ፈልግ

† ካርዲናል ብርሃነየሱስ  ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን  የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርሰቲያን  ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት † ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርሰቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት 

ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ እግዚአብሔር የሰጠንን አዲስ ዓመት በመጠቀም በእምነትና በተስፋ ለሰላም እንጸልይ ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርሰቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት፣ የ2014 ዓ. ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር ለሚገኙ ምዕመናን እንዲሁም በጎ ፈቃድ ላላቸው በሙሉ መልዕክት አስተላልፈዋል። ካርዲናል ብርሃነየሱስ በመልዕክታቸው እግዚአብሔር በልግስናው የሰጠንን አዲስ ዓመት በመጠቀም በእምነትና በተስፋ ለሰላም እንጸልይ ብለዋል።

ክቡራት እና ክቡራን ፣ የብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል መልዕክት ከዚህ በታች እንደሚከተለው ይነበባል፥

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

“እግዚአብሔር ሆይ ከዘመናት እሰከ ዘመናት መጠጊያ ሆነኸናል” (መዝ 90፥1)

ብፁዓን ጳጳሳት ፣ ክቡራን ካህናት ፣ ገዳማውያንና/ውያት ፣ ክቡራን ምዕመናን ፣ በጎ ፈቃድ ያላቸሁ ሰዎች ሁሉ ፣ ክቡራንና ክቡራት

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ምዕመናንና የአገራችን ሕዝቦች እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ በሰላም አሸጋገራችሁ በማለት መልካም ምኞቴን በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርሰቲያን ስም እገልፅላችኃልሁ።

ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ የ2014 ዓ. ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት።

እግዚአብሔር አምላካችን ከዘመናት እስከ ዘመናት መጠጊያ ሰለሆነን ወሰን በሌለው ባለጠግነት ጥበብና ኃይል ሁሌም እናሞግሰዋለን። ምክንያቱም ሁሉም የሚኖረው ከእርሱ በእርሱ ለእርሱ ነውና። እግዚአብሔር በልግስናው አዲስ ዓመትን ስጥቶናል። ስለሆነም በሙሉ ልባችን እናመሰግነዋለን። እርሱ ሁሌም የተለያዩ ዓመታትን በመስጠት እየተንከባከበን ያሻግረናል። በአዲስ ፀጋም ይጎበኛናል ።

እግዚአብሔር ጥበብ ነው። ሁሉን ያውቃል ሁሉንም ፈጥሮ በሥርዓትና በውበት ይመራል እኛ ደግሞ የብርሃን ልጆች የሆንን እንቅልፍ እንዳይወስደን መትጋትና መበርታት ይገባናል። ፈጣሪያችን ሰዎች ዘመንን በሚገባ እንዲጠቀሙበት ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ሰጥቷቸዋል። ስለሆነም በእግዚአብሔር ፊት ጊዜ አይቆጠርምና እርሱን እያመሰገንን በሰጠን ሁሉ በሙሉ ፈቃድ እንሥራበት። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ተረድተን በሙሉ ልባችን ስንፈጽመው እምነታችን እየበረታ ይሄዳል ዋጋችን ትልቅ ይሆናል።

በሮሜ 5፥1-2 ቅዱስ ጳውሎስ "በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ" ይላል። እንደሚታወቀው ሰላም የፍቅር ፍሬ ነው። እግዚአብሔር ከእኛ ከሰዎች ጋር እርቅን ያደረገው ፍቅርን በልባችን በማፍሰስና በሙላት በመስጠት ነው። እኛም ይህን ፍቅር ተቀብለን እግዚአብሔርንና ሰዎችን በሙሉ ልባችን ልንወዳቸው ይገባል።

እግዚአብሔር ሰላምን ይወዳል አለመግባባትንም ሁሉ ይጠላል። ሰላምን የሚወዱና ሰላምን የሚፈጥሩ እግዚአብሔርን መስለው በትህትና ይታዘዛሉ። ሰላም ሰላምን ይፈጥራል። አለመግባባትም ቢኖር በመልካም ቃል በመመካከር የሰዎችን ሕይወት ሁሉም ወገኖች መታደግ ይኖርባቸዋል።

