ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በኅዳር ወር 2019 ዓ. ም ወደ ጃፓን እና ታይላንድ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በኅዳር ወር 2019 ዓ. ም ወደ ጃፓን እና ታይላንድ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት  

አቡነ ዮሴፍ ሚጿኪ ከአቶሚክ ቦምብ ጥቃት ወደ ሰላም የኦሎምፒክ ውድድሮች መሸጋገር መቻሉን ገለጹ

እ. አ. አ ነሐሴ 6/1945 ዓ. ም. በሂሮሺማ እና በናጋሳኪ ከተሞች የተፈጸሙትን የአቶሚክ ቦምብ ጥቃቶች ዓርብ ሐምሌ 30/2013 ዓ. ም በጃፓን እና መላው ዓለም ታስቦ መዋሉ ታውቋል። ዕለቱ ታስቦ የዋለው በጃፓን ሲካሄድ የቆየው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ውድድር ከመፈጸሙ ከሁለት ቀናት በፊት መሆኑ የናጋሳኪ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ሚጿኪ ታካሚ ገልጸው፣ የኦሊምፒክ ውድድሮች ዝግጅት እያንዳንዱ አገር የኑክሌር ጦር መሣሪያን በመያዝ እውነተኛ ሰላምን መገንባት የማይቻል መሆኑን የሚያስገነዝብ ዝግጅት መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ኒውክሌር የጦር መሣሪያ በጃፓን ውስጥ ከፍተኛ ውድመት ማስከተሉን ዓለም ከተገነዘበ 76 ዓመታት ተቆጥረዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ እ. አ. አ ነሐሴ 6 እና 9/1945 ዓ. ም. አሜሪካ በሁለቱ የጃፓን ከተሞች፣ በሂሮሺማ እና በናጋሳኪ በፈጸመችው የኒውክሌር መሣሪያ ጥቃቶች ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል። አንዳንድ ምንጮች በጥቃቱ ወደ 200 ሺህ ሰዎች እንደተደሉ ይናገራሉ። አሜሪካ በጃፓን ከተሞች የፈጸመችው የኒውክሌር መሣሪያ ጥቃት በጦርነት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው መሆኑ ቢነገርም፣ ነገር ግን በብዙ አገራት የሚታይ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ምርት እና ባለቤትነት የዓለማችንን ሰላምን አደጋ ላይ መጣሉን ያመላክታል ተብሏል።

ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ምስክርነት

ዓርብ ሐምሌ 30/2013 ዓ. ም  ዕለቱን በማስታወስ በጃፓን ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 2፡15 ደቂቃ ላይ የሕሊና ጸሎት መደረጉ ታውቋል። ይህ ሰዓት አሜሪካ አቶሚክ የጦር መሣሪያን ተጠቅማ በሂሮሺማ ከተማ በመፈጸመችው ጥቃት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደሏን የሚያሳይ ነው ተብሏል። ጥቃቱ ከተፈጸመ ከአሥራዎቹ ዓመታት በኋላም የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች አስከፊ ውጤቶች መታየቱ ተገልጿል። ዕለቱን ለማስታወስ በሂሮሺማ ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ የሰላም አደባባይ የመጡ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የታዳሚው ቁጥር ዝቅ እንዲል መደረጉ ታውቋል። 86 አገራትን የወከሉ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ እንግዶች በሂሮሺማ የሰላም አደባባይ መገኘታቸው ታውቋል። የሂሮሺማ ከተማ ከንቲባ ክቡር አቶ ካዙሚ በሥፍራው ለተገኙት እንግዶች ባሰሙት ንግግር፣ በኮቪድ-19 ወረርሽን ምክንያት ኒውክሌር የጦር መሣሪያ መስፋፋትን በመቃወም ወደ ስምምነት ለመድረስ የሚደረግ ድርድር እንደገና እንዲቀጥል መንግሥታትን አሳስበዋል። ጃፓን የአቶሚክ የጦር መሣሪያ ሰለባ ብቸኛ ሀገር ብትሆንም ስምምነቱን ያላጸደቀች መሆኑ ታውቋል።            

