ፈልግ

የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት እንቅስቃሴ የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት እንቅስቃሴ  

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” ቃለ ምዕዳን የሥነ-ምኅዳር ዕውቀትን የሚያሳድግ መሆኑ ተገለጸ

በደቡብ ጣሊያን፣ ባዚሊካታ ክፍለ ሀገረ ውስጥ የሚገኙ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና የቁምስና መንፈሳዊ ማኅበራት አስተባባሪዎች የሚሳተፉበት የእግር ጉዞ ከነሐሴ 17/2013 ዓ. ም ጀምሮ ሚካሄድ መሆኑን የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አስታውቋል። ለስድስት ቀናት የሚካሄደው የ150 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ ዋና ዓላማ በሥነ-ምህዳር ዙሪያ የሚደርሱ ችግሮችን ለመከላከል እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ ግንዛቤን ለመስጠት መሆኑ ታውቋል። በእግር ጉዞ ወቅት የጸሎት ሥነ-ሥርዓቶች ፣ የአስተንትኖ እና ከወጣቶች በኩል ምስክርነቶች የሚቀርቡ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት እ. አ. አ በታኅሳስ ወር 1995 ዓ. ም. ያስጀመሩት ብሔራዊ የእርግር ጉዞ 23 ወጣቶች የተሳተፉበት ሲሆን፣ ዕቅዱ በወንጌል አገልግሎት ላይ የሚሳተፉ ወጣቶችን ለማዘጋጀት ያለመ መሆኑ ታውቋል። በማኅበረሰቡ መካከል የሚታዩ ችግሮችን ተገንዝበው የመፍትሄ መንገዶችን የሚያፈላልጉ 13 የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና የቁምስና መንፈሳዊ ማኅበራት አስተባባሪዎች የሚሳተፉበት የ150 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ የሚካሄድ መሆኑን የመርሃ ግብሩ መሪ ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ ገልጸዋል። ስድስት ቀናትን የሚፈጅ የእግር ጉዞ ሰባት ርዕሠ ጉዳዮችን መሠረት በማድረግ የሚከናወን ሲሆን እነርሱም፣ መንፈሳዊ አስተንትኖ፣ ቀውስ ማስወገድ፣ የሕይወት ለውጥ፣ የጋራ ግንኙነት፣ የአካባቢ እንክብካቤ፣ ማኅበራዊ አንድነት እና ክብረ በዓል የሚሉ መሆናቸው ታውቋል።

ማሰላሰልን የሚጠይቁ ሰባቱ የ“ውዳሴ ላንተ ይሁን” ቃለ ምዕዳን ርዕሠ ጉዳዮች

የእግር ጉዛ መርሃ ግብር መሪ ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ በገለጻቸው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንን መሠረት ያደረገ የሁለገብ ሥነ-ምሕዳር አገልግሎት ግንዛቤ ማግኘት የሚቻል መሆኑን ገልጸው፣ ይህንንም ለማድረግ በክፍለ ሀገራቸው ከሚገኙ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ጋር መገናኘት እና ማስተንተን እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የፕሮጄክቱ 25 ኛ ዓመት እና የዶን ኦፔርቲ ትውስታ

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንን መሠረት ያደረገ የእግር ጉዞ ዋና ዓላም በበጋው የዕረፍት ጊዜያቸው ወጣቶች በማኅበረሰባቸው መካከል የሚታዩ ችግሮችን ለይተው በማወቅ የመፍትሄ ሃሳቦችን እዲያቀርቡ ለማገዝ “ካሪታስ” በተሰኘ የጣሊያን እርዳታ ድርጅት ከብሔራዊ የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያ ጋር ያስተባበሩት መሆኑ ታውቋል። የዘንድሮ መርሃ ግብሩ ሃያ አምስተኛ ዙር መሆኑን ያስተወቁት ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ ገልጸው፣ እ. አ. አ በ2001 ዓ. ም. ያረፉት የቶሪኖ ሀገረ ስብከት ካህን ክቡር አባ ማርዮ ኦፔራቲ ያራምዱት ከነበረው ሐዋርያዊ እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