ዘመን ሲለወጥ ሰማይንና ምድርን በእነርሱም ያለውን የፈጠረውን አምላካችንን እንደምናመሰግነው ካለንበት የጨለማ መንፈስ ወጥተን ወደ ብርሃን መንፈስ ሁላችንም መመለስ አለብን። በጊዜያችን የጦርነት አስከፊነትን ከአንድም ሁለቴ አይተናል ስለዚህ መጥፎ ክስተት አስከፊነትና በሕዝቦቻችን፣ በቤተሰቦቻችን ሰላመጣው ስቃይ መልዕክቶች የጻፍን ስንሆን በዚህ በአዲስ ዓመትም በእምነትና በተስፋ አድርገን በድጋሚ ስለ ሰላም እንጸልያለን። የእግዚአብሔር ቃል በማቴዎስ ወንጌል እንደሚለው ሰዎችን የሚያስታርቁ፣ የተጣሉትን ይቅር ተባባሉ የሚሉ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ። ስለዚህ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ሰለ ሰላምና እርቅ የሚሠሩትን እንደ እምነታችን የምናበረታታ ሲሆን የጥላቻ ንግግር የሚያባብሱ ዜናዎችንና ትንታኔዎችን አስወግደው በዚህ አዲስ ዓመት ፍቅርና እርቅን የሚሰብኩ እንዲሆኑ እንጸልያለን እንመኛለን።

ሁላችንም መንፈሳችን በእምነት ብርሃን እንዲበራ ያስፈልጋል። ምክንያቱም የእምነታችን ብርሃን ደካማ ሲሆን መንፈሳዊ ነገሮቻችን ይደበዝዛሉ። እምነታችን ብርቱ ከሆነ ግን ጌታን በየቀኑ በሚገጥሙን አስቸጋሪ ነገሮች ውስጥ እናየዋለን። ሰለዚህ ወደ እርሱ ለመቅረብ እንትጋ በችግርም ጊዜ ወደ እርሱ ተመልሰን እንጸልይ።

ሐዋርያት ችግርና መከራን እንደተሻገሩ እኛም በዙሪያችን ያሉ ነፋሶች ብርቱና ተለዋዋጭ ቢሆኑብን፤ ተስፋ አስቆራጭ ቢመስሉንም መሪያችን የሆነውን ፈጣሪያችንን ይዘን በእርሱ ታድሰን አዲሱን ዓመት እንቀበለው ለራሳችንና ለተተኪው ትውልድ መልካም ነገር ለማስተላለፍ በብርሃን እንጓዝ። ወንጌል ለሁላችንም የብርሃን ልጆች እንሁን ይለናል ።

የተወደዳችሁ ምዕመናን በዚህ የዘመን መለወጫ በዓል በተለመደው ቸርነታችሁ ድሆችን፣ የተቸግሩትን፣ ከቤት ንብረታችው የተፈናቀሉትንና የተሰደዱትን በመርዳት ክርስቲያናዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ አደራ ማለት እንወዳለን። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚለው “ሰውን መርዳት ለእግዚአብሔር የሚደረግ መስዋዕት ነውና”።

በመጨረሻም በተለያዩ አገሮችና ቦታዎች የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በየሆሰፒታሉና በየቤታችሁ የምትገኙ ህሙማን፣ በጦርነትና በግጭት መካከል ያላችሁ ልጆቻችን ሁላችሁ እና በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ የሕግ ታራሚዎች እንኳን ለ2014 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል አደረሳችሁ በማለት አዲሱን ዓመት ለሁላችንም የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅርና የአንድነት ያድርግልን። በጦርነትና በዘር ጥላቻ ምክንያት የተከፋፈሉትን ቤተሰቦች፣ በኮሮና ሰቃይ የተጎዱትን እግዚአብሔር በምሕረቱ እንዲጎበኛቸው እንፀልያልን ።

የተባረከና የተቀደሰ አዲስ ዓመት ይሁንልን!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!

† ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርሰቲያን

ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት

11 September 2021, 08:45