ፈልግ

ፅንስ እንዲያስወርዱ ማድረግ ሕሊናን የሚቃወም ከባድ የመብት ጥሰት ነው! ፅንስ እንዲያስወርዱ ማድረግ ሕሊናን የሚቃወም ከባድ የመብት ጥሰት ነው! 

የሰሜን አሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ሕይወትን ከሞት ለማትረፍ እንደገና ይግባኝ አሉ

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ እ. አ. አ ሐምሌ 29/2021 ዓ. ም የአሜሪካ ኮንግረስ በ219 ድምጽ ብልጫ ያጸደቀው እና በቁጥር 4502 የተቀመጠው ሕግ ሕይወትን ለሞት የሚዳርግ፣ ከባድ ሰብአዊ መብት ጥሰትን የሚያስከትል መሆኑን አስታውቀዋል። ሕጉ ከዚህ በተጨማሪ ከሥራ፣ ከጤና፣ ከሰብአዊ አገልግሎቶች እና ከትምህርት ዘርፎች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ፕሮጄክቶች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ ታውቋል። ፕሮጄክቱ ፅንስን ለማስወረድ ከሕዝብ የሚሰበሰቡ የገንዘብ ድጋፎችን የሚያካትት መሆኑም ተመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአሜሪካ መንግሥት ማሻሻያዎችን በማድረግ በድምጽ ብልጫ ያጸደቀው ሕግ፣ ከዚህ በፊት የእናቶችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥለውን ፅንስ የማስወረድ ተግባር በገንዘብ መርዳትን የሚከለክል የ46 ዓመቱ የሃይድ ሕግ መሆኑ ይታወቃል። ይህ የዌልደን ማሻሻያ ሕግ የፌደራል ኤጀንሲዎች፣ የክልል እና የአከባቢ አስተዳደሮች፣ የህዝብ ግብር ተቀባዮች፣ በግለሰቦችን እና በተቋማት ውስጥ ለውርጃ የሚደረጉ ወጪዎችን የሚያግድ ሕግ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ሕግ ላይ ሕግ ማሻሻያ መደረጉ፣ የአሜሪካ ግብር ከፋዮች በፈቃደኝነት ፅንስ ማስወረድን በገንዘብ እንዲደግፉ እና የጤና እንክብካቤ ባለሙያዎችን ከእምነታቸው ውጭ ውርጃን እንዲለማመዱ ከማስገደድ በተጨማሪም ሥራ ቀጣሪዎች እና የሕይወት ዋስትና ሰጪ ድርጅቶች ፅንስን በ​​ማስወረድ ተግባር ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ ያስገድዳቸዋል ተብሏል።

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ በቤተክርስቲያኒቱ የሐይማኖት ነጻነት በሚከታተል ኮሚቴ ፕሬዚደንት በሆኑት በብጹዕ ካርዲናል ቲሞቲ ኤም ዶላን እና በሕይወት ተንከባካቢ እንቅስቃሴዎች ኮሚቴ ፕሬዝዳንት በሆኑት በብጹዕ አቡነ ጆሴፍ ኤፍ ኑማን በኩል በሕግ ቁጥር 4502 ላይ የተቃውሞ ድምጹን ማሰማቱ ይታወሳል። ብጹዓን ጳጳሳቱ የአሜሪካ ኮንግሬስ በከፍተኛ ድምጽ ያጸደቀው ሕግ ከዜጎች ፍላጎት ውጭ የሆነ እና ለውርጃ የሚደረጉ ወጪዎችን የሚያግድ ሕግ የሚጻረር፣ የሃይድ ማሻሻያው ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ 2.4 ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት ከሞት መታደጉን አስታውቀዋል። አሁን ያለ ህይድ ማሻሻያ ሕግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ድሃ ሴቶች ፣ በተስፋ መቁረጥ ሕፃናቶቻችውን ለሞት አሳልፈው ለመስጠት የሚያስገድድ የማይሻር የመንግሥት ውሳኔን ለመቀበል ይገደዳሉ ብለዋል።

በጥያቄ ውስጥ የሚገኝ ኢፍትሐዊነት የሕግ ማዕቀፍ

የአሜሪካ ኮንግረስ በድምጽ ብልጫ ያጸደቀው ይህ ሕግ፣ እርጉዝ ሴቶችን ጨምሮ ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎችን የሚረዱ ድንጋጌዎችን የሚያጠቃልል ቢሆንም “የተሳሳተ ምርጫ ሊጸድቅ አይገባም” ያለው የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ “ፅንስን በማስወረድ ንፁሁን የሰውን ሕይወት ማጥቃት አይገባም” ብሎ፣ ይህ የሆነበት ምክንያት “በጣም ተጋላጭ በሆኑ ደረጃዎች ውስጥ የሚገኝ ሕይወትን መጠበቅ እና መከላከል አለመቻል በማኅበረሰቡ ውስጥ ድሃ እና ተጋላጭ የሆነውን የማኅበረሰብ ክፍል የሚከላከሉ ሌሎች የፍትህ ጥያቄ ድንጋጌዎችን አደጋ ውስጥ ስለሚጨምር ነው ብሏል።

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የሐይማኖት ነጻነት በሚከታተል ኮሚቴ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ቲሞቲ ኤም ዶላን እና የሕይወት ተንከባካቢ እንቅስቃሴዎች ኮሚቴ ፕሬዝዳንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጆሴፍ ኤፍ ኑማን በጋራ በሰጡት መግለጫቸው፣ ጥያቄ ውስጥ የሚገኘውን እና ኢፍትሐዊነት የሚታይበትን ሕግ ማጽደቅና ፅንስን ማስወረድ ስህተት ነው ብለው፣ እምነታቸው በሚያስተምረው መንገድ ሕይወትን ለማገልገል እና ለመፈወስ አገልግሎት ላይ የሚገኙ የጤና ባለሞያዎች ሕሊና በመጻረር ነፃነታቸውን እስከ መሰረዝ ድረስ ይዘልቃል ብለዋል። በዚህ መሠረት 

ገና ያልተወለዱ ንፁሃን የሰው ሕይወት ለማጥፋት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እና ሰዎችን እንዲገድሉ ማስገደድ ሕሊናን የሚጥስ፣ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት የታየበት መሆኑን ብጹዓን ጳጳሳቱ ገልጸዋል። የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ በቁጥር 4502 የተጠቀሰው እና በድምጽ ብልጫ ውሳኔን ያገኘው ሕግ ውድቅ እንዲደረግ በማለት ለሴኔቱ ድምጻቸውን አሰምተው፣ የሰውን ክብር በማስጠበቅ እና ተጋላጭ ለሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ሙሉ ድጋፍ እንዲሰጥ በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

02 August 2021, 17:22