ፈልግ

የደቡብ አፍሪቃ አገራት ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ተወካዮች በዮሐንስቤርግ ውስጥ የደቡብ አፍሪቃ አገራት ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ተወካዮች በዮሐንስቤርግ ውስጥ 

የደቡብ አፍሪቃ ብጹዓን ጳጳሳት ዴሞክራሲ ኃላፊነት መሆኑን ገለጹ

የደቡብ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ከሰኞ ሐምሌ 26 እስከ ነሐሴ 1/2013 ዓ. ም ድረስ አገሪቱን እያስጨነቀ ባለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላይ ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በጉባኤ መካከል ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፣ ዜጎች ስለ ዴሞክራሲያዊ መርሆ ትርጉሞች እና ሚናዎች እንደገና ማሰብ እንደሚያስፈልግ፣ ክርስቲያኖችም የበለጠ ማኅበራዊ ቁርጠኝነት እንዲኖራቸው በማለት ግልፅ ጥሪ ማቅረባቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የደቡብ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በምልዓተ ጉባኤያቸው መካከል ባስተላለፉት መልክት “ከስሜታዊነት መውጣት እንደሚያስፈልግ፣ ከተወሰኑ ሰዎች እና ፓርቲዎች ጋር ከመሻረክ ይልቅ ህዝቡን ስለ ዴሞክራሲ በማስተማር፣ ትክክለኛ መርሆችን በመከተል ኃላፊነት ባለው መንገድ ምርጫን ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን፣ የደቡብ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት፣ ብጹዕ አቡነ ሲቴምበሌ አንቶን ሲፑካ ገልጸዋል።

ማኅበራዊ ማነቃቂያ ሊኖር ይገባል

ብጹዓን ጳጳሳቱ ከሁሉ አስቀድመው በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ውስጥ በተመሳሳይ መልኩ በኤስዋቲኒ እና በደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የተቀሰቀሱ የሕዝብ አመጾችን እና ዝርፊያዎችን አስመልክተው መነጋገራቸው ታውቋል። በቀድሞ ስዋዚላንድ በአሁኗ ኤስዋቲኒ ውስጥ በንግሥና መንበረ ሥልጣን ላይ ከሰላሳ ዓመታት በላይ በተቀመጡ በንጉሥ ምጽውቲ ላይ የተቃውሞ አመጽ መቀስቀሱ ይታወሳል። ባለፈው ሚያዚያ ወር በኤስዋቲኒ ውስጥ የተፈጸመው የአንድ ተማሪ ግድያ የአመጹ መነሻ እንደሆነ ሲነገር ሃላፊነቱን የአገሪቱ ፖሊስ ውስዶ ጉዳዩን በመከታተል ላይ መሆኑ ታውቋል። የሕዝቡን አመጽ ለማቀዝቀዝ ሲባል ፖሊሶች ጭካኔያዊ ተግባር በመፈጸም በሰው ሕይወት ላይ ሞትን እና የመቁሰል አደጋን ማስከተላቸው ታውቋል። በደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ በቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚደንት በነበሩት በያዕቆብ ዙማ ላይ የተፈረደበትን የአስራ አምስት ወራት የእስር ብይን በመቃወም የተቀሰቀሰው አመጽ ለ70 ሰዎች የሕይወት መጥፋት እና ለ1200 ሰዎች መታሰር ምክንያት መሆኑ ታውቋል። በደቡብ አፍሪቃ ከተቀሰቀሰው አመጽ አንድ አዎንታዊ ምላሽ መመልከት ይቻላል ያሉት የደቡብ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት፣ ብጹዕ አቡነ ሲቴምበሌ አንቶን ሲፑካ፣ “አገሪቱ ያጋጠማትን የዴሞክራሲ እጥረት በቆራጥነት ለመቅረፍ የማይቀለበስ እርምጃ መወሰዱን ተመልክተናል” ብለዋል። ይህ መሆን ያለበት አሉ ጳጳሱ፣ ይህ መሆን ያለበት ግን “ተጨማሪ ውድ የሰው ሕይወት ሳይጠፋ” መሆን አለበት ብለዋል።