በ 130 ሀገረ ስብከቶች ውስጥ የሚገኙ 180 የማህበረሰብ አስተባባሪዎች

በጣሊያን ውስጥ ላለፉት 25 ዓመታት ሲካሄድ የቆየው የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት እንቅስቃሴ እድገትን በማሳየት ወደ 130 ሀገረ ስብከቶች ዘንድ መስፋፋቱ ሲታወቅ፣ በሀገረ ስብከቶች ውስጥ የሚገኙ የቁምስና እንቅስቃሴዎችን እና መንፈሳዊ ማኅበራትን የሚያተባብሩ 180 አባላት ያለው መሆኑ ታውቋል። በሃያ አምስት ዓመታት ጉዞ ወቅት ከአራት መቶ በላይ የአነስተኛ ንግድ ድርጅቶች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራዊ እና በማይክሮ ክሬዲት የሚታገዙ የንግድ እንቅስቃሴዎች መመስረታቸው ታውቋል።

ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር የተደረገ ስብሰባ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከጣሊያን ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ከተወጣጡ ወጣቶች ጋር ግንቦት 28/2013 ዓ. ም በተገናኙበት ወቅት፣ የወንጌል አገልግሎት ለሥራ አስፈላጊውን ክብር መስጠትን እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ ለማለፍ መተባበርን እንደሚጠይቅ፣ በጣሊያን ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ሥር የሚገኙ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ አባልትን ማሳሰባቸው ይታወሳል። ማኅበራዊ እንቅስቃሴው በተጓዘባቸው 25 ዓመታት ውስጥ በብሔራዊ ደረጃ በተመረጡ 20 አባላት እና በብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ መመራቱ ታውቋል።

የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ዓላማ የሁሉ ነው

ብሔራዊ የወጣቶች ሐዋርያዊ እንቅስቃሴ 25ኛ ምስረታውን ለማክበር ያቀደው እ. አ. አ 2020 ዓ. ም ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ 2021 ዓ. ም. መዛወሩ ታውቋል። ብሔራዊ የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ቢሮ፣ በየሀገረ ስብኮቶቹ የሚታዩ ማኅበራዊ ችግሮች እና የሥራ ዕድል እጥረት መሠረቱ ምን እንደሆነ በማጤን ለችግሮች መፍትሄ የሚገኘው በኅብረት በመጓዝ መሆኑን በጳጳሳት ጉባኤ የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያ ቢሮ አስታውቆ፣ ባሁኑ ጊዜ የመፍትሄ አፈላላጊ አካላት ከዘርዓ ክህነት ትምህረት ቤት እና ከቁምስና ማኅበራት የተወቀጣጡ መሆኑ ታውቋል። በጣሊያ ሀገረ ስብከቶች እንቅስቃሴውን በማጠናከር ላይ የሚገኘው የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ማኅበር የተመሠረተው በጣሊያን ውስጥ የቱርሲ-ላጎኔግሮ ሀገረ ስብከት ጳጳስ በሆኑ በብጹዕ አቡነ ቪንቼንሶ ካርሚኔ አስተባባሪነት ሲሆን መርሃ ግብሩ የሚመሩት ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ መሆናቸው ታውቋል። 

ከአፔኒኖ ሉካኖ እስከ አዮኒያ ባህር ዳርቻ

የ“ውዳሴ ላንተ ይሁን” ማኅበር በጣሊያ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ሐዋርያዊ እንቅስቃሴውን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት የመርሃ ግብሩ መሪ ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ፣ እንቅስቃሴውን የበለጠ ፍሬያማ ለማድረግ የብጹዕ ዶሜኒኮ ሌንቲኒ የሕይወት ምሳሌነት መከተል በቂ እንደሆነ ገልጸው፣ የወጣቶችን መንፈሳዊ ሕይወት ለማሳደግ፣ በሚያጋጥማቸው ችግሮች ላይ እያስተነተኑ የእግር ጉዞን በኅብረት ማካሄድ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ አስረድተዋል።

