ፈልግ

የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም ዓመታዊ በዓል በቫቲካን በተከበረበት ወቅት የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም ዓመታዊ በዓል በቫቲካን በተከበረበት ወቅት   (AFP or licensors)

የሰኔ 27/2013 ዓ.ም የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም የሚከበርበት እለተ ሰንበት የቅዱስ ወ.

“ቅዱስ ቁርባን የኃጢአተኞች እንጀራ እንጂ የቅዱሳን ሽልማት አይደለም”

የእለቱ ንባባት

1.      ኦ. ዘፀዐት 24፡3-8

2.    መዝ. 115

3.    ዕብራዊያን 9፡11-15

4.    ማርቆስ 14፡12-16፣22-26

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የጌታ እራት

የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያው ቀን፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ ውሃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤትም ተከተሉት፤ የቤቱንም ጌታ፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የትኛው ነው?’ ብሎአል በሉት፤ እርሱም በሰገነቱ ላይ የተሰናዳና የተነጠፈ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁልን።” ደቀ መዛሙርቱም ወጥተው ወደ ከተማዪቱ ሄዱ፤ ማንኛውም ነገር ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካውንም አሰናዱ።

ሲበሉም እንጀራ አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸውና፣ “እንኩ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው፣ ጽዋውንም አነሣ፤ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከዚያ ጠጡ። ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ እስከምጠጣበት እስከዚያች ቀን ድረስ ዳግም ይህን አልጠጣም።” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ዛሬ የክርስቶስ ሥጋ እና ደም የሚታወስበት ዓመታዊ በዓል ይከበራል። ቅዱስ  ወንጌል የመጨረሻው እራት (ማርቆስ 14: 12-16.22-26) በምን መልኩ እንደ ተከናወነ የሚገልጽ ዘገባ ያቀርብልናል። የጌታ ቃሎች እና ምልክቶች ልባችንን ይነኩ- “እንጀራ አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸውና፣ “እንኩ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው” (ማርቆስ 14፡22)።

ኢየሱስ እንዲህ ባለ ቀልል ባለ መልኩ ነበር ታላቅ የሆነውን ምስጢረ ቅዱስ ቁራባንን የሚሰጠን። የእሱ ትሁት የሆነ ስጦታ፣ የመጋራት ምልክት ነው። በሕይወቱ መጨረሻ አከባቢ ላይ ሕዝቡን ከራብ ለማስታገስ አስቦ ያከፋፈለው እንጀራ ሳይሆን ነገር ግን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በፋሲካ በዓል ላይ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ያቀርባል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ የሕይወት ግቡ ራስን ለሌሎች አሳልፎ መስጠት መሆኑን ያሳየናል ፣ ትልቁ ነገር ማገልገል መሆኑን ይገልጽልናል። እናም ዛሬ የእግዚአብሔርን ታላቅነት በአንድ ቁራሽ እንጀራ ውስጥ በፍቅር ውስጥ እናገኛለን። አቅመ ቢስ የሚለው ቃል ላይ አፅንዖት ለመስጠት እፈልጋለሁ። ኢየሱስ እንደሚፈረፈር እና እንደሚቆረስ እንጀራ ሆኖ ራሱን አቅመ ቢስ አድርጎ ያቀርባል። ነገር ግን በትክክል ጥንካሬው ፣ በአቅመቢስነቱ ውስጥ ይገኛል። በቅዱስ ቁርባን ውስጥ አቅበ ቢስነት ጥንካሬ ነው- ተቀባይነት ለማግኘት እና ፍርሃትን ለማስወገድ ራሱን ዝቅር አድርጎ የተገለጸ የፍቅር ጥንካሬ፤ ለመመገብ እና ሕይወትን ለመስጠት የሚቆራረስ እና የሚከፋፈል የፍቅር ኃይል፣ ሁላችንንም ወደ አንድነት ለማምጣት የሚቆረስ የፍቅር ጥንካሬ ነው።

እናም በቅዱስ ቁርባን አቅመ ቢስነት ውስጥ ጎልቶ የሚወጣ ሌላ ጥንካሬ አለ-ስህተት የሚሠሩትን የመውደድ ጥንካሬ። ኢየሱስ የሕይወት እንጀራ የሰጠን በተከዳበት ሌሊት ነው። በልቡ ውስጥ ጥልቅ የሆነውን ትልቅ ገጠመኝ እየተጋፈጠ በነበረበት ወቅት ነበር ትልቁን ስጦታ የሰጠን-አብሮ ከእርሱ ጋር እየተመገበ የነበረው እና ከእርሱ ጋር በወጪቱ ውስጥ እያጠቀሰ ይመገብ የነበረው ደቀ መዛሙርት ሊከዳው እየተዘጋጀ ነው። እናም ክህደት ከሚወዱት ሰው ሲመነጭ እጅግ ትልቅ ሥቃይ ነው። እና ኢየሱስ ምን አደረገ? እሱ ለክፉ ነገር እጅግ በጣም ከፍ ያለ በጎ ምላሽ ይሰጣል። ለይሁዳ “አይሆንም” ለሚለው ምላሽ በምህረቱ “አዎ” ብሎ ይመልሳል። ኃጢአተኛውን አይቀጣም ፣ ነገር ግን ነፍሱን ለእርሱ ይሰጣል ፣ ለእርሱ ዋጋ ይከፍላል። ቅዱስ ቁርባንን ስንቀበል ኢየሱስ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ነገር ያደርጋል እርሱ ያውቀናል ፣ እኛ ኃጢአተኞች እንደሆንን ያውቃል እና በጣም የተሳሳትን መሆናችንን ያውቃል ፣ ነገር ግን ህይወቱን ከእኛ ጋር ለመቀላቀል አይታክትም። እኛ እንደሚያስፈልገን ያውቃል፣ ምክንያቱም ቅዱስ ቁርባን የቅዱሳን ሽልማት አይደለም ፣ በፍጹም እንዲህ አይደለም። እርሱ የኃጢአተኞች እንጀራ ነው እንጂ። ለዚህም ነው “አትፍሩ! ወስዳችሁ ብሉ” በማለት የሚመክረን።

