ፈልግ

ክርስቲያናዊ ጋብቻ ክርስቲያናዊ ጋብቻ 

በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለጋብቻ ሕይወት በቂ ግንዛቤ ሊሰጥ ይገባል ተባለ

የደቡብ አፍሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጸም የጋብቻ ሕይወት እሴት በሕዝቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤን ለማስጨበጥ የሚያግዝ ቅስቀሳ ከነሐሴ 16/2013 እስከ መስከረም 29/2014 ዓ. ም ድረስ የሚደረግ መሆኑን ገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “የፍቅር ደስታ” ባሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ በቁ. 325 ላይ “እያንዳንዱ ቤተሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ በውስጡ ፍቅርን ማሳደግ የሚችልበት ብቃት ሊኖረው ይገባል” ያሉትን የደቡብ አፍሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በጋብቻ ሕይወት እና ቤተሰብ መምሪያ ጽሕፈት ቤት በኩል አስታውሷል። ጉባኤው በማሳሰቢያው በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጸም የጋብቻ ሕይወት እሴት በሕዝቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤን እንዲኖር የሚረዱ የተለያዩ ትምህርቶች እና ቅስቀሳዎች ከነሐሴ 16/2013 ዓ. ም እስከ መስከረም 29/2014 ዓ. ም ድረስ የሚሰጡ መሆኑን አስታውቋል። በደቡብ አፍሪካ ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ የታየው የጋብቻ እና የቤተሰብ ሕይወት መልካም ውጤቶችን እያሳየ እንዳልሆነ የገለጸው የጳጳሳቱ ጉባኤ፣ ቢሆንም በአስቸጋሪ ወቅትም ቢሆን ለጋብቻ ሕይወት ክብርን በመስጠት እና ተስፋን በማድረግ ወደፊት ለመጓዝ ጥረት የሚያደርጉ በርካታ ቤተሰቦች መናራቸውን ገልጿል።

የተያዘው ዕቅድ

የደቡብ አፍሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በመልዕክታቸው በአገሪቱ ውስጥ ጋብቻን እና የቤተሰብ ሕይወትን ከፍተኛ ቀውስ ያጋጠመው መሆኑን ገልጸው፣ ከነሐሴ 16/2013 እስከ መስከረም 29/2014 ዓ. ም ድረስ በአገሪቱ ካቶሊካዊ ሬዲዮ ጣቢያ አማካይነት የሚሰጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ትልቅ እገዛን እንደሚያደርግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ በፌስ ቡክ ማኅበራዊ ሚዲያ በኩልም ተመሳሳይ ትምህርቶች የሚሰጡ መሆኑን ገልጸዋል። በመርሃ ግብሩ ባለትዳሮች፣ እጮኛሞች እና የተፋቱት እና ከባል ወይም ሚስት አንዱ የሞተባቸው በመሳተፍ መንፈሳዊ ድጋፍን በማግኘት ላጋጠማቸው ችግር መፍትሄ የሚያገኙበትን ዕድል ለመስጠት የታሰበ መሆኑን አስረድተዋል።

በደቡብ አፍሪካ ያለው ሁኔታ

በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚካሄደው ይህ መርሃ ግብር በ “ፍቅር ደስታ” በተሰኘው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ቃለ ምዕዳንን መሠረት በማድረግ የሚከበረውን የቤተሰብ ዓመት በማስታወስ መሆኑን የደቡብ አፍሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በመልዕክታቸው ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ያደረጉት “የፍቅር ደስታ” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ የሆነበት አምስተኛ ዓመታት ለማስታወስ የተጠራው ዝግጅቱ እ. አ. አ በመጋቢት 19/2021 ዓ. ም. በቅዱስ ዮሴፍ ክብረ በዓል የተጀመረ ሲሆን በ10 ኛው ዓለም አቀፍ የቤተስብ ስብሰባን ባማካሄድ እ. አ. አ ሰኔ 26/2022 ዓ. ም. የሚጠናቀቅ መሆኑ ታውቋል።            

21 August 2021, 16:45