ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት 

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ የሱባኤ እና የጸሎት ቀን አዋጅን አስመልክተው መልዕክት አስተላለፉ

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ የዕርቀ ሰላም ኮሚሺን ሰብሳቢ፣ የሱባኤ እና የጸሎት ቀን አዋጅ አፈጻጸምን በማስመልከት ለመላው ካቶሊካውያን እና በጎ ፍቃድ ላላቸው ሁሉ የሚከተለውን ሀገር አቀፍ መልዕክት አስተላለፈዋል፥

ለክቡራን ጳጳሳት፣

ለክቡራን የሀገረስብከት እንደራሴዎች፣ የሐዋርያዊ ሥራ አስተባባሪዎች፣

ለክቡራን ቆሞሳት፣ ካህናት፣ ለገዳማውያንና/ውያት፣

ለክቡራን ምዕመናን

ከሁሉ አስቀድሜ የጌታ ሰላም ይብዛላችሁ ለማለት እወዳለሁ።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የወቅቱን የሃገራችንን የሰላም ዕጦት ሁኔታዎችን አስመልክቶ ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ. ም. ባስተላለፈው መግለጫ ሀገር አቀፍ የሱባኤ እና የጸሎት ቀን በማወጅ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ከጷግሜ 1 – 5 ቀን 2013 ዓ. ም. በሱባኤ፤ በተለይም ደግሞ ጷግሜ 1 ቀን 2013 ዓ. ም ሁሉም እንደየእምነቱ በሱባኤ፤ በጸሎት እና በጾም ወደ ፈጣሪው ይጮህ ዘንድ ጠይቁዋል። እኛም እንደ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከመላው ሕዝባችን ጋር በመሆን በእምነታችን ሥርዓት ይህንኑ ጊዜ በጾም እና በጸሎት እናሳልፍ ዘንድ በደብዳቤ ቁጥር CBCE/GS/285/21 መጠየቃችን ይታወሳል። ስለሆነም አሁንም በድጋሚ በየሀገረ ስብከቶቻችን እና በየቁምስናዎቻችን ስለሀገራችን ሰላም በተጠቀሱት ቀናት በቅንነት መንፈስ ከልባችን እንድንጸልይ እና የእግዚአብሔርን እርዳታ እንድንለምን በአጽንዖት እና በአደራ ጭምር ለማሳሰብ እወዳለሁ።

በመቀጠልም እሁድ ነሐሴ 30 ቀን እና አምስቱን የጷግሜን ቀናት በዓይነትም ሆነ በገንዘብ የሚሰበሰበውን መባዕ በየአካባቢው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣብያዎች ለሚገኙ ወገኖቻችን በጋራ የሚዳረስ በመሆኑ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ እንዲሰራ በየቁምስናው እና በየሀገረስብከቶቻችሁ ያላችሁ የሚመለከታችሁ አገልጋዮች ይህንኑ አስተባብራችሁ ወደ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ እንዲደርስ ታደርጉ ዘንድ እጠይቃለሁ።

እግዚአብሔር ለሀገራችን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ይስጥልን።

ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት

04 September 2021, 22:49