ሰላም የሚገኘው የጦር መሣሪያ ትጥቅን በመፍታት ብቻ ነው

ጃፓን ያሳለፈቻቸውን አስከፊ የጦርነት ዓመትን እና የሞቱባትን ከፍተኛ የሰው ቁጥር በማስታወስ፣ ለዓለም በሙሉ “ከእንግዲህ ጦርነት ይብቃ” በማለት ድምጿን የምታሰማ መሆኗ ታውቋል። ድንበርን እና ትውልድን አቋርጦ ግለሰቦች ፣ ዜጎች እና ገዥዎች ለሰላም ባላቸው ጥማት፣ ኒውክሌር የጦር መሣሪያ እንዳይሰራጭ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ፣ ይህን በማድረግ በዓለም ላይ አውዳሚ እና አደገኛ የጦር መሣሪያ ያላቸው አገሮች ቁጥር እንዲቀንስ ጥረት መደረግ እንዳለበት ተነግሯል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በኅዳር ወር 2019 ዓ. ም ወደ ጃፓን እና ታይላንድ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ አቶሚክ ኃይልን ለጦርነት ዓላማ ማዋል “በሰው ላይ ብቻ ሳይሆን በክብሩ ጭምር የሚፈጸም ወንጀል” እንደሆነ ገልጸው፣ “በጋራ መኖሪያ ምድራችን ውስጥም በሚኖር ማንኛውም የወደፊት ዕድል ላይ የተቃጣ” ወንጀል ሲሉ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው፣ እውነተኛ ሰላም የሚገኘው የጦር መሣሪያ ትጥቅን የፈቱ ጊዜ ነው ብለው፣ ዛሬ በሕይወት የሌሉ ሰዎች ጩኸት ማሰማታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።

የኦሎምፒክ ነበልባል “ከእንግዲህ ቦምብ ሊኖር አይገባም” ይለናል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሁለት ዓመታት በፊት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ወደ ጃፓን ሲገቡ አቀባበል ያደረጉላቸው የናጋሳኪ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ሚጿኪ ታካሚ እንደነበሩ ይታወሳል። የናጋሳኪ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ሚጿኪ፣ በጃፓን ሲካሄድ የቆየው የኦሊምፒክ ጨዋታ ውድድሮች ማጠናቀቂያ ዋዜማ ላይ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ ማድረጋቸው ታውቋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ በቃለ ምልልሳቸው፣ እውነተኛ እና ተጨባጭ ሰላምን ለመገንባት የኒውክሌር ትጥቅ ማስፈታት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ውድድር ስፖርታው በዓል ቢሆንም በዓለም ውስጥ ሰላምን ለመፍጠርም ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን አስረድተዋል። ምንም እንኳን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ብዙ ሰዎች በውድድሩ ላይ መሳተፍ ባይችሉም፣ አጋጣሚው በጣም አስፈላጊ እንደነበር ገልጸው፣ በውድድሮቹ መካፈል መልካም በመሆኑ ፣ ጥሩ ድባብን እና ብዙ ጉጉት ያመጣል ብለዋል። አስፈላጊነቱን በመግለጽ ምስክርነታቸውን የሚስጡ ሰዎች ቁጥር በየዓመቱ እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም፣ ውድድሮቹ በሕጻናት ልብ ውስጥ የማይጠፉ ልምዶችን አስቀምጠው እንደሚያልፉ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መናገራቸውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ አስታውሰዋል። ይህን ታሪካዊ ሥነ-ሥርዓትን ወደ ሕዝብ ዘንድ ለማቅረብ የሲኒማ ፣ የሥነ ጽሑፍ እና የመገናኛ ብዙሃን አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን አስርድተው፣ ማህደረ ትውስታውን ለማቆየት ጥረትን ማድረግ መቀጠል አለብን ብለዋል።

ይህን እንዳናደርግ የሚከለክል የጋራ ችግር አለብን ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ፣

እጅግ አደገኛ የሆነውን የአቶሚክ ኃይልን ማውገዝ አለብን ብለው፣ የኒውክሌር ኃይል በአንድ መልኩ አስፈላጊ ቢሆንም አደገኛ የሆነውን የኒውክሌር ኃይል በሌላ ኃይል መተካት ያስፈልጋል ብለዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ኒውክሌር የጦር መሣሪያዎችን ይዘን እውነተኛ ሰላምን ማስፈን ስለማንችል ከምድራችን ገጽ ማጥፋት ይኖርብናል ማለታቸውን፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ አስታውሰዋል። እ. አ. አ ከዘንድሮ ጥር 22/2021 ዓ. ም ጀምሮ ኒውክሌር የጦር መሣሪያን መጠቀም በሕግ የተከለከለ መሆኑን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ በማጽደቁ ሂደት ላይ ያልተሳተፉ ብዙ አገሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በዘንድሮ የቶኪዮ ውድድር የስደተኛ አትሌቶች ቡድን አለ

ሊቀ ጳጳሱ ዘንድሮ በቶኪዮ ከተማ በተካሄደው የኦሊምፒክ ውድድሮች የስደተኛ አትሌቶች ቡድን መኖሩን ገልጸው፣ ይህም ዛሬ በዓለማችን ውስጥ በርካታ ግጭቶች መኖራቸውን ያስታውሰናል ብለው፣ የኦሊምፒክ ውድድሮች ሰላም የሚገኝበትን ዓለም ለመፍጠር በአገራት መካከል ፈቃደኝነት መኖሩን ይመሰክራል ብለዋል።

07 August 2021, 16:38