ፈልግ

የኅዳር 05/2014 ዓ.ም 32ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የኅዳር 05/2014 ዓ.ም 32ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የኅዳር 05/2014 ዓ.ም 32ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“ለእግዚአብሔር እና ባልንጀራ ያለን ፍቅር በተጨባጭ ሊታይ ይገባል!”

የእለቱ ምንባባት

1.      ዘዳግም 6፡2-6

2.    መዝሙር 17

3.    ዕብራዊያን 7፡23-28

4.    ማርቆስ 12፡28-34

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ

ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ ሲከራከሩ ሰማቸው፤ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠቱን አስተውሎ፣ “ለመሆኑ ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’ ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።’ ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።”

ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፣ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።”

ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፣ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ከማር. 12፡ 28-34 ተወስዶ የተነበበው የዛሬው ቅዱስ ወንጌል፣ ከሙሴ ሕግ መምህራን መካከል አንዱ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ከሁሉ የሚበልጥ ትዕዛዝ የትኛው ነው?” በማለት ያቀረበውን ጥያቄ ያስታውሰናል። (ማር. 12፡28)  ኢየሱስም ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጥቀስ የሚከተለውን መልስ በመስጠት ያረጋግጣል፥ ከሁሉ የሚበልጥ የመጀመሪያው ትዕዛዝ እግዚአብሔር አምላክህን ውደድ የሚል ነው። ከዚህም የሚቀጥል ሁለተኛው ትዕዛዝ ሰውን ሁሉ እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ የሚል ነው፤ (የማር. 12፡ 29-31) የሙሴ ሕግ መምህር የኢየሱስን መልስ በሰማ ጊዜ፣ ራሱን ትክክል እንደሆነ ብቻ ሳይሆን፣ ይህን አድርጎ በመገኘቱ ትክክል መሆኑን በመገንዘብ፣ መምህር ሆይ! ‘እግዚአብሔር አንድ ነው፤ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም’ ብለህ የተናገርከው ልክ ነው፤ ሰው በፍጹም ልቡ፣ በፍጹም ነፍሱ፣ በፍጹም አሳቡ፣ በፍጹም ኃይሉ እግዚአብሔርን መውደድ ይገባዋል፤ እንዲሁም ሰውን ሁሉ እንደ ራሱ አድርጎ መውደድ ይገባዋል። (ማር. 12፡ 32-33)

ይሁን እንጂ የሙሴ ሕግ መምህሩ ኢየሱስ የተናገረውን ቃል መድገም አስፈላጊ እንደሆነ የተሰማው ለምንድን ነው? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። የማርቆስ ወንጌል፣ መልዕክትን ለማስተላለፍ የሚጠቀምበት ዘይቤ አጭር መሆኑን ካሰብን፣ በዚህ ጊዜ መደጋገሙ የበለጠ ያስደንቀን ይሆናል። ስለዚህ ይህ ድግግሞሽ ምንድነው? ለምን አስፈለገ? ይህ ድግግሞሽ ለምናዳምጥ ሁላችን ትልቅ ትምህርት ይሆነናል። የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሌላ ማንኛውም ዜና ሊታይ ወይም ሊወሰድ አይገባም።

