ፈልግ

በሚሞተው ሥጋችሁ ላይ ኃጢአትን አታንግሱበት በሚሞተው ሥጋችሁ ላይ ኃጢአትን አታንግሱበት  (ANSA)

በሚሞተው ሥጋችሁ ላይ ኃጢአትን አታንግሱበት

በሚሞተው ሰውነታችሁ ላይ ኃጢአት ሥልጣን እንዲኖረውና ለሥጋ ምኞት ተገዢ እንዲያደርጋችሁ አትፍቀዱለት፡፡

ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶን ከኃጢአት ተገዢነት ነፃ አወጣን፡፡ እርሱ ከመቃብር ሲነሳ እኛን ደግሞ ከኃጢአት ሞትና መጥፎ ኑሮ ለጸጋ ሕይወት በማስነሳት የእግዚአብሔር ልጆች አደረገን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደኀንነታችን የአምላክ ምሕረት እና ርኀራኄ፣ ትልቅ ጸጋ አንደሆነ እያስታወሰ እንደገና ወደ ኃጢአት እንዳንመለስና እንዳንጠፋ ይመክረናል፡፡

እንግዲያውስ በሚሞተው ሰውነታችሁ ላይ ኃጢአትን አታንግሱት፣ ሥልጣን እንዲኖረውም አትፍቀዱለት፣ ለምኞቱ አትገዙ፣ የሰውነታችሁን ክፍሎች የኃጢአትና የአመጽ መሣሪያ አታድርጉ፣ ከሞት እንደተነሳችሁ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፣ ለእርሱ ብቻ ተሰጡ፣ ለኃጢአት የሞትን ካልሆንን እንዴት ብለን በእርሱ እንኖራለን; እንግዲያውስ ኃጢአት እየገዛችሁ ለእርሱ ተገዢ አትሁኑ፣ ከሕግ ኃጢአት ሥር በባርነትና በግዞት አይደላችሁም፣ ከጸጋ በታች ናችሁ፡፡ እንግዲያውስ ኃጢአት አይግዛችሁ ተገዢነቱ ከሞት ሥር ነው፣ የጽድቅ ዋጋ ግን ሕይወት ነው´ (ሮሜ 6፣12-14)፡፡

አዎ የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው፤ የጽድቅ ደመወዝና ዋጋ ሕይወት ነው፡፡ የሰው ልጅ ኑሮ በኃጢአት የተበላሸ እና በዚህም የማይምር ኃይለኛ መርዝ የተበከለ ነው፡፡ ሰው ሳያሳሳት ሳይበድል ክቡር ደስተኛ እና ባለ ሰማያዊ ግርማ ሞገስ በመሆኑ የሕይወቱ ዕድል የሚያስደንቅ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ በሰይጣን ፈተና እና አይዞህ ባይነት ተሳስቶ ከወደቀ በኋላ ግን ከውድቀቱ በፊት የነበረውን ሀብትና ክቡር አጥፎቶ ለኃጢአት ተገዛ፣ በመከራና ለስቃይ የተዳረገ ሆነ፡፡ ያን ጊዜ ኑሮው ተበላሸበት፡፡ በዚህ አስከፊ ሁኔታ ወዶ የተቀበለው ጌታው ሰይጣን ብዙ አዋረደው፣ እንደባርያ እና ወራዳ አገልጋይ በጭቆናና በጭካኔ ረግጦ ገዛው፡፡ የሰው ልጅ ብርቱ ጸጸት እና ሐዘን ተሰማው፣ ጩኸትና ለቅሶውን ሰምቶ የአምላክ ልጅ ሊረዳውና ነፃ ሊያወጣው ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ንጹሕ ማሕፀን አድሮ ሥጋ ለብሶ ደኀንነትን እና ምስኪንነትን በፈቃዱ ተቀብሎ ወደ ዓለም መጣ፡፡ ክቡር ሕይወቱን ሰውቶ ደሙን አፍስሶ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞቶ አዳነው፡፡ ከጨካኝ ጌታው እጅ አስለቅቆ ነፃ አደገው፣ የመንፈስም ነፃነት በመስጠት ወደ ቀድሞው ጥሩ የጸጋ ኑሮው መለሰው፡፡ ከዚህ በኋላ ሰው ከራሱ ከአምላኩ ሰላምን አገኘ፣ ኃጢአት ሰውን እንዴት አድርጐ እንዳበላሸው እንመልከት፡፡ የአምላክ ልጅ ደግሞ ከኃጢአት ባርነት ቀንበር ሊያድነውና ነፃ ሊያወጣው ምን እንዳደረገ እናስተውል፡፡

በአምላክ ምሕረት አንድ ጊዜ ከኃጢአት ከዳንን እና ነፃ ከወጣን ወደ እርሱ እንመለስ፤ ያለብን ዕዳ ብርቱ እና ከባድ ነው፡፡ ዋጋውም የዘለዓለም ስቃይ በመሆኑ ከክርስቶስ የተቀበልነውን የነፃነት መንፈስ ተጠንቅቀን እናስተውለው እንጠብቀው፡፡ ይህን ክፉ ጨካኝ ጌታ ኃጢአት በላያችን እንዳናነግሰው እና ሥልጣን እንዳንሰጠው እንጠንቀቅ፡፡ የክርስቶስ የጦር መሣሪያ ታጥቀን ከእኛ ወዲያ እናርቀው፡፡

02 July 2021, 12:31