ፈልግ

በፊሊፒን ውስጥ የሚካሄድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መርሃ ግብር በፊሊፒን ውስጥ የሚካሄድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መርሃ ግብር 

በፊሊፒን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የ40 ቀናት የጾም እና የንስሐ ጊዜ መታወጁ ተነገረ

በፊሊፒን፣ ዛምቦንጋ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የ40 ቀናት የጾም እና የንስሐ ጊዜ መታወጁ ታውቋል። እ. አ. አ ከጥቅምት 3 እስከ ኅዳር 12/2014 ዓ. ም. የሚቆይ የጾም፣ የጸሎት እና የንስሐ ጊዜ፣ ምዕመናን በወረርሽኙ ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን ቀርበው እንዲያግዙ የሚያበረታታቸው መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በፊሊፒን ውስጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በወረርሽኙ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑን የታዘቡት በደቡብ ፊሊፒን የዛምቦንጋ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሞይሰስ ኩይቨስ ፣ ለ40 ቀናት በሚቆይ የጾም፣ የጸሎት እና የንስሐ ዝግጅት ላይ ምዕመናን እንዲካፈሉ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በፊሊፒንስ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ችግር

በፊሊፒን ውስጥ ሐሙስ ነሐሴ 20/2013 ዓ. ም የተመዘገበው አዲስ አሃዝ 16,313 ሰዎች በቅርቡ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መያዛቸው አስታውቆ፣ ይህም በአገሪቱ የተመዘገበውን ጥቅላላ ቁጥር ወደ 1,899,222 ማድረሱ ታውቋል። የአገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በሪፖርቱ 236 ሰዎች በቅርቡ መሞታቸው አስታውቆ ይህ ቁጥር የጠቅላላ ሟች ቁጥር ወደ 32,728 ከፍማድረጉን ገልጿል። ካለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ሳምንት ጀምሮ በፊሊፒን ውስጥ በኮሮና ቫይሬስ ወረርሽኝ የሚሞት ሰው ቁጥር መጨመሩ ሲነገር፣ በደቡብ ምሥራቅ ኤዢያ አገሮች መካከል ኢንዶኔዥያ 131,000 ቁጥር በማስመስገብ የመጀመሪያ አገር መሆኗ ታውቋል።

የ40 ቀን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ወቅት

በፊሊፒን የዛንቦንጋ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሞይሰስ ኩይቨስ ሐሙስ ነሐሴ 20/2013 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፣ ከጥቅምት 3 እስከ ኅዳር 12/2014 ዓ. ም. የሚቆይ የጾም፣ የጸሎት እና የንስሐ ጊዜ፣ ምዕመናን በወረርሽኙ ምክንያት ለተጎዱ ቤተሰቦች ዕርዳታን እንዲለግሱ፣ የሚያስፈልጋቸን ድጋፍ እንዲሰጡ በማለት ጠይቀዋል። በሀገረ ስብከታቸው በሚገኙት ቁምስናዎች ከጥቅምት 3/2014 ዓ. ም ጀምሮ በሚካሄደው የመቁጠሪያ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የምዕመናን ተወካዮች ካህናት እንደሚካፈሉ ገልጸው፣ ከዚህም በተጨማሪ የትምህርተ ክርስቶስ ዝግጅት እና የንስሐ ሥነ-ሥርዓት እንደሚኖር ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ ሞይሰስ አክለውም፣ በመንፈሳዊ እና በሞራል ተሃድሶ መሳተፍ የሚፈልጉትን ተቀብሎ ሐዋርያዊ አገልግሎት ለመስጠት የቁምስናው ካህናት፣ ምዕመናንን ንስሐ ለማስገባት እንዲዘጋጁ ጠይቀዋል።  

የአንድነት “ጣቢያዎች”

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊሊፒን ውስጥ ካስከተለው የሰው ሕይወት መጥፋት በተጨማሪ፣ የሕዝቡን ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሕይወትን እጅግ የጎዳው መሆኑ ታውቋል። በተለይም ድሆችን እና በቀን ገቢ የሚተዳደሩትን መጉዳቱ ታውቋል። ቀጣይነት ያለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሰዎች ዕለታዊ ሕይወት ላይ የሚያስከትለው ጭና ከባድ እንደሆነ ገልጸው፣ በተለይም የጤና ችግር ያለባቸውን ለጥቃት ያጋለጣቸው መሆኑ ታውቋል። “አሁን ባለው ሁኔታ ረዳት የሌለን በመሆናችን፣ እርጋታችን እና ዋስትናችን የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አጥብቀን በመያዝ፣ እንደ ማህበረሰብ ምንም የማናውቀውን እና ያልተረጋገጠ መንገድ በመጓዝ ላይ እንገኛለን” በማለት ብጹዕ አቡነ ሞይሰስ ተናግረዋል።

በመሆኑም ምዕመናን በአካባቢያቸው የሚገኙ ችግረኛ ቤተሰቦች እርዳታን የሚያገኙበት ማዕከል በየቁምስናዎች እንዲቋቋም ጠይቀዋል። በማቴ. 10:8 ላይ “በነፃ የተቀበላችሁትን በነፃ ስጡ” የሚለውን ጥቅስ ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ሞይሰስ ፣ ይህ ጥቅስ፣ በፊሊፒን ውስጥ እ. አ. አ መጋቢት 31/1521 ዓ. ም የመጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት የተፈጸመበት 500 የኢዮቤልዩ ዓመት መሪ ጥቅስ መሆኑን አስታውሰዋል። በቁምስናዎች በሚመሠርቱ ማዕከላት በኩል በችግር ለወደቁ ወንድሞች እና እህቶች በቀጣይነት ቁሳዊ ዕርዳታን ለማከፋፈል መታቀዱን ገልጸው፣ በሀገረ ስብከታቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አደጋን የሚከታተል አዲስ ቢሮ መከፈቱንም ገልጸዋል።

የእግዚአብሔር ቃል

ሀገረ ስብከታቸው የእግዚአብሔርን ቃል የሚያበስርበት የትምህርተ ክርስቶስ አገልግሎት ያዘጋጀ መሆኑን ያስታወቁት ብጹዕ አቡነ ሞይሰስ፣ ዝግጅቱ በሚቀጥለው ዓመት እ. አ. አ በጥር 23/2022 ዓ. ም. የሚከበረው በዓል ዝግጅት መሆኑንም አስታውቀዋል። አክለውም የትምህርተ ክርስቶስ አገልግሎትን ቁምስናዎች ተባብረው የሚያዘጋጁት መሆኑን ገልጸው፣ ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ይፋ እንደሚደረግ እና ዓላማውም በእነዚህ ፈታኝ ጊዜያት ምዕመናን ታማኝነታቸውን በመግለጽ በእግዚአብሔር ቃል ያለማቋረጥ ጥገኝነትን እንዲያገኙ ለማገዝ መሆኑን አስረድተዋል። የ74 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ብጹዕ ሮሙሎ ደ ላ ክሩዝ ከሕመማቸው በማገገም ላይ ባሉበት ባሁኑ ወቅት፣ ብጹዕ አቡነ ሞይሰስ ኩይቨስ የዛምቦንጋ ሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ እንዲሆኑ ነሐሴ 5/2013 ዓ. ም. በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መሰየማቸው ይታወሳል።  

30 August 2021, 20:43