ፈልግ

የ52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መክፈቻ የ52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መክፈቻ  

በቡዳፔስት የሚካሄደው 52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ በይፋ መጀመሩ ተነገረ

በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ከነሐሴ 30/2013 ዓ. ም. እስከ እሑድ መስከረም 2/2014 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄድ 52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ በይፋ መጀመሩን የጉባኤው መርሃ ግብር አመልክቷል። ጉባኤውን በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ያስጀመሩት ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ባኛስኮ መሆናቸው ታውቋል። ብጹዕነታቸው በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባቀረቡት ስብከት፣ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ምዕመና “ምንጮቼ ሁሉ በአንተ ውስጥ ናቸው” በሚለው በጉባኤው መሪ ቃል ላይ እንዲያስተነትኑ ጋብዘዋል። በቡዳፔስት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ፣ ብቸኝነትን፣ ርቀትን እና ግድየለሽነትን የሚበልጥ መሆኑን አስረድተዋል። መስከረም 2/2014 ዓ. ም. የሚፈጸመውን 52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓትን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሚመሩት መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት መጀመሪያ ላይ ንግግር ያደረጉት የሃንጋሪ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኤርዶ “ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ቁርባኑ ከእኛ ጋር መኖሩን የምንገነዘብበትን ጸጋ እግዚአብሔር ይስጠን፤ እርሱ ቤተክርስቲያኑን፣ ሕዝቡን እና መላውን ሰብዓዊ ፍጥረትን ብቻውን አይተወውም” በማለት ገልጸዋል። ካርዲናሉ አክለውም በ52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ላይ ለተገኙት፣ የክርስቲያኖችን አንድነት ለማሳደግ እና የወንጌል ምስክርነታቸውን እውነተኛ ለማድረግ በጋራ ለሚሠሩ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

የአውሮፓ ጳጳሳት ጉባኤዎች ፕሬዝዳንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ባኛስኩ ለ52ኛው የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መክፈቻ ቅዳሴ ጸሎት ያዘጋጁትን ስብከት፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኤርዶ በአገሩ ቋንቋ በንባብ ማቅረባቸው ታውቋል። ካርዲናሉ በመልዕክታቸው የቤተክርስቲያን እረኞች ድምጽ ከጉባኤው መድረክ ተነስቶ ትህትናን እና ደስታን ወደ አውሮፓ እና የዓለማችን ምዕመናንን ልብ ለማድረስ ይጓዛል ብለዋል። “ደካማ ድምጽ ቢሆንም በበርካታ የሰማዕታት ደም አማካይነት ለዘመናት ያህል ሲያስተጋባ የቆየ፣ ምስክርነት ለመስጠትም ኃይልን ከኢየሱስ ክርስቶያ ያገኘ፣ የአገልጋይ ውስንነቶች ጥላዎች ቢኖሩም ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃንን በቤተክርስቲያን ውስጥ ለማብራት ኃይል የተገኘበት ነው” ብለዋል።

ማንም ብቸኛ አይደለም

የሰማዕታቱ ድምጽ፣ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ የተሸፈነ፣ ለዛሬው ዓለም ሕዝቦች ታላቅ እውነት የሚናገር መሆኑን ያስረዱት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኤርዶ፣ በጠላት በተከበበ ዓለም ውስጥ ብቻችሁ አይደላችሁም፣ በሚያስደንቅ የሕይወት ምስጢር በፊት ብቻችሁ አይደላችሁም፣ ለነፃነት እና ለዘለዓለማዊ ሕይወት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ብቻችሁ አይደላችሁም፣ የትም ብትሆኑ የተሰወራችሁ አይደላችሁም፣ እግዚአብሔር በፍቅሩ ይመለከታችኋል፤ ወላጅ አልባም አይደላችሁም፣ እግዚአብሔር አባታችሁ ነውና። የኢየሱስ ደም፣ የዓለም ቤዛ እና የዘላለም ሕይወት እንጀራ ስለሆነ አትፍሩ፤ እግዚአብሔር አልሞተም ፣ ቅዱስ ቁርባን እያንዳንዱን ብቸኝነት፣ እያንዳንዱን ርቀት፣ ግድየለሽነትንም ሁሉ ያሸንፋልና” በማለት መልዕክታቸውን አቅርበው፣ በዚህ ሁኔታ ያ ተመሳሳይ ድምጽ ቤተክርስቲያን ድምጿን እንድታሰማ ይጠራታል ብለው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ ግርማ በሁሉም ፊት እንዲበራ ያደርጋል ብለዋል።

