ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ችግር ውስጥ ከወደቁ የሮም ከተማ ነዋሪዎች ጋር በምሳ ግብዣ ላይ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ችግር ውስጥ ከወደቁ የሮም ከተማ ነዋሪዎች ጋር በምሳ ግብዣ ላይ 

የሚገባውን ዕርዳታ ማግኘት መብት እንጂ ምጽዋዕት መቀበል አለመሆኑ ተነገረ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሮም ከተማ የሚገኙ ድሆችን ለመርዳት በማሰብ በግል የገንዘብ ወጭ ያቋቋሙት ዕርዳታ ሰጭ ማኅበር የሚፈለገውን አገልግሎት በማበርከት መልካም ውጤቶችን ማስመዝገቡን የሮም ሀገረ ስብከት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጃንፔሮ ፓልሚዬሪ ገልጸዋል። በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ምኞት የተቋቋመው እና “ኢየሱስ መለኮታዊ ሠራተኛ” በመባል የሚታወቅ የዕርዳታ መስጫ ድርጅት ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ድሃ ቤተሰቦችን ፍላጎት ሟሟላት መቻሉን ሊቀ ጳጳሱ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቁጥራቸው ከ2500 በላይ የሚሆኑ የሮም ከተማ ነዋሪዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች፣ ከእነዚህም መካከል በተለይ በሥራ እጦት ምክንያት ቤተሰቦች ለችግር መጋለጣቸው ታውቋል። በሮም ሀገረ ስብከት ውስጥ በስፋት እየታየ ያለውን ከፍተኛ ማኅበራዊ ችግር በመገንዘብ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከአንድ ዓመት በፊት፣ “ኢየሱስ መለኮታዊ ሠራተኛ” የተባለ የዕርዳታ መስጫ ድርጅት ማቋቋማቸው ይታወሳል። የዕርዳታ መስጫ ድርጅታቸውን አቅም ለማሳደግ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የመጀመሪያውን የአንድ ሚሊዮን ዩሮ ዕርዳታ መለገሳቸው ይታወሳል። ከእርሳቸው ድጋፍ በተጨማሪ “ሮምን ለማገዝ እንተባበር” በሚል ዕቅድ፣ የላሲዮ ክልል እና የሮም ከተማ ማዘጋጃ ቤት፣ በሮም ከተማ የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ወደ ሁለት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ ዩሮ የሚሆን የገንዘብ ዕርዳታ በማሰባሰብ በሮም ከተማ የሚገኙ ድሃ ቤተሰቦችን እና ግለሰቦችን መርዳት መቻሉን የሮም ሀገረ ስብከት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጃንፔሮ ፓልሚዬሪ አስረድተዋል።

ከሰዎች በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ዓላማን ማሳካት መጀመር

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የመሰረቱት “ኢየሱስ መለኮታዊ ሠራተኛ” የተባለ ዕርዳታ መስጫ ድርጅት ለ920 ቤተሰቦች እና በጠቅላላው ለ2500 ሰዎች ዕርዳታ በማድረግ ከደረሰባቸው ችግር እንዲወጡ ማድረጉ ታውቋል። የዕርዳታ አገልግሎቱ በተለይ የገንዘብ ዕርዳታ ከማድረግ በተጨማሪ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 30 ከሞቶ ለሚሆኑ የሥራ ዕድልን በማመቻቸት ወደ ሥራው ዓለም እንዲገቡ ማድረጉን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃንፔሮ አስረድተዋል። የዕርዳታ ድርጅቱ በሁለተኛ እቅዱ በላሲዮ ክፍለ ሀገር እና በሮም ከተማ ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት፣ ተቋማት እና ግለ ሰቦች ተባብረው በሚያቀርቡት የገንዘብ ድጋፍ ድርጅቱ የዕርዳታ አገልግሎቱን ተግባራዊ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል።

በሮም ከተማ ውስጥ የሚታዩ መሠረታዊ ችግሮች በመኖሪያ ቤት እጦት እና በዝቅተኛ የወር ገቢ ብቻ ተወስኖ የሚቀሩ ሳይሆን በእርግጥ ከሥራ ማጣት ጋር የተያያዘ መሆኑን ያስረዱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃንፔሮ ፣ ፍትሃዊ ክፍያ ያለበት የሥራ ዕድል ሲገኝ ሌሎችም ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ መሆኑን ገልጸዋል።

በሮም የሚገኝ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የዕርዳታ ድርጅት ሠራተኞች እንደ ዋና መመሪያቸው ወስደው በሚከተሉት “ፍትሃዊ ዕርዳታን ማግኘት እንደ ምጽዋት ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም” በሚለው ሃሳብ፣ የዕርዳታ ድርጅቱን በገንዘብ የሚደግፉት ተውቋማት እና የድርጅቱ ሠራተኞች በሙሉ የተዘጋጀላቸውን የ“መብት መመሪያዎችን” በማክበር፣ መንግሥት በየጊዜው የሚያወጣቸውን የአስቸኳይ ጊዜ ገቢ ፣ የዜግነት ገቢ እና የልዩ ልዩ ድጎማ ደንቦችን ተከትለው ወደ ዕርዳታ መስጫ ጣቢያዎች እና ካቶሊካዊ ቁምስናዎች የሚመጡ ድሃ ቤተሰቦችን እና ችግረኛ ግለሰቦችን የሚረዱ መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጃንፔሮ አስረድተዋል። በሮም ከተማ ውስጥ የሚገኙ ካቶሊካዊ ቁምስናዎች ከደሃ ቤተሰቦች እና ግለሰቦች የሚቀርቡ የዕርዳታ ጥያቄዎችን ተቀብለው ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚመራ “ካሪታስ” የተሰኘ የቸርነት ሥራ ድርጅት በክፍለ አገሩ በተዋቀሩ ከ75 ማዕከላት በላይ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ተቀብሎ የዕርዳታ ተግባራትን የሚያከናውን መሆኑን ገልጸዋል።

ጠንካራ የተስፋ ስሜት የሚመነጭበት ፕሮጀክት ...

የሮም ሀገረ ስብከት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጃንፔሮ ፓልሚዬሪ፣ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ ማኅበራዊ ችግር ብቻ አይደለም ብለው፣ በሮም ከተማ ውስጥ የሚገኙ ለችግሩ ይበልጥ የተጋለጡ አቅመ ደካሞችን ጨምሮ የከተማው ካቶሊካዊ ቁምስናዎች እና ምዕመናን ትኩረት ሊደረግላቸው የሚገባ መሆኑን አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጃንፔሮ አክለውም፣ ወረርሽኙ ባስከተለው ቀውስ የተጎዱ፣ ከሥር የሚገኙ ባሕላዊ ተቋማት እና እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል። በመሆኑንም መንግሥታዊ ተቋማት እና የቤተክርስቲያን ድርጅቶች ዋና ተግባር በተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች የተጎዱ ቤተሰቦችን እና ግለሰቦችን ማገዝ እና  መርዳት በመሆኑ፣ እነዚህን እጅግ ውድ የሆኑ ተቋማትን ለማጠናከር ማኅበረሰቡ የበኩሉን አስተዋጽዖን በማድረግ እንዲያበረታታቸው በማለት አሳስበዋል።

09 August 2021, 14:29