ፈልግ

የማሊ ዋና ከተማ ባማኮ የማሊ ዋና ከተማ ባማኮ  (Mark Fischer)

በማሊ ውስጥ ታፍነው የተወሰዱት አባ ሌዎ ዱኞ ነጻ መለቀቃቸው ተነገረ

በመካከለኛው ማሊ፣ በሞፕቲ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት፣ የሴጌ ቁምስና መሪ ካህን የሆኑት ክቡር አባ ሌዎን ዱኞን ታፍነው ከተወሰዱ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ያለፈው ማክሰኞ ሐምሌ 6/2013 ዓ. ም ነጻ መለቀቃቸውን በአገሪቱ የካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ማኅበራዊ መገናኛ መምሪያ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፌርናንድ ኩሊቤሊ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመካከለኛው ማሊ የሴጌ ቁምስና መሪ ካህን ክቡር አባ ሌዎ ዱኞ ከአራት ምዕመናን ጋር ታፍነው የተወሰዱት ያለፈው ሰኔ 14/2013 ዓ. ም መሆኑ ይታወሳል። አባ ሌዎ እና አራቱ ምዕመናን ታፍነው የተወሰዱት በሳን ሀገረ ስብከት በተፈጸመው በክቡር አባ ኦስካር ቴራ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት በሄዱበት መሆኑ ታውቋል። በመካከለኛው ማሊ እስላማዊ ታጣቂዎች ለዓመታት ያህል አመጽ እና ሽብር ሲቀሰቅሱ፣ ብዙዎችንም ለሞት አደጋ ሲዳርጉ መቆየታቸው ይታወሳል። በማሊ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የማኅበራዊ መገናኛ መምሪያ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፌርናንድ ኩሊቤሊ፣ ከአፈናው ነጻ ከወጡት ከክቡር አባ ሌዎ ዱኞ ጋር መገናኘታቸውን አስታውቀዋል።

ክቡር አባ ሌዎ ዱኞን በአካል ማግኘት የቻሉት ክቡር አባ ኩሊቤሊ፣ ካህኑ ነጻ ከተለቀቁ በኋላ በጸሎት የረዷቸውን እና መልካምን ለተመኙላው በሙሉ ምስጋና ማቅረባቸውን ገልጸዋል። አክለውም የካህኑ ነጻ መለቀቅ ዜና ሲነገር መላው ሕዝብ ደስታውን በመግለጽ ወደ ፈጣሪው ምስጋናውን ማቅረቡን ክቡር አባ ኩሊቤሊ አስረድተው፣ በርካታ ምዕመናን የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ለማቅረብ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። የካህኑን ነጻ መለቀቅ በሰሙ ጊዜ ምስጋናቸውን በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ያቀረቡት ክብር አባ ኩሉቤሊ “እንደ አለመታደል ሆኖ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በማሊ ውስጥ የአፈና ተግባር ቁጥር እየጨመረ መጥቷል” ብለዋል።  

በአገሪቱ ሁኔታው አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል

በማሊ ውስጥ የአባ ሌዎ ዱኞ ታፍነው መወሰድ የመጀመሪያ እንዳልሆነ የገለጹት ክቡር አባ ኩሊቤሊ፣ በአገሪቱ የአፈና ተግባር እንዳልተገታ እና በአጎራባች አገር ቡርኪና ፋሶም የሚፈጸም መሆኑን አስረድተው፣ ይህን ተግባር የሚፈጽም ወገን ማንነት እና ለምን እንደሚፈጽም አይታወቅም ብለዋል። አክለውም አፈናው በተለይ በካህናት እና በደናግል ላይ ለምን እንደሚጸፈም ግልጽ አይደለም ብለዋል። ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአገሪቱ የተከበረች እና ድጋፍን ያገኘች መሆኗን ገልጸው፣ ቤተክርስቲያኒቱ በማሊ ውስጥ የምታቀርበው ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ አገልግሎቶች ሰፊ መሆናቸውን ክቡር አባ ኩሊቤሊ አስታውሰዋል። በሕዝቦች መካከል ፍቅር እንዲያድግ እናስተምራለን ያሉት ክቡር አባ ኩሊቤሊሁ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በማለት ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በክርስቲያን እና ሙስሊም ማኅበረሰብ ዘንድ ተግባራዊ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። በማሊ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የወንድማማችነት እና እህትማማችነት እሴቶችን ለማሳደግ በርትታ የምትሰራ መሆኗን ክቡር አባ ኩለቤሊ ገልጸው፣ በሌላ ወገን ይህ ዓላማ ተግባራዊ እንዳይሆን ጥረት የሚያደርግ ወገን መኖሩን ገልጸዋል።  “በማሊ ሕዝቦች መካከል መተማመን የለም” ያሉት ክቡር አባ ኩለቤሊ፣ ይህ ደግሞ ዜጎች መደበኛ እና ሰላማዊ ሕይወት እንዳይኖሩ ያደርጋቸዋል ብለዋል።     

17 July 2021, 15:13