ፈልግ

በጃፓን የባሕር ላይ አውሎ ነፋስ ያስከተለው አደጋ ሲታወስ በጃፓን የባሕር ላይ አውሎ ነፋስ ያስከተለው አደጋ ሲታወስ 

የጃፓን ምዕመናን ለአሥር ቀናት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት መዘጋጀታቸው ተገለጸ

በጃፓን የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን ሰላምን በመመኘት አሥር ቀናት የሚቆይ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ከሐምሌ 30 እስከ ነሐሴ 9/2013 ዓ. ም ለመፈጸም መዘጋጀታቸው ታውቋል። በየዓመቱ የሚደረግ ይህ የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ መሪ ርዕሥ “ፍጥረታትን ከጥፋት በመታደግ ሰላምን እናምጣ” የሚል መሆኑ ታውቋል። ዓላማው በተጨማሪም በሂሮሺማ እና ናጋሳኪ በተጣለው የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችን ለማስተወስ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ጭብጦች መካከል አንዱ ነው

የጃፓን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የናጋሳኪ ከተማ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ሚጿኪ ታካሚ የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአሥር ቀን የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ መሪ ርዕሥ የተወሰደው ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ ከኅዳር 23-26/2019 ዓ. ም በጃፓን ውስጥ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፣ በአገሪቱ ውስጥ የኒውክሌር ጦርነት እስከ ዛሬ ድረስ ያስከተለውን እና በማስከተል ላይ ያለውን ጥፋት እና ስጋት አስታውሰው ያደረጉትን ንግግር መሠረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የዓለም ሰላም ስጋት ውስጥ ይገኛል

ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ሚጿኪ በመልዕክታቸው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሰላም እና በመረጋጋት እጦት አደጋ ውስጥ መውደቁን አስታውሰው፣ ዛሬም በዓለማችን በጦር መሣሪያ የታገዙ አመጾች መኖራቸውን፣ ስደት እና መከራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን እና በአሜሪካ እና በቻይና መካከል የሚታየው ፍጥጫ አዲስ ቀዝቃዛ ጦርነትን ሊያስከትል እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። ይህ አስፈሪ ሁኔታ በሚታይባት ዓለማችን ውስጥ ትዕግስትን የተላበሰ የጋራ ውይይት በማድረግ ግንኙነቶችን ማሻሻል እንደሚገባ አሳስበዋል። ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ሚጿኪ አክለውም ኒውክሌር የጦር መሣሪያን መጠቀም እ. አ. አ ከዘንድሮ ጥር 22/2021 ዓ. ም ጀምሮ በሕግ የተከለከለ ቢሆንም በማጽደቁ ሂደት ውስጥ አሁንም ብዙ ያልተሳተፉ አገሮች መኖራቸውን ገልጸው፣ በተለያዩ የዓለማችን አካባቢዎች የሚታዩ አመጾች እና የጅምላ ጥፋት የሚያስከትሉ የጦር መሣሪያዎች መገኘት ለሰላም አስጊ መሆናቸውን አስረድተዋል። የጃፓን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የናጋሳኪ ከተማ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ሚጿኪ በመልዕክታቸው በሚያንማር እና አፍጋኒስታን በመሳሰሉ አገሮች ሰዎች ሰላምን ለማጣጣም የሚያስችላቸውን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት መነፈጋቸውን፣ የተሳሳተ መንገድ የሚከተሉ ባለ ሥልጣናት እና የጦር ኃይሎች ለእያንዳንዷ የሰው ሕይወት ክብርን ከመስጠት ይልቅ ለብሔራዊ ጸጥታ እና ሃብት ቅድሚያ መስጠትን መርጠዋል ብለዋል።

ዓለም የበለጠ መተባበርን ይጠይቃል

በመልዕክታቸው ዓለማችንን ክፉኛ የጎዳውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስ ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ሚጿኪ፣ ዓለማችን የበለጠ መተባበርን ይጠይቃል ብለው፣ ሃብታም አገራት ድሃ አገራትን በሚችሉት መጠን መደጋፍ እና ማገዝ እንዳለባቸው አሳስበው በተለይም ለሰው ልጅ በሙሉ እኩል ክብር በመስጠት በመካከላቸው ያለውን የእርስ በእርስ የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት ግንኙነት የበለጠ ሊያድግ ይገባል ብለው፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በአቡ ዳቢ ከተማ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም በሆኑት በአህመድ አል ጣይብ መካከል ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. የተፈረመውን የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድንም አስታውሰዋል።

ሕይወት ክቡር ነው

በሰዎች መካከል ልዩነትን ሳያደርጉ ለእያንዳንዱ ሕይወት ጥበቃን እና ከለላን መስጠት ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ሚጿኪ አስረድተው፣ ሰላምን ለማምጣት የሚደረግ ጥረት ነፍሳትን ከሞት ለማትረፍ ብቻ ሳይሆን ሰዎች በመካከላቸው ያካበቱት መልካም ግንኙነት በከንቱ እንዳይጠፋ መታደግ በመሆኑ አንዱን ከአደጋ መከላከል ማለት ሌላውንም ከጉዳት መከላከል መሆኑን አስረድተው፣ ሰላም መንገሥ ያለበት በሰዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በፍጥረታት ሁሉ መካከል ሊነግሥ ይገባል በማለት የጃፓን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የናጋሳኪ ከተማ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ሚጿኪ ታካሚ   መልዕክታቸውን አጠቃልለዋል።

እ. አ. አ በ1982 የተጀመረው የ “አሥር ቀናት የሰላም” ጸሎት መርሃ ግብር

በጃፓን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዘንድ እ. አ. አ ከ1982 ዓ. ም ወዲህ ሲካሄድ የቆየው የ “አሥር ቀናት የሰላም” ጸሎት መርሃ ግብር በጃፓን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት መልካም ፈቃድ የተጀመረው ሲሆን መነሻውም የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ የካቲት 25/1981 ዓ. ም. የሰላም አስፈላጊነትን በመጥቀስ ባስተላለፉት መልዕክት “ያለፈውን ታሪክ ማስታወስ የወደፊቱን ለመኖር ያግዛል” ማለታቸው ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስም እ. አ. አ በኅዳር ወር 2019 ዓ. ም. ወደ ጃፓን ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ኒውክሌር የጦር መሣሪያ ባለቤት መሆን ሥነ ምግባር የጎደለው ነው ማለታቸው ይታወሳል።

27 July 2021, 15:17