ፈልግ

ካርዲናል ግሬሽ፣ የቤተክርስቲያን አባቶች ምዕመናንን ማድመጥ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ፣ ለአሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በላኩት የቪዲዮ መልዕክት፣ በመካሄድ ላይ ባለው የቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ጉዞ ብርታትን ተመኝተው፣ የቤተክርስቲያን አባቶች የምዕመናንን ድምጽ እንዲያዳምጡ አደራ ካሉ በኋላ፣ የቤተክርስቲያን አባቶች መንፈስ ቅዱስ ለቤተክርስቲያን የሚያመለክተውን በግልጽ እንዲናገሩ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ  መልዕክታቸውን የላኩት፣ በባልቲሞር ሜሪላንድ ከተማ ከኅዳር 6 – 9/2014 ዓ. ም. ድረስ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ላካሄዱት የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መሆኑ ታውቋል።

“ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ መንፈሳዊ ጉዞ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ፣ ከምዕመናን የሚቀርቡ ልዩ ልዩ ምስክርነቶችን በመቀበል፣ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች፣ ሀገረ ስብከቶች፣ ቁምስናዎች ወይም መንፈሳዊ ማኅበራት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለውይይት ማዘጋጀታቸው “የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በተግባር እየተገለጸ መሆኑን የሚያረጋግጡ ምልክቶች ናቸው።” ብለዋል።

ለጋራ ቁርጠኝነት የቀረበ የቤተክርስቲያን ስጦታ

የአሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት የቤተክርስቲያን ስጦታዎች መሆናቸውን ለመግለጽ መልካም አጋጣሚን አግኝቻለሁ ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ፣ ይህንም “በጋራ ቁርጠኝነት ለቤተክርስቲያን አብረን ስለምናስብላት ነው” ብለዋል። በኅብረት መጓዝ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በድጋሚ አስታውሰውናል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ግሬሽ፣ “በኅብረት መጓዝ ማለት ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ሕዝቦች በኅብረት የሚጓዙበት እና የእርሱ መልዕክተኞች የሚሆኑበት ውጤታማው መንገድ ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል። በመሆኑም ሲኖዶሳዊነት ማለት ቤተክርስቲያን የሚሆኑበት፣ ለቤተክርስቲያን ሕይወት የሚስማማ ባሕል የሚገኝበት፣ አንድነትን የሚገልጹ እሴቶች፣ የምዕመናን ተሳትፎ እና ተልዕኮ በግልጽ የሚታይበት መሆኑን አስረድተዋል።

የሲኖዶሳዊነት ገጽታዎች

ሰባት የሲኖዶሳዊነት ገጽታዎች መኖራቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ፣ ሲኖዶሳዊነት ሁላችንም ወደ አምላካችን በምንሄድበት የጋራ ጉዞ ላይ መሆናችንን የሚገልጽ፣ በዚህም የጋራ ሰብዓዊነታችን እና በጥምቀት ያገኘነው ክብር የዚህ ጉዞ ዋና መሠረት ይሆናል ብለዋል። ይህን እውነት መሠረት በማድረግ የአንድነት መንገዳችንን እንድንገመግም ተጋብዘናል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ፣ በጥምቀት ጸጋ ያገኘነው ግንኙነት፣ በምእመናን ፣ በገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ ለቤተክርስቲያን አገልግሎት በተሾሙ አገልጋዮች መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ማሰላሰል ያስፈልጋል ብለዋል።

ሲኖዶሳዊነት፣ በሁሉም የውይይት ጊዜያት፣ በውሳኔ አሰጣጥ እና በአስተንትኖ ጊዜያት፣ ማወቅ የምንፈልገው የራሳችንን ፍላጎት እና ምኞት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሆነ የሚረዳን በመሆኑ፣ ዛሬ በዓለማችን ውስጥ የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ በተሻለ መነገድ ለመስማት፣ እርስ በርሳችን መደማመጥ እና መበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሲኖዶሳዊነት፣ “በሁሉም የሕይወት ዘርፎች እያንዳንዱ ምዕመን ከቤተክርስቲያን ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረው በመጋበዝ፣ የማያቋርጥ እና ጠንካራ ጥረት እንድናደርግ ይገፋፋናል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ፣ በመሆኑም የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ከማኅበረሰቡ የተገለሉትን እና ድሆችን ጨምሮ እያንዳንዱ ሰው በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ያለው አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ መጋበዛቸውን ገልጸዋል።

ሲኖዶሳዊነት፣ ምዕመናን እርስ በእርስ እንዲማማሩ እና በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ በማሳተፍ ሁሉንም የማኅበረሰብ አባላት በቅንነት እና በትክክለኛው መንገድ የማዳመጥ ስነ-ምግባርን ለማሳደግ እንደሚፈልግ አስረድተዋል።

ሲኖዶሳዊነት፣ ለኅብረት ጉዞ የማይመቹ ጠንካራ አቋሞችን እና ግቦችን በመተው፣ የውይይት እና የጋራ ውሳኔ አሰጣጥ ባህልን ለማመቻቸት ፈቃደኛ መሆንን እንደሚጠይቅ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ አስረድተዋል።

ሲኖዶሳዊነት፣ እንደዚሁም ኃላፊነትን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ቤተክርስቲያን በወንዶችን፣ በሴቶች፣ በልጆችን እና በቤተሰቦች ላይ የምትፈጥርባቸውን ቁስሎች በሙሉ በትህትና ለመገንዘብ ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል።

በመጨረሻም ሲኖዶሳዊነት፣ ከምንኖርበት ዓለም ጋር ለሚኖረን የወንጌል ተልዕኮ ግንኙነት ግብዣን የሚያቀርብ መሆኑን ገልጸው፣ ዛሬ ለዓለማችን ምን ዓይነት ቤተክርስቲያን ማቅረብ እንደሚያስፈልግ፣ ለኅብረተሰባችን ምን ዓይነት አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለብን፣ እንዴትስ ማከናወን እንዳለብን እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል ብለዋል።

የእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን አስተዋፅዖ ጠቃሚ ነው

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ፣ ለአሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በላኩት መልዕክት፣ የእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን አስተዋፅዖ ጠቃሚ እንደሆነ አስረድተው፣ እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ለሌሎች ቤተክርስቲያናት እና ለዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን የሚያቀርበው ስጦታ እንዳለ ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ፣ በ2ኛው የቫቲካን ጉባኤ አስተያየት መሠረት፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን በመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሳ ተበታትነው ቢገኙም በመንፈስ ቅዱስ አንድ መሆናቸውን አስረድተዋል።

መንጋውን ለመስማት መፍራት አያስፈልግም

የቤተክርስቲያን አባቶች ምዕመናንን ከማድመጥ ወደኋላ ማለት የለባቸውም በማለት የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ግሬሽ፣ የአሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በተጀመረው የቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ሂደት ወቅት ከምዕመናን የሰበሰቡትን አስተያየት ሰነድ እንዲያዘጋጁ በድጋሚ በመጋበዝ አሳስበዋል። ለአሜርካ ካቶሊካዊ ምዕመናን ከዚህ በፊት በላኩት መልዕክት መሠረት፣ ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ መርሆችን በመከተል በሲኖዶሱ ሂደት ለመሳተፍ ያላቸውን ፍላጎት በሙላት እንዲገልጹ አደራ ብለዋል። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ በመጨረሻም የአሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በተለያዩ የሲኖዶሱ ሂደቶች ውስጥ ለሲኖዶሱ ጽሕፈት ቤት ድጋፍ እንዲያደርግ በማሳሰብ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል። 

18 November 2021, 11:53