በፍጥረት በማሰብ የሚደረግ አስተንትኖ

ተፈጥሮን እና ሰው ሠራሽ አስገራሚ የእጅ ሥራ ውጤቶችን በማስታወስ የሚደረግ አስተንትኖ አስደናቂ ልምዶችን እንደሚያቀዳጅ የገለጹት ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው “በፍጥረታት ላይ ማስተንተን ካልቻሉ በሰዎች ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ላይ ማስተንተን ይከብዳል” ማለታቸውን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል። “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በሚገባ በተከታታይ ማንበብ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ፣ በሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ላይ በማስተንተን እግዚአብሔር ለሰው ልጅ አዘጋጅቶ ከተሰጠው የተፈጥሮ ስጦታ ጋር መገናኘት የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል።

በየዓመቱ በጋ ወራት የወጣቶች ሐዋርያዊ እንቅስቃሴ መርሃ ግብር በተግባር እንደሚገለጽ ያስረዱት ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ፣ ይህን በማድረግ እንቅስቃሴው ራሱን ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊያጠናክር የሚችልባቸውን አዳዲስ ሃሳቦችን ማፍለቅ መቻሉን አስረድተዋል። ሐዋርያዊ እንቅስቃሴው የወጣቶች ምርጫ በመከተል  የቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮን እና “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በሚገባ ለመመልከት መወሰናቸውን ገልጸዋል። በጣሊያን በሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ዘንድ በየዓመቱ ተግባራዊ የሚደረጉት ዕቅዶች ወጣቶች ጠቃሚ ትምህርቶችን እና ሐዋርያዊ ምክሮችን የሚያገኙበት አጋጣሚ መሆኑን አስረድተዋል።

በየዓመቱ በሚካሄደው የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት መርሃ ግብር ላይ የሚሳተፉ ወጣቶች ቁጥር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መቀነሱን የአለጹት አባ ብሩኖ ቢኛሚ፣ በኅብረት ሆነው ለሚያካሂዱት ዓመታዊ መርሃ ግብር ላይ እንቅፋት መፍጠሩን አስታውሰው፣ ዓመታዊ መርሃ ግብራቸው በወጣቶች የሥራ ዕድል እና “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ ተጨማሪ ግንዛቤ ማሳደጉን አስታውሰዋል። የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ባለፈው ዓመት ባስተባበረው የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት መርሃ ግብር ላይ፣ ኮቪድ-19 ወረሽኝ ባስከተለው የጤና ቀውስ ምክንያት ተሳታፊዎቹ ከዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ተማሪዎች መሆናቸው ተገልጿል። ይህም የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎችን ለማግኘት እና  የቤተክርስትያን ማኅበራዊ አስተምህሮን ለማጥናት ዕድል የከፈተ መሆኑ ታውቋል።

የእስካሁን ልምዳቸው ያስገኘውን ውጤት ተመልክተው ቀጣይ ዕቅዶችን ለመወጠን ሃሳብ እንዳላቸው የገለጹት ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ፣ ወደፊትም ይህን የመሰለ መርሃ ግብር በመወጠን ተግባራዊ ለማድረግ ምኞት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል። ዋና ዓላማቸው የጋራ ጉዞን በማዘጋጀት ችግሮቻችንን በኣጋራ መወያየት እንደሆነ የገለጹት ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ፣ የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገትን በማሳየት፣ ከተለያዩ አባላት ጋር በሚያደርገው ግንኙነት በመታገዝ ወደ ሌሎች ሀገረ ስብከቶችም እየደረሰ መሆኑን፣ የመርሃ ግብሩ መሪ ክቡር አባ ብሩኖ ቢኛሚ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።    

23 August 2021, 16:36