የኃላፊነት አንጓዎች

በሁለቱ አገራት መካከል የሚካሄዱ አመጾች ልዩነታቸው፣ በኤስዋቲኒ ውስጥ ሕዝቡ ያመጸው ንጉሡ የአገራቸውን ሕዝብ እንደ ግል ንብረት እንደሚመለከቷቸው፣ ነገር ግን በደቡብ አፍሪቃ የተቀሰቀሰው የሕዝብ አመጽ፣ “ሰዎች ለፈጸሙት ጥፋት ተመሳሳይ ቅጣት እንዲሰጣቸው” የሚል መሆኑን ብጹዕ አቡነ ሲቴምበሌ አንቶን ሲፑካ አስረድተዋል። ነገር ግን አመጹ በአገሪቱ ውስጥ ዝርፊያን ማስከተሉን እና በዚህም ሕግ መጣሱን ገልጸዋል። በኢስዋቲኒ ውስጥ ሕዝቡ በንጉሳቸው እጅግ መማረሩን፣ በደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ሕዝቡ የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚደንት ያዕቆብ ዙማን የመሰለ መሪ ሁለተኛ ወደ ስውልጣን ተመልሶ እንዳይመጣ መታገሉን አስረድተዋል።

የደቡብ አፍሪካ ቤተክርስቲያን ጉዞ

ተመሳሳይ ችግር በቤተክርስቲያናቸው መካከልም ይታይ እንደነበር የገለጹት፣ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት፣ ብጹዕ አቡነ ሲቴምበሌ አንቶን ሲፑካ፣ አሁን ግን ችግሩ በመወግዱ ምክንያት ፈጣሪያቸውን አመስግነው፣ በደቡብ አፍሪቃ ቆራጥ ኢኮኖሚያዊ መሻሻል እንዲታይ፣ አመጽ የቀሰቀሱትን እና ያካሄዱትን ወደ ሕግ ዘንድ ለማቅረብ ሃላፊነት ከተሰጣቸው ጋር ቤተክርስቲያን ድምጿን ማስተባበር እንዳለባት እና የደቡብ አፍሪቃ ሕዝብ ጊዜያዊ ጥቅምን ከመመኘት ይልቅ ራሱን ማንቃት እንዳለበት መክረዋል።

ጳጳሳቱ በሲቪል ማህበረሰብ ላይ ያላቸው እይታ

በደቡብ አፍሪቃ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በገጠራማው አካባቢ ትምህርትን በማዳረስ፣ የሥራ ዕድሎችን በማመቻቸት የበኩሏን አስተዋጽዖ ማበርከት የምትችል መሆኑን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ሲቴምበሌ፣ ሚሲዮናውያኑ ያወረሷቸው ትምህርት ቤቶች እና ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች እንዳሏቸው ገልጸው፣ ይህን ዕድል በመጠቀም ለአንዳንድ ማኅበራዊ ችግሮች መፍትሄን መፈለግ ይቻላል ብለዋል። አክለውም በኢስዋቲኒ እና በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያለው አስከፊ ሁኔታ፣ ቤተክርስቲያኗ ለብሔራዊ እርቅ ጠቃሚ የሆነውን የዴሞክራሲ መርሆዎችን ለሕዝብ ለማስተላለፍ መልካም አጋጣሚ የሆናቸው መሆኑን ገልጸዋል። በደቡብ አፍሪቃ በከፍተኛ ሁኔታ የተዛመተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እስከ 2. 47 ሚሊዮን ሰዎችን ማጥቃቱን እና ከ72 ሺህ በላይ ሰዎችን መግደሉን አስታውሰዋል። ይህን አደጋ ለመቀነስ የቤተክርስቲያናቸው ካህናት ከሌሎች ሐዋርያዊ አገልጋዮች ጋር በመተባበር የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ተጋላጭ ማኅበረሰብን ለመርዳት ጥሪ ቀርቧል

የደቡብ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት፣ ብጹዕ አቡነ ሲቴምበሌ አንቶን ሲፑካ፣ ካቶሊካዊ ምዕመናንን ጨምሮ መላው የክርስቲያን ማኅበረሰብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ በተቀሰቀሰው አመፅ ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቁትን ለመደገፍ የበለጠ መተባበር እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ ለማቃለል መላው የአገሪቱ ሕዝብ የጋራ ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።  

05 August 2021, 16:28