በጉባኤው መክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወቅት የመጀመሪያ ቅዱስ ቁርባን እና የሜሮን ምስጢራትን የተቀበሉ በርካታ ሰዎችን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ባኛስኮ፣ ምስጢራቱን የተቀበሉት በሙሉ የዘለዓለም ወዳጅ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመቀበል ያስቻላቸውን የልባቸውን ዝግጁነት አስታውሰዋል።  በካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙት ወጣት ተማሪዎች ንግግር ያደረጉት ካርዲናል አንጀሎ ባኛስኮ፣ እምነት እና ምክንያት አብረው የሚሄዱ መሆናቸውን አስረድተው “እግዚአብሔር የሰዎችን ነፃነት የሚጋፋ አለ መሆኑን ገልጸው፣ እምነትም እገዳዎችን የሚያስቀምጥ ሳይሆን ይልቁንም ፍቅር መስዋዕትነትን የሚያስከፍል ቢሆንም ለደስታ ታላቅ የአዎንታ መልስ ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ባኛስኮ ለወጣት ተማሪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ቤተክርስቲያን ወጣቶችን እና ቅንዓትነታቸውን የምትፈልግ፣ ወጣቶችም ኢየሱስን የሚፈልጉ መሆናቸውን አስረድተዋል። 

እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ነው

የሁሉም ነገር ዕድሜ የተገደበ እንደሆነ ፣ ለዘለዓለም የሚኖር እግዚአብሔር ብቻ ነው ብለው፣ ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ እና ደም በቅዱስ ቁርባን ጠብቃ ያቆየች በመሆኗ እውነተኛ ዘለዓለማዊት መሆኗን አስረድተዋል። አክለውም ቅዱስ ቁርባን በሕይወታቸው ውስጥ የእያንዳንዷ ቀን ማዕከል ይሁን ብለዋል። ለካኅናት ባስተላለፉት መልዕክታቸውም፣ ካኅናት የእናት እና አስተማሪ ቤተክርስቲያን ቀዳሚ አገልጋዮች መሆናቸውን ገልጸው፣ ካኅናት የእግዚአብሔ ፍቅር መስካሪዎች፣ በቁሳዊው ዓለም ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ነቢያት፣ በጠፋው ዓለም ውስጥ ተስፋን የሚያበስሩ የሕያው ባሕል ወራሾች መሆናቸውን አስረድተዋል። አክለውም፣ ቤተክርስቲያን በሐዋርያዊ አገልግሎት መካከል ችግር እና መከራ እንደሌለ የምታረጋግጥላቸው ሳትሆን፣ ነገር ግን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሆና ፍርሃት እንዳይዛቸው የምታበረታታ ናት ብለዋል።

ኢየሱስ በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ ነው

የአውሮፓ ጳጳሳት ጉባኤዎች ፕሬዝዳንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ባኛስኩ ለ52ኛው የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መክፈቻ ያዘጋጁትን ስብከት ሲያጠቃልሉ፣ የመከራ መስቀል የከበዳቸው፣ ለፍትህ ሲሉ ስቃይን የሚቀበሉ፣ ድምጻቸው እንዳይሰማ የተደረጉ፣ በስደት ዓለም የሚገኙ በሙሉ፣ ኢየሱስ ወደ እርሱ በሚጮሁት ሰዎች ልብ ውስጥ ስለሚገኝ ድፍረትን እንደገና እንዲያገኙ አደራ ብለዋል።

ቤተክርስቲያን መልካም ዜናን የምታውጅበት እና የምታመልከው ከኢየሱስ ክርስቶስ ስም በቀር ሌላ ስም የሌላት መሆኑን አስታውሰው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገለጸው በቅዱስ ቃሉ፣ አለኝታነቱም በጉልህ የሚታየው በቅዱስ ቁርባን መሆኑን አስረድተዋል። 

07 September 2021, 16:56