የእግዚአብሔር ቃል መደገም አለበት፣ የግል መሆን አለበት፤ እንዲሁም መጠበቅ እና መከበር አለበት። ይህን ለመግለጽ የገዳማዊያን ሕይወት ትውፊት ደፋር እና ተጨባጭ ቃል ይጠቀማል። የእግዚአብሔር ቃል በተደጋጋሚ መብላላት አለበት። አስፈላጊነቱ እና ጥቅሙ በሁሉም የሕይወት ደረጃ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ በየጊዜው መብላላት ይኖርበታል። ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስም እንዳለው፣ የእግዚአብሔርን ቃል በልባችን፣ በነፍሳችን፣ በአእምሮአችን እና በኃይላችን ሁሉ ማሳተፍ ይገባል። (ማር. 12፡ 30) የእግዚአብሔር ቃል በውስጣችን ሊኖር ይገባል፤ በውስጣችን እንደ ገደል ማሚቶ ራሱን ደጋግሞ የሚያስተጋባ ከሆነ፣ ይህ ማለት እግዚአብሔርም በልባችን ውስጥ ይኖራል ማለት ነው። በማር. 12፡34 ላይ እንደተጠቀሰው፣ ለሙሴ ሕግ መምህር “አንተስ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” እንዳለው ሁሉ ለእኛም ተመሳሳይ መልዕክት ይናገረናል።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! እግዚአብሔር የሚፈልገው የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞችን ሳይሆን፣ ቃሉን ተቀብለው ራሳቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ የሚሆኑትን ልቦች ነው። ወንጌልን በደንብ ማወቅ፣ ሁል ጊዜም በእጃችን እንዲኖር ማድረግ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለዚህም ነው። ሌላው ቀርቶ አነስተኛ መጠን ያለውን የወንጌል መጽሐፍ በኪሳችን ወይም በቦርሳችን ይዘን በየጊዜው ለማንበብ ያለን ፍላጎት ማደግ አለበት። ይህን የምናደርግ ከሆነ የእግዚአብሔር ቃል የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ልባችን ውስጥ ይገባል። ወደ እኛ የበለጠ በመቅረብ እኛም በእርሱ ፍሬን እንናፈራለን። የዛሬውን ወንጌል እንደ ምሳሌ ከወሰድን፣ እግዚአብሔርን እና ጎረቤታችንን መውደድ እንዳለብን ማንበብ እና መረዳት ብቻውን በቂ አይደለም። “ከሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ” በውስጣችን መኖሩ እንዲሰማን፣ እንዲዋሃድ፣ የህሊናችን ድምጽ እንዲሆንልን ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ፣ በመደርደሪያ ላይ ተረስቶ እንደቀረ ደብዳቤ ሊሆን አይችልም።

ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በልባችን ውስጥ እንዲበቅል ያደርገዋል። የእግዚአብሔር ቃል ዘወትር ይሠራል፣ ሁልጊዜም በእንቅስቃሴ ላይ ነው፣ ሕያው እና ውጤታማም ነው። “የእግዚብሔር ቃል ሕያው እና የሚሠራ ነው፤ ነፍስን እና መንፈስን፣ ጅማትን እና ቅልጥምን እስኪለይ ድረስ የሚቆራርጥ ነው፤ በልብ ውስት የተሰወረውንም አሳብ እና ምኞት መርምሮ የሚፈርድ ነው።” (ዕብ. 4፡12) ስለዚህ እያንዳንዳችን የተለያየን ብንሆንም፣ ህያው በመሆን እግዚአብሔር የሚሰጠን ተመሳሳይ የፍቅር ቃል እንሆናለን። በቅዱሳንም ሕይወት ውስጥ የምናየው ይህንን ነው። ቅዱሳን አንዳቸው ከሌላው ጋር አንድ አይደሉም፤ ሁሉም የተለያዩ ናቸው፤ ነገር ግን አንድ ዓይነት የእግዚአብሔር ቃል አላቸው።

ስለዚህ ዛሬ የሙሴ ሕግ መምህር ምሳሌን እንከተል። የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በውስጣችን እንዲሰማ፣ በውስጣችን በተደጋጋሚ እዲያስተጋባ እናድርግ። እግዚብሔር አምላክን በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ነፍስ፣ በፍጹም አሳብ፣ በፍጹም ኃይል እንውደድ፤ እንዲሁም ሰውን ሁሉ እንደ ራሳችን አድርገ እንውሰድ። ከዚህም በተጨማሪም ‘ይህ ትእዛዝ በእውነቱ ህይወቴን ይመራዋል ወይ?’፣ ይህ ትእዛዝ በዕለት ተዕለት ሕይወቴ ውስጥ በተግባር ይገለጻል ወይ?’ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። ዛሬ ማታ፣ ወደ መኝታችን ከመሄዳችን በፊት፣ በዚህ ቃል ላይ የህሊና ምርመራ እናድርግ። ጌታን እንደምንወደው እና ዛሬ ላገኘናቸው ሰዎች ትንሽ መልካም ነገር አድረገን ከሆነ ራሳችንን እንጠይቅ። ይህን ትዕዛዝ የሚፈጽም ትንሽ የፍቅር ሥራ አበርክተን ከሆነ ብለን እራሳችንን እንጠይቅ። የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ የሆነባት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ህያው የሆነውን የቅዱስ ወንጌል ቃል በልባችን መቀበልን ታስተምረን።”

 

13 November 2021, 11:56