ፈልግ

የቅዱስ መስቀል ወዳጅ የነበረች የቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ የቅዱስ መስቀል ወዳጅ የነበረች የቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ  

ቅድስት ተሬዛ፣ አለመቻቻልን የመቃወም ስጦታ የነበራት ሰው መሆኗ ተገለጸ

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ነሐሴ 3/2013 ዓ. ም የቅዱስ መስቀል ወዳጅ የነበረች የቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ ዓመታዊ ክብረ በዓልን ማክበሯ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዕለቱን በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ በቃሏ የጸናች፣ እግዚአብሔርን በንጹህ ልብ የምትፈልግ፣ በአይሁድ እና በክርስቲያን ሕዝቦቿ መካከል ፍቅርን በተግባር የገለጸች ሰማዕት መሆኗን አስታውሰዋል። አክለውም “የቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ የፍቅር ብርሃን የአህጉሩ ባልደረባ በሆንችበት በአውሮፓ ውስጥ እስከ ዛሬ የሚበራ፣ ለዛሬው ዓለማችንም ብዙ መልዕክቶችን ማስተላለፍ የምትችል ደፋር ሴት ናት” በማለት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ በቤተክርስቲያን ዘንድ ትልቅ ፍቅር የሚሰጣት፣ እምነቷን በድፍረት መመስከር የቻለች፣ ፍቅርን በመግለጽ በጨለማ ውስጥ ብርሃን መሆን ያቻለች በማለት የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ መግለጻቸ ይታወሳል። እ. አ. አ በ1881 ዓ. ም በጀርመን ስሌሲያ በተባለ አካባቢ ከአይሁድ ቤተሰብ የተወለደችው ኤዲት ስታይን ወይም ቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ ፈላስፋ እና በኋላም ከአይሁድ እምነት ሳትወጣ በአቪላ ቅድስት ተሬዛ ሕይወት በመማረክ የካቶሊክ እምነትን መቀበሏ ይታወሳል።

ቀጥሎም የቅዱስ መስቀል ወዳጅ ተሬዛ ቤነዴታ የሚል ስም በማግኘት በናዚዎች ጦርነት ጊዜ ወደ ሆላንድ በመዛወር የቀርሜሎሳዊያን ደናግል ማኅበር አባል መሆኗ ይታወሳል። ተሬዛ ቤነዴታ በኤክት ውስጥ ቀርሜሎስ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በመጽሐፍ ጽፋ ካባስቀመጠችው መልዕክት፣ በእውነተኛ ሰላም መማረኳን እና በክርስቶስ ተቃዋሚ መንግሥት ላይ የደረሰውን ሽንፈት በመግለጽ መጻፏን ለመረዳት ተችሏል።  ተሬዛ ቤነዴታ ወደ ሆላንድ ከተዛወረች ከሁለት ዓመታት በኋላ እ. አ. አ በ1940 ዓ. ም. እርሷ የነበረችበትን አገር የናዚ ጦር በመውረሩ አብሯት ከነበሩ 244 የአይሁድ ዝርያ ካላቸው ካቶሊካዊ እህቶች ጋር በጀርመን ውስጥ ወደሚገኝ አውሽዊትዝ መምጣቷ ይታወሳል። በዚህ የሰዎች ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የካቶሊክ እምነትን ከተቀበለች ሮዛ ከምትባል እህቷ ጋር አብረው መሞታቸው ይታወሳል። 

ፍቅር ህመምን ይፈውሳል

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ. በጥቅምት 11/1998 ዓ. ም የተሬዛ ቤነዴታን ቅድስና ባወጁበት ዕለት “ቅዱስ መስቀልን ለማወቅ የሚደረግ ጉዞ” በማለት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ፍቅር ህመምን እንዴት ፍሬያማ እንደሚያደርግ መናገራቸው ይታወሳል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በቀጣዩ ዓመት ተሬዛ ቤነዴታን ከሲዬና ቅድስት ካታሪና እና ከስዊድን ቅድስት ብሪጅድ ጋር የአውሮፓ ባልደረባ አድርገው ማወጃቸው ይታወሳል። በቅርቡ “Città Nuova” በመባል የሚታወቅ ማተሚያ ቤት “የኢዲት ስታይን የተሟላ ሥራዎች” የሚለውን ተከታታይ ጽሑፍ አትሞ ይፋ ሲያደርግ፣ በሮም የላተራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የዘመናዊ ፍልስፍና ታሪክ መምህር እና በጣሊያን የኤዲት ስታይን ማህበር ፕሬዝዳንት፣ ፕሮፌሰር አንጄላ አሌስ ቤሎ ሃላፊነትን ወስደው ለህትመት ማብቃታቸው ይታወሳል።  

