ፈልግ

በእመቤታችን ማርያም ቤተ መቅደስ የተደረገ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት (ቤኒን) በእመቤታችን ማርያም ቤተ መቅደስ የተደረገ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት (ቤኒን) 

በቤኒን ወደሚገኝ የእመቤታችን ቤተ መቅደስ የሚደረግ መንፈሳዊ ጉዞ መጀመሩ ተገለጸ

በምዕራብ አፍሪካ አገር ቤኒን፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የቆየው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ የሚደረግ መንፈሳዊ ጉዞ መጀመሩ ታውቋል። ከቤኒን እና አጎራባች አገሮች ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆኑ ምዕመናን በአገሪቱ ወደሚገኝ የአሪግቦ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ የሚያደርጉትን መንፈስዊ ጉዞ (ንግደት) ከዚህ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ማካሄድ እንደሚቻል የብሔራዊ ጤና ባለሥልጣን ያወጣው መመሪያ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

67ኛውን  የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ከጳጳሳት ጋር ሆነው የመሩት በናይጄሪያ የአቡጃ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦሎሩንፌሚ ኦናይዬካን መሆናቸው ታውቋል። ያለፈው እሑድ ለመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የተዘጋጀውን መጽሐፍ በመጥቀስ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦሎሩንፌሚ በክብረ በዓሉ ላይ ያቀረቡትን ስብከተ ወንጌል በሦስት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ መመስረቱን አስታውቀዋል። የቤኒን እና ጎረቤት አገሮች ካቶሊካዊ ምዕመናን የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደ መሆናቸው፣ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ በሚያደርጉት መንፈሳዊ ጉዞ እምነታቸውን በእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንዲያደርጉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንዲያውቁ የሚያደርግ የእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል። እምነትን ከእግዚአብሔር የተቀበልን በሙሉ የእምነት ስጦታን አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁል ጊዜ ልናውቀው እና በተግባር ልንኖረው ይገባል ብለዋል። አክለውም፣ ምእመናን ከስግብግብነት፣ ከአጉል እምነት፣ ለእግዚአብሔር እና ለጎረቤት ፍቅርን ከማጉደል እንዲቆጠቡ፣ እግዚአብሔርን ከመራቅ ከሚመጣ ጥላቻ፣ ሙስና፣ ግጭቶት እና ራስ ወዳድነት መራቅ እንዳለባቸው አሳስበው፣ “አፍሪካ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነትን ለማድረግ ተጠርታለች” ብለዋል።

የቤተሰብ ሚና

እምነት በግለሰብ ደረጃ የሚቀርብ እንዳልሆነ ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦሎሩንፌሚ፣ ነገር ግን ቤተሰቦች እምነትን በማስተላለፍ እና በማሰራጨት ከፍተኛ ሚና ያላቸው መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ሚናቸው በተግባር ሳይገለጽ መቅረት የለበትም ብለዋል። በአፍሪካ ውስጥ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤተሰብ በመሆኑ ቤተሰብ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከእግዚአብሔር እጅ የተቀበለውን የቤተሰብ ተቋም እና የጋብቻ ቅዱስነት በመደገፍ፣ የምስክርነት ተልእኮውን በተግባር መግለጽ እንደሚኖርበት፣ መልካም ካቶሊካዊ ቤተሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ በጨለማ ውስጥ እንደሚበራ ብርሃን ይታያል” ብለው፣ ይህ በሁሉም ዘንድ ሊደነቅ የሚችል አምሳያነት መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦሎሩንፌሚ ገልጸው፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉም ነገር የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦሎሩንፌሚ በመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ የቤኒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አባላት፣ በቤኒን የቅድስት መንበር እንደራሴ ሞንሲኞር ማርክ ጄራርድ ማይልስ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ካህናት መሳተፋቸው ታውቋል።

በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ተወካዮች፣ የብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፣ የብሔራዊ ሕገ መንግሥት ኮሚሽን ተወካዮች፣ የአስተዳደር እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዲሁም ባህላዊ መሪዎች ተገኝተዋል። በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የቤኒን ሀገረ ስብከቶች ወጣቶች በተለያዩ ቋንቋዎች ዝማሬአቸውን አቅርበዋል። ከመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ቀጥሎ በነበረው ዝግጅት በርካታ ምዕመናን ጸሎታቸውን እስከ ምሽት ድረስ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ዘንድሮ የተዘጋጀው ክብረ በዓል መሪ ቃል፣ በወንጌል ምስክርነት ብርሃን ሆና በምትረዳን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ሁላችንም ወንድማማቾች እና እህትማማቾች ነን” የሚል መሆኑ ታውቋል።  

24 August 2021, 16:27