ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ፣ 

ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ፣ የቤተክርስቲያንን አንድነት በአገልግሎት ማስመስከር እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

በኢራቅ የከለዳዊያን ሥርዓተ አምልኮን በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንት፣ ከነሐሴ 3-8/2013 ዓ. ም ድረስ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጉባኤ መካሄዱን ከሥፍራው የደረሰን ዘገባ አመልክቷል። የምዕመናን ሚናን አስመልክቶ በተደረገው ውይይት በተለይም የሴት ምዕመናን ተሳትፎ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል። የኢራቅ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ በስብሰባው ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ምዕመናን በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸውን ክርስቲያን ሚኒስትሮች እና የምክር ቤት ተወካዮች ለጋራ ዕድገት ብለው ለሚያደርጉት ጥረት እገዛን በማድረግ የቤተክርስቲያንን አንድነት በተግባር ማስመስከር ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢራቅ የተቀመጠው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በተለያዩ እና ውስብስብ የቤተክርስቲያን እውነታዎች ላይ በማሰላሰል እና በአገሪቱ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በማትኮር መወያየቱ ታውቋል። በውጭ አገራቱ ለሚገኙ የኢራቅ ምዕመናን ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙ ብጹዓን ጳጳሳትንም ጭምር ባሳተፈው የሲኖዶሱ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ፣ ኢራቅ የምትገኝበትን ማኅበራዊ ሕይወት በማጤን፣ የሕዝቡን ፍላጎት እና በአገሪቱ የሚታዩ የለውጥ ሂደቶች ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል። ከሁለት ዓመት በፊት መካሄድ የነበረበት ጉባኤው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መዘግየቱን ገልጸው፣ ከነሐሴ 3-8/2013 ዓ. ም ባካሄዱት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ላይ በቤተክርስቲያን አንድነት፣ በሴት ምዕመናን ሚና፣ በሥርዓት አምልኮ እና በመላው ምዕመናን ተሳትፎ ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

የምዕመናንን ሚና በተመለከተ ምን ተከሰተ?

ከሁለት ዓመት በፊት የተሰበሰበው ልዩ የምዕመናን ምክር ቤት ኮሚቴ በስብሰባው ማግሥት  የምዕመናንን ኃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ሐዋርያዊ ሕይወት የተመለከተ ጠቅላላ ሪፖርቱን እንዳቀረበ ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ሳኮ ቀዳማዊ፣ ከሪፖርቱም ሆነ ባሁኑ ጉባኤያቸው፣ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ባላቸው ተሳትፎ፣ ሥርዓተ አምልኮን በማስተባበር፣ በበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት በመሳተፍ እና በትምህርተ ክርስቶስ መምህርነት ለቤተክርስቲያን ከፍተኛ አጋዥ መሆናቸውን አስታውሰው፣ ለዚህ ሁሉ ድጋፍ በብጹዓን ጳጳሳቶቻቸው በኩል ልባዊ ምስጋና የሚደርሳቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በፖለቲካው ዘርፍም ውይይት ተካሂዷል?                    

የኢራቅ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ በስብሰባው ወቅት ባደረጉት ንግግር በአገሪቱ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ክርስቲያን ሚኒስትሮች፣ ለጋራ ዕድገት እስከ ቆሙ ድረስ መላው የክርስቲያን ማኅበረሰብ በሚችለው ሁሉ ማገዝ እና መደገፍ እንደሚያስፈልግ መስማማታቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በፊት የነበረው የቤተክርስቲያናቸው መጠሪያ ስም መቀየሩን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ፣ የ “ባቢሎን ቤተክርስቲያን” የሚለው መጠሪያ የፖለቲካ እና የብሔረተኝነት ስሜቶች እያንጸባረቀ ከቤተክርስቲያን ሕይወት ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም የጳጳሳቱ ጉባኤ መቀመጫን በዋና ከተማ ባግዳድ ያደረገች ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መጠሪያ ስሟ፥ “የከለዳዊያን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን” የሚል መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ስሟ ኢራንን ጨምሮ በሶርያ፣ በቱርክ፣ በሊባኖስ እና በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች በስፋት የሚታወቅ መሆኑን አስረድተዋል።

የቤተክርስቲያንን ሲኖዶሳዊነት የተመለከቱ ሌሎች ርዕሦች

የቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ቀዳሚ አመሠራረቷን የተከተለ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ፣ የቤተክርስቲያን ሕይወት በኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በኩል በተግባር የታየ፣ እያንዳንዱ ክርስቲያን በተሰጠው ጸጋ አማካይነት አገልግሎቱን በማበርከት አንድነቱን የሚያስመሰክርበት መሆኑን አስረድተው፣ ቤተክርስቲያናቸው ከምስራቃዊያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ መሆኗን፣ የረጅም ጊዜ ሲኖዶሳዊነት ተሞክሮ ያላት እና ከዚህ ልምዷ የምዕራባዊያን ቤተክርስቲያንም መጠቀም መቻሏን ገልጸዋል። ቋሚ ሲኖዶስ እና ጠቅላላ ሲኖዶስ እንዳላቸው ያስረዱት ብጹዕ ካርዲናል ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ፣ እያንዳንዱ አገር የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ያለው በመሆኑ፣ ሉዓላዊነቱን በማስከበር ሐዋርያዊ አስተዳደሩን የሚያጠናክርበት መንገድ ማሰብ እንደሚኖርበት፣ በኢራቅ የከለዳዊያን ሥርዓተ አምልኮ የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ ቀዳማዊ አስገንዝበዋል።  

18 August 2021, 11:49