ፕሮፌሰር አንጄላ አሌስ ቤሎ ስለ መጽሐፉ ሲገልጹ፣ መጽሐፉ በርካታ መልዕክቶችን የያዘ መሆኑን ገልጸው፣ ይህን በሚገባ ለመረዳት የታሪክ መስክን መመልከት ጠቃሚ እንደሆነ አስረድተው፣ “የታሪክ መስክ እውነትን ከማሳየት በተጨማሪ የሰዎችን መልካም አብነት የሚገለጽ በመሆኑ ከዚህም ጋር በተያያዘ የመልካም አብነት ተዋናዮችንም መመልከት ጠቃሚ ነው” ብለዋል። በማከልም “ኤዲት ስታይን ያቀረበችው ‘ማህበረሰብ’ የሚለው ጽንሰ-ሀሳብ አስፈላጊ ነው” ብለዋል። ማህበረሰብ ማለት መተባበርን እና የጋራ ሃላፊነት መውሰድን የሚገልጽ መሆኑን አስረድተው፣ “ይህ መልዕክት  መሠረቱን በሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ያደረገ፣ በአይሁድ እና በክርስቲያን እምነቶች ልኬት ላይ የተመሠረተ ሞራላዊ መልዕክት ነው” በማለት አብራርተዋል። 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ነሐሴ 3/2013 ዓ. ም የተከበረውን የቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ ዓመታዊ ክብረ በዓልን በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ የቅዱስ መስቀል ወዳጅ የነበረች፣ በቃሏ የጸናች፣ እግዚአብሔርን በንጹህ ልብ የምትፈልግ፣ በአይሁድ እና በክርስቲያን ሕዝቦቿ መካከል ፍቅርን በተግባር የገለጸች ሰማዕት ናት” ማለታቸውን ፕሮፌሰር አንጄላ አሌስ ቤሎ አስታውሰዋል። ከቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ የሕይወት ታሪክ ለመረዳት እንደቻሉት፣ እጅግ አስቸጋሪ እና አስፈሪ የናዚ ጦርነት ወቅት ቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ ያሳየችው የእምነት ጽናት እና ድፍረት እንዲሁም ከቤተሰቦቿ ፍላጎት ወጥታ ወደ ካቶሊክ እምነት መምጣቷ ድፍረቷን እና ቆራጥነቷን ይገልጻል ብለዋል። የሚደርስባትን ስቃይ መቋቋም መቻሏ በእምነቷ ላይ የሚደርስ ማንኛውንም መከራ በትዕግስት ለመሸከም የሚያስችላት ውስጣዊ ሰላም ያላት መሆኑን ያሳያል ብለዋል። የቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ ጽናት የሞራል ጥንካሬ ምሳሌ ሊሆነን እንደሚገባ ፕሮፌሰር አንጄላ አሌስ ቤሎ ገልጸው፣ ቅድስት ተሬዛ ቤነዴታ በጽሑፍ አስፍራ ባስቀመጠቻቸው መልዕክቶቿ፣ ሁሉንም የሕይወት አሉታዊ ገጽታዎችን መቋቋም የሚቻለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ብቻ እንደሆነ መግለጿን አስታውሰዋል።

ፕሮፌሰር አንጄላ አሌስ ቤሎ በመጨረሻም፣ “ኢየሱስ በፍቅሩ እና በሞቱ ጊዜ ውስጣዊ ጥንካሬ እንዳሳየን ሁሉ፣ ኤዲት ስታይን ወይም ቅድስት ተሬዛ ቤነዴታም ኢየሱስን በመምሰል ያሳየችን ምስክርነት ቅድስናዋን ለመወሰን አስፈላጊ የሕይወቷ ታሪክ አካል እንደሆነ አምናለሁ” ብለዋል።

10 August 2021, 15:59