ፈልግ

በማሊ ድንበር አካባቢ የሚገኝ የሰሃል ጫካ በማሊ ድንበር አካባቢ የሚገኝ የሰሃል ጫካ 

ጋና፣ የአምስት ዓመት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የተግባር መርሃ ግብር ይፋ አደረገች

የጋና ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እ. አ. አ ከ2022 – 2026 የሚቆይ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የድርጊት መርሃ-ግብርን ይፋ አድርጓል። የኬፕ ኮስት ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቻርልስ ፓልመር-ባከል፣ አስተሳሰብን የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከመበዝበዝ ይልቅ ወደ መንከባከብ እና መጠበቅ ፍላጎት ማዞር አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ አስተምህሮ ተነሳሽነታቸውን የገለጹት  የጋና ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ለጋራ መኖሪያ ምድራችንን የሚደረገውን እንክብካቤ፣ እ. አ. አ ከ2022 እስከ 2026 ለማካሄድ የታቀደውን የ5 ዓመት የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የድርጊት መርሃ-ግብር ማዘጋጀታቸው ታውቋል።

ከዚህም ጋር አያይዘው የድርጊት መርሃ-ግብሩ ከኅዳር 15/2014 ዓ. ም. ጀምሮ ይፋ እንደሚሆን አስታውቀው፣ ይህም የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አምስተኛ ዓመት መታሰቢያ እና ቅዱስነታቸው ለጠየቁት የቃለ ምዕዳናቸው መታሰቢያ የአንድ ዓመት ክብረ በዓል ፍጻሜ ምላሽ ለመስጠት መሆኑን ብጹዓን ጳጳሳቱ አስረድተዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሁሉም ሰው ለትውልድ ያለብንን ኃላፊነት በማስታወስ፣ በጋራ ምድራችን ላይ እያንዣበበ ያለውን የአካባቢ እና ማኅበራዊ ቀውሶች መከላከል እንዳለብን ማሳሰባቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ምዕመናን የጋራ መኖሪያ ምድራችንን የመንከባከብ ኃላፊነታቸውን በተግባር እንዲወጡ መድረክ ማዘጋጀታቸው ይታወሳል።

የጋና ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በቅርቡ ያሳየው ተነሳሽነት፣ ሰባቱን ዓለም አቀፍ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ግቦችን ለማሳካት ያለመ ሲሆን እነርሱም፥ ምድራችን ለምታሰማው የስቃይ ጩሄት ምላሽ መስጠት፣ ሥነ-ምህዳራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮችን ማጤን፣ ዘላቂነት ያለው የአኗኗር ዘይቤዎችን መከተል፣ የሥነ-ምህዳር ትምህርትን ማሳፋፋት፣ ሥነ-ምህዳራዊ መንፈሳዊነትን ማሳደግ እና ማኅበረሰብን የሚያሳትፍ የድርጊት መርሃ-ግቦችን መዘርጋት የሚሉ መሆናቸው ታውቋል።

በጋራ ጥረቶች ውስጥ ሁሉንም ማሳተፍ

በጋና ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መርሃ ግብር አስፈጻሚ እና የኬፕ ኮስት ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቻርልስ ፓልመር-ባከል የብጹዓን ጳጳሳቱን ተነሳሽነት በበላይነት የሚመሩት መሆኑ ታውቋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቻርለስ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የጉባኤያቸው የአምስት ዓመት የድርጊት መርሃ-ግብሩ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በ2015 ዓ. ም. ይፋ ያደረጉትን የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ አስተምህሮን በጋናዊያኑ አስተሳሰብ መሠረት በተግባር ለመተርጎም የሚያስችል እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል። 

ሊቀ ጳጳሱ አክለውም የ5-ዓመት የድርጊት መርሃ ግብራቸው ከቅዱስነታቸው “ውዳሴ ላንተ ይሁን የድርጊት መርሃ ግብር ዓላማዎች ጋር የሚስማማ እና ይህን መርሃ-ግብር በህዝቡ ዘንድ ለማስተዋወቅ፣ “ምድር ከእግዚአብሔር ዘንድ ለሰዎች የተሰጠች ስጦታ እንደሆነች ለማሳወቅ እና እኛ የእግዚአብሔር ስጦታዎችን ለመጠበቅ የተጠራን በመሆናችን፣ የእግዚአብሔር ስጦታን በማክበር እና በመንከባከብ ለትውልድ መትረፉን ማረጋገጥ አለብን ብለዋል።

