ፈልግ

የምድራችን ስቃይ፣ ድሆችን ጨምሮ የሁሉን ሰው ጩሄት የሚያስተጋባ መሆኑ ተነገረ

የአየር ንብረት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ቪራባድራን ራማናታ የምድራችን እና የድሆች የስቃይ ጩሄት የሁላችን ጩሄት መሆኑን ገልጸው ለዚህ ዋና ምክንያቱ የምድራችን የሙቀት መጠን በመጨመሩ የሚከሰት የአየር ንብረት መዛባት መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዓለም መንግሥታት መሪዎች በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ ከጥቅምት 21 - ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. የአየር ንብረት ለውጥን በማስመልከት 26ኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ሊያካሂዱ ጥቂት ቀናት ብቻ እንደቀሩ ይነገራል።

የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በ2007 ዓ. ም. የተካሄደው ጉባኤ የምድርን ሙቀት መጨመር ተከትሎ እየደረሰ ያለውን አደጋ ለመከላከል በሚያስችሉ የመፍትሄ ሃሳቦች ስምምነት ላይ መድረሱ ይታወሳል። በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ የሚካሄድ የዓለም መንግሥታት መሪዎች ጉባኤ ዓላማ የተባበሩት መንግሥታት ስምምነት ማዕቀፍ ግቦች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ መሆኑ ታውቋል። የቫቲካን ዜና አገልግሎት፣ ጉባኤው ከመካሄዱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ፣ የአየር ንብረት ዕውቅ ተመራማሪ ከሆኑት ከፕሮፌሰር ቪራባድራን ራማናታን ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። ፕሮፌሰር ራማናታን ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ስጋት የሆኑ አደጋዎችን ለማስወገድ ቆራጥ እና ፈጣን እርምጃ ያልተወሰደ ከሆነ አሁን የምናየው አደጋ 50 በመቶ እንደሚያድግ አስጠንቅቀዋል።  

የእናት ምድራችን የብሶት ጩኸት

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የ “አየር ንብረት” ጠበብት የሆኑት ፕሮፌሰር ራማናታን በዓለማችን የተከሰተውን የአየር ንብረት ለውጥን በማስመልከት የመጀመሪያ ጥናታዊ የምርምር ጽሑፋቸውን በ1967 ዓ. ም. ማቅረባቸው ይታወሳል። ፕሮፌሰር ራማናታን በዚህ የመጀመሪያቸው በሆነው የመርመር ጽሑፋቸው፣ “በምድራችን ላይ እየታየ ያለውን አደጋ ወደ ሰዎች ደረጃ በማውረድ አልተነጋገርንበትም” ብለው፣ ውይይት ስናካሂድ የቆየነው ስለ በረዶ መቅለጥ እና ስለ ባሕር ከፍታ መጨመር ብቻ እንደ ነበር አስታውሰው፣ በአየር ሙቀት መጨመር እና በአየር መቀዝቀዝ መካከል ያለው ለውጥ ባለፉት አሥር አመታት ውስጥ እጅግ ግልጽ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል።

የቫቲካን ተወካዮች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫቸውን በሰጡበት ወቅት
የቫቲካን ተወካዮች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫቸውን በሰጡበት ወቅት

“የጋራ መኖሪያ ‘እናት ምድራችን’ ብሶቷን በጩኸት እየገለጸች ትገኛለች” ያሉት አየር ንብረት ጠበብት ፕሮፌሰር ራማናታን፣ “ይህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ‘ውዳሴ ላንተ ይሁን’ በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ስለ ጋራ መኖሪያ ምድራችን እና ስለ ድሃው ማኅበረሰብ ጩሄት ያስተላለፉትን መልዕክት እንደገና እንድመለከተው አድርጎኛል” ብለዋል።

የምድራችን ጩኸት

“የጋራ መኖሪያ ምድራችን የሚሰማትን ብሶት በምን መንገድ ትገልጸዋለች?” ያሉት ፕሮፌሰር ራማናታን፣ አንደኛው መንገድ በአየር መቀት መጨመር እንደሆነ አስረድተው፣ ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር ሆነው እ. አ. አ በ2018 ዓ. ም. ባሳተሙት መጽሐፋቸው፣ የአየር ሙቀት መጠን እ. አ. አ በ2030 ዓ. ም 1.5 ድግሪ የሚያድግ መሆኑን ተንብየዋል። ይህ ግልጽ የሚሆነው ከሚቀጥሉት ዘጠኝ ዓመታት በኋላ መሆኑን ገልጸው፣ ከ 1.0 ድግሪ ወደ 1.5 ድግሪ ሴንቲግሬድ ጨመረ ማለት 50% ጨመረ ማለት እንደሆነ አስረድተዋል። የአየር ሙቀት መጨመር በሌላ ወገን የአየር ንብረት ለውጥን ያስከትላል ያሉት ፕሮፌሰር ራማናታን፣ ሁለት እርስ በእርስ የተገናኙ መሆናቸውን አስረድተዋል። ከአሥር እና ከአሥራ አምስት ዓመታት ወዲህ የነበረው የምድራችን ሙቀት መጨመር ያስከተለውን ውጤት ወይም አደጋ ዛሬ መመልከት ጀምረናል ያሉት ፕሮፌሰር ራማናታን፣ በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች ሰዎች እንግዳ የሆኑ የአየር ጸባይ እያስተዋሉ መምጣታቸውን አስረድተዋል። አክለውም እነዚህ የአየር ንብረት ለውጦች በሽህ ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ ወይም በአምስት መቶ ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ ሊታዩ የሚችሉ ነበር ብለው፣ ዛሬ ግን በአሥር ዓመታት ውስጥ ብቻ ሁለት ጊዜ መንጸባረቃቸውን አስረድተዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ፕሮፌሰር ራማናታንን በተቀበሏቸው ጊዜ
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ፕሮፌሰር ራማናታንን በተቀበሏቸው ጊዜ

