ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ፣  

ብጹዕ ካርዲናል ሳኮ፣ የኢራቅ ፖለቲከኞች አለመግባባቶችን እንዲያስወግዱ አሳሰቡ

በኢራቅ የባቢሎን ከለዳዊያን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ፣ የኢራቅ ፖለቲከኞች በአገሪቱ ውስጥ የሚታዩ አለመግባባቶችን እንዲያስወግዱ አሳስበዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ ማሳሰቢያቸውን የገለጹት፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ በሌላው ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ሲሉ የሚፈጥሩት ውጥረቶች እያደጉ በመጡበት ወቅት መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢራቅ ውስጥ መስከረም 30/2014 ዓ. ም. የተካሄደው ብሔራዊ የፓርላማ ምርጫ አብላጫ ድምፅ ያለውን ፓርቲ ሳይለይ መጠናቀቁ ይታወሳል። በሺዓው መሪ ሙክታዳ አል-ሳድር የሚመራው የፓርቲዎች ጥምረት እና የሳድሪስት ንቅናቄ 329 አባላት ባሉት ፓርላማ ውስጥ 73 መቀመጫዎችን ማሸነፉ ይታወቃል። ይህም ቀጣዩን የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ ቡድኑ ወሳኝ ድምጽ ማግኘቱን የሚያሳይ መሆኑ ታውቋል። የሺዓው መሪ አቶ ሙክታዳ አል-ሳድር፣ ንቅናቄአቸው በተሃድሶ ጥላ ሥር በመሆን ከሃይማኖት እና ከብሔር ነጻ የሆነ ብሔራዊ የጥምረት መንግሥት ለመመስረት ፍላጎት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የፖለቲካ ግርግር እና አለ መግባባቶች

የምርጫ ውጤቶቹ እየጨመሩ በሄዱ ቁጥር እያንዳንዱ ፓርቲ ቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመወሰን ተጽዕኖን ለማድረግ በፓርቲዎች መካከል አለመግባባቶች እና የፖለቲካ ሽኩቻዎች መፈጠራቸው ተነግሯል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁኑ በስልጣን ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል ካዲሚ ዳግም መመረጥን ባይፈልጉም የብዙኃኑ ድጋፍ ከሆነ ለሁለተኛ ዙር ሥልጣናቸውን ለማራዘም እንደሚችሉ አስታውቀዋል። በዚህም ምክንያት የከለዳውያን ፓትርያርክ፣ ለሁሉም ኢራቃውያን እና ፖለቲከኞች ባስተላለፉት መልዕክት “ለዜጎቻቸው እና ትውልድ አገራቸው ካላቸው አሳቢነት እና ፍቅር” በመነሳት ይግባኝ ብለው፣ የፖለቲካ ቀውሱ ለማንኛውም ፖለቲካ ፍላጎት የማያረካ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ በምሬት ገልፀዋል።

ፍትህ እንጂ የጦር መሣሪያ አያስፈልግም

በኢራቅ የባቢሎን ከለዳዊያን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ በጽሕፈት ቤታቸው ድረ-ገጽ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፣ “የኢራቅ ፖለቲከኞች ምክንያታዊነትን በመቀበል ፣ ራሳቸውን በማረጋጋት ወደ ድርድር እና ውይይት እንዲመለሱ” በማለት አሳስበዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ አክለውም፣ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ከኢራቅ ሕዝብ የተቀበሉት አደራ እንዳለባቸው አሳስበው፣ "አሸናፊዎች የመደሰት መብት ቢኖራቸውም ነገር ግን ተሸናፊዎችን የመጉዳት መብት የላቸውም" ብለዋል። አንዳንድ ቅሬታ የሚሰማቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንደተስተናገዱ የሚሰማቸው መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ አክለው ፣ የጦር መሣሪያን ከመምዘዝ ይልቅ ጉዳያቸው ወደ አገሪቱ ፍርድ ቤት ዘንድ መቅረብ ይኖርበታል ብለው፣ አገራቸው “ፍትህ እንጂ የጦር መሣሪያ አያስፈልጋትም” ብለዋል።

21 October 2021, 17:08