ለጋራ መኖሪያ ምድራችን የሚደረገውን እንክብካቤን ለማሳደግ የተወጠኑ ሌሎች የድርጊት መርሃ ግብሮች በአገራቸው መዘርጋታቸን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቻርልስ፣ በትምህርት ቤት ልጆች ምድርን ከሚደርስባት አደጋ ለመከላከል ቁርጠኛ አቋም እንዲይዙ የሚያደርግ የአንድ ሳምንት የግንዛቤ ማሳደጊያ ፕሮግራም መካሄዱን ገልጸዋል። እንደዚሁም በመጋቢት ወር 2013 ዓ. ም. በጋና የሚገኙ ሐይማኖታዊ ተቋማት እና ሲቪል ማኅበራት የሚሳተፉበት የአምስት ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን መንግሥት ተግባራዊ ማድረጉን ሊቀ ጳጳሱ አስታውሰዋል።     

የምእመናንን አስተሳሰብ መቀየር

በ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የድርጊት መርሃ ግብር ላይ አንዳንድ ተግዳሮቶች አልጠፉም ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቻርልስ፣ ምድርንና ሀብቷን በዘላቂነት ከመጠቀም እስከ መንከባከብ ባለው ሂደት ላይ “የአስተሳሰብ ለውጥ” መፍጠር ላይ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል። በሰዎች ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ መፍጠር እና ምድርን “ማልማት” እንደ አንድ ጠቃሚ ጉዳይ እንዲመለከቱ ማድረግ እንደሆነ ገልጸው፣ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ማድረግ፣ “የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነች ምድራችን፣ ከእግዚአብሔር እና ከጎረቤቶቻችን፣ በተለይም ከድሃ እና ችግረኛ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር የምንገናኝበት ቤት እንድትሆን ማድረግ ነው” ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ ቻርልስ በማከልም፣ ድህነትን እንደ ምግብ፣ ውሃ እና መጠለያ እጦት ብቻ አድርጎ ከመቁጠር ይልቅ፣ “ድህነት ማለት እግዚአብሔር ለልጆቹ ያለውን መሠረታዊ ግምት ካለመረዳት እና አንዳችን ለአንዳችን እንድንሆን መፈጥራችንን ለማወቅ ቸል ከማለት የሚመጣ ነው" ብለዋል። በመሆኑም የሰዎችን አስተሳሰብ መቀየር ከተፈለገ፣ ተፈጥሮን የተመለከቱ መልካም የምሥራች ማብሰር፣ ስለ ሰው ልጆች መልካም የምሥራችን ማብሰር፣ ስለ ችሎታቸው እና ስለ ስጦታዎቻቸው የሚመሰክሩ ሰዎችን በማዘጋጀት የወንጌልን መልካም ዜና ልንሰብክ ይገባል ብለው፣ እኛ የፍጥረታት ተንከባካቢዎች እንጂ ጌቶች አይደለንም ብለዋል።

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” ዕቅዶችን ለማስፈጸም የሚያግዙ ድርጅቶች

ካርታስ የተባለ ካቶሊካዊ ዕርዳታ ሰጭ ድርጅት፣ ከጋና ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጋር በመተባበር ከ2022 እስከ 2026 ለማካሄድ የታቀደውን የ5 ዓመት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የድርጊት መርሃ-ግብር በማገዝ ላይ መሆኑ ታውቋል። የካሪታስ ጋና ተጠሪ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ዛን አኮሎጎ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንዳስረዱት፣ ካሪታስ ጋና፣ ሰባት የተግባር መርሃ ግብር ዓላማዎችን ወደ ተግባራዊነት ለመተርጎም በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ሥራ በማስተካከል ላይ መሆኑን ገልጸዋል። ድርጅቱ የሚያጋጥሙትን ማህበራዊ እና አካባቢያዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት አዳዲስ የተግባር አቅጣጫዎችን በመቃኘት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል። አቶ ሳሙኤል አክለውም የጋና ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የጀመረው የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የተግባር መርሃ ግብር “በስልታዊ ሐዋርያዊ እቅድ” እና “በተቀናጀ አካሄድ እንደገና ለመገምገም የሚያነሳሳ” እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ የማኅበረሰብ ተሳትፎን ያማከለ ተነሳሽነትን መከተል እንደሚገባ ገልጸዋል። 

23 November 2021, 16:25