የሕይወትን እንጀራ በተቀበልን ቁጥር ኢየሱስ ለአቅመ ቢስነታችን አዲስ ትርጉም ለመስጠት ይመጣል። እኛ ከምናስበው በላይ በእርሱ ዘንድ ውድ እንደሆንን ያስታውሰናል። ድክመቶቻችንን ለእርሱ ብናካፍለው ደስተኛ መሆኑን ይነግረናል። ምህረቱ የእኛን ኃጢአቶች እንደማይፈራ በድጋሚ ይነግረናል። የኢየሱስ ምህረት የእኛን ኃጢአት አይፈራም። እና ከሁሉም በላይ እኛ በራሳችን ልንፈውሳቸው ከማንችላቸው ከእነዚያ ድክመቶች በፍቅር ይፈውሰናል። ምን ዓይነት ድክመቶች? ብለን እናስባለን። ለጎዱን ሰዎች ቂም የመያዝ ስሜት - ከዚህ ዓይነቱ ስሜት በርሳችን ችሎታ ብቻ ልንፈወስ አንችልም፣ ራሳችንን ከሌሎች በመለየት እና እራሳችንን ማግለል - ከእዚህ ዓይነቱ በሽታ በራሳችን ኃይል ብቻ ልንፈወስ አንችልም፣  በእራሳችን ላይ ማልቀስ እና በማጉረምረም ሰላም ሳያገኙ መኖር፣ ከእዚህም ዓይነቱ በሽታ በራሳችን ኃይል ብቻ ልንፈወስ አንችልም። እርሱ ከእኛ ጋር በመገኘት፣ በእንጀራው ፣ በቅዱስ ቁርባን የሚፈውስ እርሱ ነው።    በእነዚህ ዓይነ በሽታዎች ላይ ቅዱስ ቁርባን ውጤታማ የሆነ መድሃኒት ነው። በእርግጥም ፣ የሕይወት እንጀራ ግትርነትን ይፈውሳል እና ወደ ትሁትነት ይለውጣቸዋል። የቅዱስ ቁርባን ቁስል ከኢየሱስ ጋር አንድነት ስላለው ይፈውሳል-የሕይወት አኗኗር ዘይቤአችን የእርሱን እንዲመስል፣ ለሌሎች መቆረስ እንችል ዘንድ እና እራሳችንን ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን አሳልፈን የመስጠት ችሎታችንን ከፍ በማደረግ ለክፉ ነገሮች ሁሉ በጥሩ ሁኔታ መልካም ምላሽ እንድንሰጥ ያደርገናል። ከራሳችን በመውጣት እና ለሌሎች ሰዎች ድክመቶች በፍቅር ራሳችንን ዝቅ ማደረግ እንችል ዘንድ ድፍረትን ይሰጠናል። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደሚያደርገው እኛም የሌሎች ሰዎችን ድክመት እንድንረዳ ያደረገናል። ይህ የቅዱስ ቁርባን አመክንዮ ነው- እኛን የሚወደን እና ድክመቶቻችንን የሚፈውስ ኢየሱስን የምንቀበለው ሌሎችን ለመውደድ እና በድክመቶቻቸው ውስጥ እነሱን ለመርዳት ነው። እና ይሄ በህይወት ዘመን ሁሉ ሊከናወን የሚገባው ጉዳይ ነው። ዛሬ በደገምነው የመዝሙረ ዳዊት ጸሎት ውስጥ አንድ ውዳሴ ጸልየናል - አራት ጥቅሶች የኢየሱስን አጠቃላይ ሕይወት ጠቅለል አድርገው ያቀረቡ ሲሆን በዚህም ኢየሱስ ሲወለድ በሕይወት ውስጥ ተጓዥ ጓደኛችን እንደ ሆነ ይነግሩናል። ከዚያ በእራት ውስጥ እንደ ምግብ ሆኖ ይሰጣል። ከዚያ በመስቀል ላይ ፣ በሞቱ ፣ ዋጋ ከፍሏል ለእኛ ከፍሏል። እናም አሁን እርሱ በመንግሥተ ሰማይ ሆኖ ሽልማት ሊሰጠን ተዘጋጅቷል፣ ዋጋችንንም ይከፍለናል።

እግዚአብሔር ሥጋ ነስቶስ ሰው የሆነበት ቅድስት ድንግል ማርያም የቅዱስ ቁርባን ስጦታን በምስጋና ልብ ለመቀበል እንዲሁም ሕይወታችንንም ስጦታ እንድርገን ለሌሎች መስጠት እንችል ዘንድ እንድትረዳን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል። ቅዱስ ቁርባን እኛ ሁላችን ራሳችንን ለሌሎች ስጦታ አድርገን ማቅረብ እንችል ዘንድ ይርዳን።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ በግንቦት 29/2013 ዓ.ም ካደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

03 July 2021, 11:02