ፈልግ

ብሔራዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ጉባኤ ብሔራዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ጉባኤ  

የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት የማኅበረሰብ እና የጊዜ መግለጫ መሆኑ ተገለጸ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስ በአምልኮ ሥርዓት ላይ ምን ውጤት እንዳስከተል ካኅናትን እና ምዕመናንን እያወያየ መሆኑ ታውቋል። ቤተክርስቲያን ባሁኑ ጊዜ በመጓዝ ላይ ያለችበት ከባድ የፈተና ጊዜ ጥንካሬን እና ብርታትን የሚሰጥ እንጂ የሚያስደነግጥ መሆን የለበትም። በጣሊያን ውስጥ ክሬሞና ከተማ ከነሐሴ 17-20/2013 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ ያለውን 71ኛ ብሔራዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ሳምንት ጉባኤን በርካታ ብጹዓን ጳጳሳት እና ካህናትን በመካፈል ላይ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጣሊያን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ ማዕከል ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ፣ በምዕመናን መካከል ያለውን ግንኙነት፣ የምንገኝበትን ታሪካዊ ዘመን እና የአምልኮ ሥነ-ሥርዓትን በሚመለከት ሰፋ ያሉ ውይይቶች በመደረግ ላይ መሆኑ ታውቋል። እነዚህ ርዕሠ ጉዳዮች በጣሊያን ውስጥ ክሬሞና ከተማ በመካሄድ ላይ የሚገኘው 71ኛ ብሔራዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ጉባኤ የሚወያይባቸው ጉዳዮች መሆናቸው ታውቋል። ይህን ጉባኤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዩቲዩብ ማኅበራዊ ሚዲያ በኩል እየተከታተሉ መሆኑ ታውቋል።

በጉባኤው መጀመሪያ ላይ ከቀረበው የውዳሴ ጸሎት ቀጥሎ፣ የሎምባርዲያ ጳጳሳት ጉባኤ ተወካይ እና የክሬማ ከተማ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዳንኤል ጋኖቲ የጉባኤውን ሁለተኛ ቀን ውይይት መምራታቸው ታውቋል። በሁለተኛው የጉባኤው የውይይት ቀን ንግግር ያደረጉት በቶሪኖ ሀገረ ስብከት የሥርዓተ አምልኮ መምህራን ማኅበር ፕሬዚደንት ክቡር አባ ፓውሎ ቶማቲስ እና በቤርጋሞ ሀገረ ስብከት የሥነ-መለኮት ሐዋርያዊ አገልግሎት መምህር ክቡር አባ ፓውሎ ካራራ መሆናቸው ታውቋል። በጉባኤው መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የሐዋርያዊ አምልኮ ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ ማዕከል ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ ማኒያጎ እና የክሬሞና ከተማ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንቶኒዮ ናፖሊዮኒ፣ የማንቶቫ ሀገረ ስብከት ጳጳስ እና በጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የሐዋርያዊ አምልኮ ሥመ-ሥርዓት ምክር ቤት አስተባባሪ ብጹዕ አቡነ ማርኮ ቡስካ መሆናቸው ታውቋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ ለጉባኤው ተካፋዮች ባደረጉት የመክፈጫ ንግግር፣ “የጉባኤው ዋና ዓላማ በአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ላይ በማስተንተን፣ በዘመናት ታሪክ ውስጥ የሚኖር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠውን የእምነት ሕይወት አቅጣጫ በጋራ ለመመልከት ነው” በማለት አስረድተዋል።

አሁን የምንገኝበትን ጊዜ ያስታወሱት ብጹዓን ጳጳሳቱ፣ ሁላችን አንድ አካል ሆነን የምንገኝባት ቤተክርስቲያን ፍጹም አይደለችም በማለት ገልጸው፣ ቤተክርስቲያን በዘመናት መካከል የሚያጋጥሟትን የተለያዩ ችግሮችን አልፋ የመጣች መሆኗን አስረድተዋል። አክለውም ጉባኤው የሚካሄድበት የክሬሞና ክፍለ ሀገር ሕዝብ ከፍተኛ ስቃይ የደረሰበት መሆኑን አስታውሰው፣ የክፍለ ሀገሩ ሕዝብ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ እና ደም የትንሳኤው ተካፋይ መሆኑንም አስታውሰዋል።

ቤተክርስቲያን የዘመኑን ችግሮች መቋቋም አለባት ያሉት፣ በቶሪኖ ሀገረ ስብከት የሥርዓተ አምልኮ መምህራን ማኅበር ፕሬዚደንት ክቡር አባ ፓውሎ ቶማቲስ፣ እምነት ሁል ጊዜ ጥያቄ ያለው መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ማለት ደግሞ በዘመኑ አስተሳሰብ በመታለል ለፈተና እጅ መስጠት ማለት እንዳልሆነ አስረድተው፣ ይልቁንም ጊዜ የማይሽረውን እምነት መንገድ ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በቶሪኖ ሀገረ ስብከት የሥርዓተ አምልኮ መምህራን ማኅበር ፕሬዚደንት የሆኑት ክቡር አባ ፓውሎ ቶማቲስ፣ ከሃምሳ ዓመታት በፊት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ይፋ ያደረጉትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥርዓት አስታውሰው፣ በቤተክርስቲያን ሕይወት፣ በማኅበራዊ እና ባሕላዊ ሕይወት ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጦች እንዳሉ መመልከት እንዳግዳ እንዳልሆነ አስረድተው፣ የሐዋርያዊ አምልኮ ሥነ-ሥርዓት አተባባሪ ምክር ቤት፣ በዘመናት ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ለውጦችን ተገንዝቦ አስፈላጊ ማሻሻያዎችን ያደርጋል ብለዋል። ክቡር አባ ፓውሎ ቶማቲስ አክለውም በካህናት ማነስ ምክንያት የሚታዩ የሐዋርያዊ አምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች ማጠር፣ የምዕመናን ቁጥር መቀነስን ታዛቢ በማድረግ፣ በመለኮታዊው የእግዚአብሔር ቃል ላይ በመመስረት የበለጠ ምቹ መንገዶችን በመምርጥ፣ ለምዕመናን ክርስቲያናዊ ሕይወት የበለጠ በመቅረብ፣ ካህናት ከምዕመናን ጋር ሆነው በጋራ የሚያመልኩበት ዕድል መገኘቱን አስረድተዋል። በሐዋርያዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት የታየው ለውጥ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፈጠረው እንቅፋት ሳይሆን የአገሩን እና የምዕመናን ማኅበረሰብ የደረሰበት የማኅበራዊ ሕይወት ደረጃን የተከተለ መሆኑን አስረድተዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ምዕመናን ከማኅበራዊ ግንኙነት ታግደው በዝግ እንዲቀመጡ በመገደዳቸው የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ተቋርጦ መቆየቱ፣ በጣሊያን ውስጥ ቀድሞውኑ የሚታየውን የእሑድ ዕለት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ተሳትፎ ተዳክሞ መቆየቱ ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፣ በየእሑዱ የሚካሄደው የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት የሚዳከመው በባሕል መመሳሰል፣ በቁምስና ሕይወት ውስጥ ውህደትን ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ሲዳከም እና የመንፈሳዊ አገልግሎቶች የምሕረት ተልዕኮን ወደ ሁሉም አካባቢዎች ለማድረስ የሚደረግ ጥረት እንቅፋት ሲያጋጥመው እንደሆነ አስረድተዋል።             

25 August 2021, 16:44