ቆላማ አካባቢዎች ይበልጥ ቆላማ እየሆኑ፣ ዝናባማ አካባቢዎች የበለጠ እርጥብ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸው በቅርቡ በጀርመን ለተከሰተው የንብረት እና የሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነውን ከፍተኛ የዝናብ መጠን እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል።         

የድሆች ጩኸት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በጋራ መኖሪያ ምድራችን ላይ የተከሰተውን አደጋ ከድሃው ማኅበረሰብ ጩሄት ጋር ማዛመዳቸውን ያደነቁት ፕሮፌሰር ራማናታን፣ “በዓለም ላይ እስካሁን ድረስ የቅሪተ አካል ነዳጆችን ያላገኙ ሦስት ቢሊዮን ሰዎች” በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎች ሰለባ እንደሆኑ መናገራቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህ የዓለማችን ሕዝቦች ምግባቸውን የሚያበስሉት እና ለዕለታዊ ፍጆታቸው የሚጠቀሙት አካባቢን ከማይጎዳ በእንጨት ከሚነድ እሳት መሆኑን አስረድተዋል። ለዕለታዊ ኑሮአቸው ነዳጅን ከማይጠቀሙ ከሦስት ቢሊዮን ሰዎች መካከል አብዛኛው በግብርና ሥራ የሚተዳደር መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ራማናታን፣ እንደ ምዕራቡ ዓለም እጅግ ሰፋፊ የእርሻ መሬት ያላቸው ሳይሆን እጅግ በጣም አንሰተኛ የእርሻ መሬት ያላቸው መሆኑን አስታውሰዋል። “በተከታታይ ለረጅም ጊዜ  ዝናብ ቢዘንብ ምን ችግር አለው?” የሚሉ ሰዎች መኖራቸውን ያስታወሱት ፕሮፌሰሩ፣ ሕንድን በመሳሰሉ ድሃ አገራት የሚኖሩ ገበሬዎች ለም አፈራቸው በዝናብ ውሃ በመታጠቡ የምርት መጠንም የሚቀንስ መሆኑን አስረድተዋል።

የሁሉም ሰው ጩሄት ነው

ብሶታቸውን በጩሄት እየገለጹ ያሉት ምድራችን እና ድሃው ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን፣ በምድራችን ሙቀት መጨመር ጉዳት የደረሰበት ድሃ እና ሃብታም ሳይለይ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል መሆኑን ያስረዱት ፕሮፌሰር ራማናታን፣ ልክ እንደ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው አደጋ በእያንዳንዳችን ጓዳ እንደሚገባ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። ይህም በከፍተኛ ሙቀት ወይም በኃይለኛ ዝናብ በርካታ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸውን ሳይቀር ሊያጡ እንደሚችሉ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።    

ለቅሶን ወደ ደስታ መቀየር

ሁለት አማራጮች ብቻ አሉን ያሉት ፕሮፌሰር ራማናታን፣ አደውን ለመከላከል የተዘጋጀን እንደሆነ ልንከላከለው እንችላለን፤ አለበለዚያ በአደጋው ክፉኛ እንጠቃለን ብለዋል። ከአሁን በኋላ የባህሪ ለውጥ ማድረግ አያችላም ብለው ያለው አማራጭ ፣የግብርና ምርትን በተመለከተ ገበሬዎች የምርት ማምረቻ ሥርዓትን ለአካባቢያቸው ከሚመች የአየር ንብረት ጋር ማመሳሰል እንደሚገባ አሳስበዋል። ከአሥር እስከ አሥራ አምስት ዓመታት በፊት የነበረውን የአየር ንብረት ምልክትን መመልከት ሳይሆን, የዛሬውን የአየር ንብረት ምልክትን በማስተዋል የግብርና ሥርዓትንም በዚሁ መልክ መቀየር እንደሚያስፈልግ ፕሮፌሰር ራማናታን መክረዋል።  

የማን ድምፅ ተሰሚነት ይኖረዋል?

በአየር ንብረት ለውጥ የደርሰውን አደጋ ለመቀልበስ፣ የተቃጠለ አየር ልቀትን መቀነስ ሁለተኛ አማራጭ እንደሆነ የገለጹት ፕሮፌሰር ራማናታን፣ ባሁኑ ጊዜ የሚታየው ከፍተኛ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን ውጤት እንደማያመጣ፣ ይልቅ በሰዎች መካከል ከፍተኛ ልዩነትን እንደሚፈጥር አስረድተዋል። ከፖለቲካው መድረክ ወጣ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት፣ ቤተመቅደሶች፣ ምኩራቦች እና መስጊዶች ብቻ ናቸው ብለዋል። እንደ አለመታደል ሆኖ ማኅበራዊ ሚዲያውም ወገናዊነት ያጠቃዋል ብለው፣ የእምነት ተቋማት እና መሪዎቻቸው ሰዎችን በፍጥነት በማስተማር ክፍተቱን መሙላት ይችላሉ ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በማለት ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው አማካይነት የማስተማር ጥረት መጀመራቸውን ገልጸዋል። በቫቲካን የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ አማካይነት የተለያዩ የሳይንሳዊ ተመራማሪዎች፣ የእምነት ተቋማት መሪዎች እና ፖሊሲ አውጭዎች ኅብረት መመስረቱን አስታውሰው፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከደሃው ማኅበረሰብ ጋር በቀጥታ የምትገናኝበትን መስመር ማዘጋጀቷን፣ የአየር ንብረት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ቪራባድራን ራማናታ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።     

26 October 2021, 17:10