  ካቶሊክ ቤተክርስቲያን፣ የሶርያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ የአርመን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና የከለዳውያን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሆናቸው ይታወቃል። በቅድስት ሀገር የሚገኙ የአንግሊካን እና የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት እና ክርስቲያናዊ ማህበረሰቦች፣ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን፣ የሉተራን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን እና ልዩ ልዩ የፕሮቴስታንት ተሐድሶ ቤተክርስቲያናት፣ የወንጌላዊያን አንድነት እና የጴንጤቆስጤ ክርስቲያን ማህበረሰቦች መሆናቸው ታውቋል። የእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች የወደፊት ሕልውናቸው በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም እንደሚገኝ የሚያምኑ መሆናቸው ታውቋል።

በዚህ ምክንያት፣ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ማህበረሰቦች መካከል ያለው እውነተኛ አንድነት እና ኅብረት ፍጽም መሆን እንዳለበት አዲሱ የሐዋርያዊ አገልግሎት መመሪያው ገልጿል። የሐዋርያዊ አገልግሎት መመሪያው አክሎም በእምነት እና በቅዱሳት ምስጢራት ሕይወት ያሉ የኅብረት ደረጃዎችን መጋራት እንደሚቻል ገልጿል። በተጨማሪም ምእመናን በቤተክርስቲያን ሕይወት እና ተግባራት አማካይነት እራሳቸውን እንደ ክርስቲያን መግለጽ እንደሚችሉ፣ ካኅናትም በሥርዓተ አምልኮ እና በቅዱሳት ምስጢራት ሕይወት እራሳቸውን መግለጽ እንደሚችሉ እና በአንዳንድ አካባቢዎች የእምነት ማንነትን እንደገና የማረጋገጥ ዝንባሌ ስለሚኖር፣ ይህን ያገናዘበ የአብያተ ክርስቲያን አንድነት እና ኅብረት ግልጽ ሊሆን እንደሚገባ አዲሱ የሐዋርያዊ አገልግሎት መመሪያው ያስረዳል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ሙሉ ግንኙነት አላት ባይባልም በሥርዓተ አምልኮ ሕይወት ውስጥ ላለው የጠበቀ ግንኙነት ትልቅ አክብሮት የምትሰጥ መሆኑ ታውቋል። ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ለሚኖራት ግንኙነት በተለይም ለምስጢረ ጥምቀት እውቅናን የምትሰጥ መሆኑ ይታወቃል። ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሙሉ ግንኙነት ከሌላቸው አብያተ ክርስቲያናት ጋር የምስጢረ ቁርባን ሥርዓትን በጋራ ማክበር ያልተፈቀደ ሲሆን የቅዱስ ቁርባን ምስጢረ የግል ድርጊት ሳይሆን ነገር ግን በአብያተ ክርስቲያናት ወይም በቅዱስ ቁርባን ውስጥ በሚሳተፉት የክርስቲያን ማህበረሰብ መካከል ያለውን እውነተኛ አንድነት የሚያመለክት መሆኑን የሐዋርያዊ አገልግሎት መመሪያው አስረድቷል። አዲሱ የሐዋርያዊ አገልግሎት መመሪያው፣ የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን እምነታቸውን እና የምሥጢረ ሥጋዌ ሕይወታቸውን በሚከተሉት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲለማመዱ ከማበረታታቱ በተጨማሪ፣ ምዕመናን በመንፈሳዊ አስተምህሮ ምክንያት እምነታቸውን እንዲቀይሩ የሚያደርጉ አካሄዶችን ማስወገድ እንደሚገባ ያሳስባል።

የሐዋርያዊ አገልግሎት መመሪያ የተለያዩ ድንጋጌዎች

ከምስራቅ ቤተክርስቲያ ወይም ከኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን ጋር የቅዱሳት ምስጢራት ሕይወትን መጋራት በተመለከተ፣ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን በሥርዓተ አምልኮ ወቅት ቅዱስ ወንጌልን የሚያነበው ካህን ወይም ዲያቆን እንደሆነ፣ በምስጢረ ጥምቀት ሥነ-ሥርዓት ወቅት ብቻ የክርስትና አባት ወይም እናት ቅዱስ ወንጌልን ማንበብ እንደሚችሉ መመሪያው ገልጾ ምዕመናን በመስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባትን ማንበብ የሚችሉ መሆናቸውን አስረድቷል። በተጨማሪም፣ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ውጭ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ወይም በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት መካከል ተግኝቶ ስብከትን ማቅረብ እንደሚፈቀድ የገለጸው የሐዋርያዊ አገልግሎት መመሪያው፣ ከአባት ወይም ከእናት አንዳቸው ካቶሊክ የሆነው የሌላ ቤተ ክርስቲያን ምዕመን በምስጢረ ትምቀት ወቅት ምስክር ሆኖ ሊቀበለው እንደሚችል ገልጿል። የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት አባላት በምስጢረ ተክሊል ወቅት በምስክርነት ሊቀርቡ እንደሚችሉ የሐዋርያዊ አገልግሎት መመሪያው አክሎ አስረድቷል።

የሁለት ወገን ጋብቻ

በሁለት የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን መካከል የሚፈጸም የጋብቻ ወይም የምስጢረ ተክሊል አፈጻጸም በተመለከተ፣ ሁለት ተጋቢዎች ከሚከተሉት ቤተክርስቲያን መሪዎች ፍቃድ እንዲቀርብ የሚያሳስበው መመሪያው፣ ምስጢረ ተክሊልን የሚባርክ አንድ ካኅን ብቻ መሆን እንዳለበት አስታውቋል። ሁለቱ ተጋቢዎች የጋብቻ ሥነ-ሥርዓታቸውን የሚፈጽሙት በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከሆነ መሪ ካህኑ የሌላው ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዲሳተፍ መጋበዝ እንደሚችል፣ ከቅዱስ ወንጌል ንባብ በስተቀር ሌለሎችን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባትን እንዲያነብ እና ለተጋቢዎቹ አጭር ስብከት እና ቡራኬ እንዲሰጥ መጋበዝ እንደሚችል መመሪያው ያስረዳል። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካኅን ወይም ዲያቆን ተገቢውን ጸሎት ማቅረብ፣ የቅዱስ ወንጌል ጥቅሶችን ማንበብ እና አጭር ስብከት ካቀረበ በኋላ ባለትዳሮችን መባረክ እንደሚችል አዲሱ የሐዋርያዊ አገልግሎት መመሪያው ያሳስባል።

11 November 2021, 16:19